የደቡብ ክልል ምክር ቤት የሲዳማን ክልል ጥያቄ ተቀብሎ ረፈረንደም እንዲካሄድ ወሰነ

November 2, 2018

ለቀናት ጉባኤውን በሃዋሳ ሲያካሂድ የቆየው የደቡብ ክልል ምክር ቤት የየሲዳማ ዞን ክልል የመሆን ጥያቄ ህገ መንግስታዊ ሂደቱን ተከትሎ እንዲፈጸም ወሰነ።

የሲዳማ ሕዝብ የሀገሪቷ 10ኛ ክልል በመሆን የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እንዲቋቋም ላለፉት 27 ዓመታት ሲታገል መቆየቱን የሚገልጹ የሲዳማ ተወላጆች ደስታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ::

የደቡብ ክልል ምክር ቤት የሲዳማን ክልል የመሆን ጥያቄ ጉዳይ በዛሬው ውሎው 8ኛው አጀንዳ አድርጎ በዝግ እንደመከረበት የደረሰን መረጃ ጠቆሟል:: በመጨረሻም የሲዳማ ክልል የመሆን ጥያቄ ህገ መንግስታዊ ሂደቱን ተከትሎ እንዲፈጸም ውሳኔ አሳልፏል።

የሲዳማ ዞን ምክር ቤት ከዚህ ቀደም የዞኑን ክልል የመሆን ጥያቄ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ መደገፉን ዘ-ሐበሻ ዘግቦ ነበር:: በዚህም መሰረት የዞኑ ምክር ቤት መደገፉን ተከትሎ ጥያቄው ለክልሉ ምክር ቤት ቀርቦ ምክር ቤቱም በጥያቄው ላይ በዝግ ከመከረ በኋላ፥ የቀረበው ጥያቄ ህገ መንግስታዊ ሂደቱን ተከትሎ እንዲፈጸም ውሳኔ ማሳለፉ ተገልጿል::

ሲዳማ ክልል እንዲሆን ጥያቄ በማቅረብባቸው በርካታ ሰዎች ላለፉት 27 ዓመታት ሲታሰሩ; የአካል ጉዳት ሲደርሰባቸው እና ሌሎችም የሰብአዊ መብት ጥሰት ሲደርስባቸው መቆየቱን የሚያስታወሱ አስተያየት ሰጪዎች ሲዳማ 10ኛው ክልል ከሆነ መታሰቢያነቱ ለነዚህ ወገኖች መሆን አለበት ይላሉ::

በሌላ በኩል ሲዳማ ክልል ከሆነ የአዋሳ ከተማ እጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል የሚለው አነጋጋሪነቱን መቀጠሉን ከሚሰጡ አስተያየቶች ለመረዳት ተችሏል::

https://www.youtube.com/watch?v=_2J0KB91Nvc

Previous Story

ኦዴፓ እና ኦነግ ካድሬዎቻቸውን እንዲያሳርፉ ተጠየቁ

Next Story

ወ/ት ብርትኳን ሚዴቅሳ ወደ ኢትዮጵያ ልትገባ ነው

Go toTop