ፕሬዚደንቱ ዛሬ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ በጅግጅጋ ውስጥ በተፈጠረው ግጭት በጅምላ ከተቀበሩበት ጉድጓድ ተቆፍረው የወጡ አስከሬኖች መኖራቸውን አመልክተዋል፡፡ ቁፋሮው አሁንም እንደቀጠለ መሆኑን ያስረዱት አቶ ሙስጠፋ የሟቾች ቁጥር ወደፊት የሚገለፅ ቢሆንም በርካታ ሰዎች እንደተገደሉ ጠቁመዋል፡፡
‹‹በክልሉ ውስጥ የተፈጠረው ችግር ከሀምሌ 26 እስከ 30 ቀን 2010 በተፈጠረው ግጭት ብቻ የሚወሰን አይደለም፡፡ ከዚህ በፊትም በጠራራ ፀሀይ ንፁሀን ሰዎች ይገደላሉ፡፡ ይህ ጉዳ ወደፊት ተጣርቶ ለህግ የሚቀርብ ይሆናል፡፡›› ብለዋል ፕሬዚደንቱ፡፡
ለ11 አመታት ያህል ወደአገር ውስጥ እንዳይገቡ ተከልክለው የቆዩት አቶ ሙስጠፋ አገር እንዳይገቡ የተከለከሉበትን ምክንያትና የደረሰባቸውን ግፍም ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ አድርገዋል፡፡ በክልሉ ውስጥ የተወሰኑ ሀይሎች የትጥቅ ትግል ያካሂዱ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሙስጠፋ የታጠቁ ሀይሎችን የመዋጋቱ ሂደት እንደተጠበቀ ሆኖ በዚህ ሽፋን ንፁሀን ዜጎች መጎዳታቸውን አመልክተው ይህን አካሄድ በመቃወም ሃሳባቸውን በፅሁፍ ይገልፁ እንደነበር አስረድተዋል፡፡ ጨምረውም ‹‹ህዝብን በጎሳ ፈርጆ የመወንጀል፣ የማሰርና የማሰቃየት ሁኔታዎች በክልሉ ተስተውሏል፡፡ በዚህ ላይ የሰላ ትችት በማቅረቤ ነው እንደተቃዋሚ ታይቼ ችግር ውስጥ ሊያስገቡኝ ሲሉ የተሰደድኩት፡፡ ውጭ አገር ሆኜ የክልሉ መንግስት በሚሰራው የሰብአዊ መብት ጥሰት ዙሪያ የተለያዩ ፅሁፎችን እፅፍ ነበር፡፡ ይህ እንቅስቃሴዬ የክልሉንና የፌዴራል መንግስትን የሚወቅስ ነው በሚል እንዳልገባ ተከለከልኩ›› ብለዋል፡፡ እነአብዲ ኢሌ በዚህ ሳይወሰኑ በቤተሰቦቻቸው ላይ የከፋ ግፍ እንደደረሱባቸውም ተናግረዋል፡፡ ሲዘረዝሩም ‹‹አዛውንቱ አባቴ ተገርፏል፣ ወንድሜ ተገድሏል፡፡ አጠቃላይ ቤተሰቤ ተሰደው ወደኬንያ ገብተዋል፡፡ ያፈራነው ንብረትም ተወስዷል፣ ገና አሁን ተመልሶልን ነው እየተቋቋምን ያለነው›› በማለት አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል አልሸባብን በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው ፕሬዚደንቱ ‹‹አልሸባብ ሶማሊያ ውስጥ ነው ያለው፣ እስካሁን እኛ ክልል አልገባም፣ ህዝባዊ መሰረትም የለውም፡፡ እንደማንኛውም አሸባሪ ቡድን በማንኛውም ጊዜ ገብቶ አደጋዎችን ሊያደርስ ስለሚችል ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር ነቅተን እየጠበቅነው ነው፡፡›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በክልሉ አሁን ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ደግሞ ‹‹በሱማሊ ክልል እየተካሄደ ያለውን ለውጥ ለማደናቀፍ ለአንድ አፍታም የማይተኙ ሃይሎች አሉ፡፡ አሁን ፍልሚያችን ከእነሱ ጋር ነው፡፡ በተለያዩ ጥቅሞች የተሳሰሩ፣ ለረጅም ጊዜ ወንጀል ሲፈፅሙ የቆዩ አካላት ጉዳቸው እንዳይወጣ ለውጡን ለማደናቀፍ ሲረባረቡ ይታያል›› የሚል ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በመጨረሻም ‹‹አክቲቪስት ነበሩ ወይ?›› የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ‹‹እኔ አክቲቪስት አይደለሁም፡፡ በተለያዩ የብእር ስሞች እፅፍ ነበር፡፡ የስነፅሁፍ ዝንባሌ ስላለኝ ነው የምፅፈው›› ብለዋል፡፡
https://www.youtube.com/watch?v=pkxOggM328g&t=8s