ዶ/ር አብይ አህመድ “ኢትዮጵያ ማንም ትነስቶ እንደግል ቂጣ እንደፈለገው ጠፍጥፎ የሚጋግራት አይደለችም” አሉ

October 31, 2018

(ዘ-ሐበሻ) ከአውሮፓ ከተውጣጡ ኢትዮጵያውያን ጋር ለመወያየት ወደ ጀርመን ያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በፍራንክፈርት ኮሜርዝ ባንክ አሬና ስቴድየም ለተሰበሰቡ ኢትዮጵያውያን ባደረጉት ንግግር “”ኢትዮጵያ ማንም ትነስቶ እንደግል ቂጣ እንደፈለገው ጠፍጥፎ የሚጋግራት አይደለችም” ሲሉ ተናገሩ::

“አሁን ያላየነውን የምናይበት፤ ያልሞከርነውን የምንሞክርበት ጊዜ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ኢትዮጵያ ማንም ተነስቶ በወደደው ልክ እና ፍላጎት እንደ ቂጣ የሚጠፈጥፋት ሳትሆን ታላቅ ህዝብ የመሰረታት ታላቅ ሀገር ናት” ሲሉ ሕዝቡ በሆታና በጭብጨባ አስደግሟቸዋል::

“ሀገሬ አንቀላፍታ ይሆናል እንጂ አልሞተችም:: ኢትዮጵያ ደክማ ይሆናል እንጂ አልተሸነፈችም:: እምዬ ቀጥና ይሆናል እንጂ አልተበጠሰችም” በማለት ሕዝቡን ስሜት ውስጥ የከተተ ንግግር ያደረጉት ዶ/ር አብይ ባለፈ ታሪክ ሕዝብ መነታረኩን አቆሙ “እኔ ለሀገሬ ምን ሰራሁ እንጂ እነእገሌ ሀገሬን ጉድ ሰሯት ከማለት ጠብ የሚል ነገር የለም፡፡
” ማለት እንዲቆም ጠይቀዋል::

በሃገሪቱ ውስጥ ዴሞክራሲና ሰላም ሰፍኖ ወደ አውሮፓ ቢመጡ ደስ ይላቸው እንደነበር የገለጹት ዶ/ር አብይ ሆኖም ግን በሂደት ከሕዝቡ ጋር በመተባበር ሰላምን እና ዴሞክራሲን ለማስፈን እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል::

የፍራንክፈርቱ ኮሜርዝ ባንክ አሬና ከተጠበቀው ያነሰ ታዳሚ ለተገኘበት ምክንያት አዘጋጆቹ ዝግጅቱ ረቡዕ ቀን መደረጉን እና በርካታ ሰዎች ስራ ስላላቸው ከተለያዩ አውሮፓ ሃገራት መምጣት ስላልቻሉ ነው ይላሉ::

“ሀገራችን ከአውሮፓውያን ጋር ከጥንት ጀምሮ የቆየ ታሪካዊ ትስስር ነበራት፡፡ ይህ ለዛሬው ግንኙነታችን መሰረት ጥሏል፡፡ ጀርመናውያን በዓለም ጦርነት ወድማ የነበረችውን ሀገራቸውን መልሰው ለመገንባት የወሰደባቸው ከ40 ዓመታት ያልበለጠ ጊዜ ነው፡፡ አውሮፓውያን እርስ በርስ ከመሸናነፍ ይልቅ ድህነትን ማሸነፍ በመምረጣቸው ዛሬ እዚህ ደርሰዋል፡፡ ይህ ለኛ ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ትምህርት ይሰጠናል፡” ያሉት ዶ/ር አብይ “ኢትዮጵያዊነትን ከስሜት በዘለለ በስራ የምንገልፅበት ወቅት ላይ ነን፡፡

“ጠንክረን ካልሰራን ፍትሕና ዴሞክራሲ እንዲሁ አይመጣም፡፡ ተደምረን ተግተን ስንሰራ ብቻ ነው ይህ እውን ሊሆን የሚችለው፡፡ ለዚሁ ዓላማ ተቋማትን በመገንባት ኃላፊነታቸውንም በአግባቡ የሚወጡ ሰዎች በመመደብ ላይ እንገኛለን፡፡” ያሉት ዶ/ር አብይ “በምርጫ ቦርድ፣ መከላከያ፣ ፍትሕ፣ ትምህርት ወዘተ ተቋማት አስፈላጊውን ማሻሻያ በማድረግ ላይ እንገኛለን፡፡” ብለዋል::

“በቅርቡ በፍትሕ ዘርፉ ላይ ወሳኝ የሆኑ የማስተካከያ እርምጃዎች እንወስዳለን፡፡ ለነገው ትውልድ የምትሆን ኢትዮጵያን የመገንባት ፈታኝ ስራ ከፊታችን ይጠብቀናል፡፡” ያሉት ዶ/ር አብይ “እንደ ደቡብ ኮሪያው ጄነራል ፓርክ የወር ደመወዛችሁን አስይዛችሁ እንድትበደሩልን ሳይሆን በቀን ከአንድ ማኪያቶ 1 ዶላር እንድትሰጡን በድጋሚ እንለምናችኋለን፡፡” ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል::
https://www.youtube.com/watch?v=pkxOggM328g&t=7s

Previous Story

በአዲስ አበባ በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ 15 ተማሪዎች ራሳቸውን ስተው ወደቁ

Next Story

አዲሱ የሱማሌ ክልል ፕሬዚደንቱ አቶ ሙስጠፋ ማህመድ ኡመር በክልሉ በርካታ ሰዎ በጅምላ የተቀበሩበት ጉድጓድ መገኘቱን ገለፁ

Go toTop