የቀድሞው ብአዴን የአሁኑ አዴፓ በነበረከት ስምዖን ላይ ክስ ለመመስረት የመረጃ ማሰባሰብ ሥራ አጠናቀቀ

October 15, 2018

አቶ በረከት ስምዖን እና ታደሰ ካሳ ጥንቅሹን በጥረት ኮርፖሬት ውስጥ በፈጸሙት ጥፋት በሚል ምክንያት ከድርጅቱ አግዶ በኋላም ከማዕከላዊ ኮሚቴነት ያባረረው አዴፓ በነዚህ እና በሌሎችም የጥረት ኮርፖሬሽን ባለስልጣናት ላይ ክስ ለመመስረት የመረጃ ማሰባሰብ ሥራውን ማጠናቀቁ ተሰማ::

የአማራ ክልል መንግስት ቃል አቀባይ አቶ ንጉሡ ጥላሁን በስም አይጥቀሱ እንጂ “ከአሁን ቀደም የቀድሞው ብአዴን የአሁኑ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /አዴፓ/ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥረት ኮርፖሬትን አስመልክቶ ልዩ ልዩ ውሳኔዎችን ማስተላለፉን እናስታውሳለን:: በውሳኔውም መሰረት ጥረት የለውጥ እርምጃዎችን ጀምሯል:: የጥረት አምራሮች ሰሞኑን በተቋሙ ውስጥ ብልሹ አሰራር የፈጸሙ አካላትን ለህግ ለማቅረብ የኦዲትና የመረጃ ማሰባሰብ ስራ ተጠናቋል::” ሲሉ ይፋ አድርገዋል::

“በተቋሙ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የአሰራር ግድፈት ሲፈጸምበት የቆየ በመሆኑ የባከነ ሐብትና የከሰሩ ኩባንያዎችም እንዳሉ ተለይቷል ::
ኮርፖሬቱ በበላይነት የሚያስተዳራቸው ከ20 ኩባንያዎችና ፕሮጀክቶች በላይ ቢኖሩም በውስጣቸው በነበረው ብልሹ አሰራር ምክኒያት ውጤታማ እንዳልነበሩ በግልፅ ታውቋል፡፡” ያሉት አቶ ንጉሡ ተቋሙን በአዲስ ለማደራጀት ከጥረት ዋና መስሪያ ቤት ጅምሮ በሁሉም ኩባንያዎችና ፕሮጀክቶች ላይ አዳዲስ አሰራሮችን ለመዘርጋት የሪፎርም ስራና በሰለጠነ ሰው ኃይል የማደራጀት ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል::

እነበረከት ስምዖንን ብ አዴን ባወጣው መግለጫ በጥረት ኮርፖሬሽን ውስጥ ጥፋት በማጥፋት የተከሰሱ ቢሆንም ወዲያውኑ በሚዲያ ወጥተው ጥረትን ከወደቀበት አንስተው አትራፊ ድርጅት እንዳደረጉት; ምንም ጥፋት አለመፈጸማቸውን መግለጻቸው ይታወሳል:: አሁን አቶ ንጉሡ በለቀቁት መረጃ ለክስ የሚያበቃ መረጃ የተሰባሰበባቸውን ባለስልጣናት ስም ዝርዝር ባይጠቅሱም ድርጅቱ ቀደም ብሎ እነ በረከትን በጥፋት ተጠያቂ ማድረጉን የሚጠቅሱት ምንጮች መረጃው የተሰባሰበባቸው እነርሱው ናቸው ይላሉ::
እነ አቶ በረከት ስምዖን ኑሯቸውን ትግራይ ክልል ማድረጋቸው መዘገቡ ይታወሳል::

ጥረት ኮርፖሬት በስሩ የሚከተሉት 26 በስራ ላይ ያሉ እና በሒደት ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶች ያሉት ግዙፍ ተቋም ነው:: ያሉት አቶ ንጉሡ ድርጅቶቹን ዘርዝረዋቸዋል::

1. አምባሰል የንግድ ስራዎች ድርጅት
2. ዳሽን ቢራ ፋብሪካ
3. ዋሊያ ቆርኪ ፋብሪካ
4. ገንደ ውሃ የጥጥ መዳመጫ ፋብሪካ
5. ጎንደር ብቅል ፋብሪካ
6. ጣና ኮሙኒኬሽን የሞባይል መገጣጠሚያ
7. አዞላ ኤሌትሮኒክስ ፋብሪካ
8. ቲ ቲ እንጂኔሪንግ እና ማህበር
9. ላፓልማ ዳይቶማይት ፋብሪካ
10. ጀሪ የተፈጥሮ ምንጭ ውሀ ፋብሪካ
11.ተላጅ የልብስ ስፌት ፋብሪካ
12.የቆቦ ዶሮ እርባታ፤ እንስሳት ማድለብና ስጋ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ
13.ጣና ወረቀትና የወረቀት ውጤቶች ማምረቻ
14.ቢዲሲ ኮንስትራክሽን
15.ተከራርዋ የፕላስቲክ ማምረቻ
16. ዘለቀ እርሻ መካናይዜሽን
17.የዓሳ ልማት ፕሮጀክት
18. የትመን የጂፕሰምና የጅብሰም ውጤቶች ማምረቻ
19. ማዕድ የምግብ ኮምፕሌክስ ፕሮጀክት
20.ቲአይ ሜታልስ ፈርማንግ
21.የጁ ማርና የማር ውጤቶች ማምረቻ
22.የወተት ሀብት ልማት ማቀነባበሪያና የወተት ዱቄት ማምረቻ
23.ጥቁር አባይ ትራንስፖርት አ/ማ
24. እሸት ስታርችና የስታርች ውጤቶች ማምረቻ ፕሮጀክት
25. ጀርባ ፖኬጂንግ ፕሮጀክት
26.በለሳ የሎጂስቲክ አ.ማ
https://www.youtube.com/watch?v=dzVLCUTEMyY&t=3s

Previous Story

የሕግ ባለሙያው በግፍ የታፈሱት የአዲስ አበባ ወጣቶች ላይ የተፈፀመውን ሕገ መንግስታዊ ጥሰት ያብራራል! ደግሞኮ አያፍሩም ስለ ሕገ መንግስትም ያወራሉ

Next Story

አሥር ሴቶች የተካተቱበት የጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲሱ ካቢኔ በፓርላማ ፀደቀ | በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሴት መከላከያ ሚ/ር መረጠች

Go toTop