የፖለቲካ እስረኞችን የመፍታቱ ሂደት አሁንም ባለስልጣናቱን እያወዛገበ እንደሚገኝ ታወቀ፡፡ የኢህአዴግ ባለስልጣናት በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በኩል ባስተላለፉት መልዕክት፣ የፖለቲካ እስረኞችን እንደሚፈቱ መናገራቸው ይታወሳል፡፡ ይህ ከተገለጸ ወደ አስር ቀናት ቢቆጠሩም አሁንም ግን አንድም የፖለቲካ እስረኛ ሊፈታ አልቻለም፡፡ እንደ ምንጮች ገለጻ፤ ይህ መንጓተት የተፈጠረው፣ የትኞቹ የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ የሚለው ጥያቄ ባለስልጣናቱን እያወዛገበ ስለሚገኝ ነው፡፡
ወደ ኤርትራ ሲያመሩ የመን ላይ የተያዙት የግንቦት ሰባት ከፍተኛ አመራር አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ ባለስልጣናቱን ካወዛገቡ የፖለቲካ እስረኞች መካከል አንዱ መሆናቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ህወሓት አቶ አንዳርጋቸውን ሰንዓ ላይ ለመያዝ፣ ለየመን ደህንነቶች ከሶስት ሚሊዬን ብር በላይ የከፈለ ሲሆን፤ ይህ ሁሉ ወጪ የተደረገባቸውን እና የህወሓት ተቀናቃኝ የሆነውን የግንቦት ሰባት ከፍተኛ አመራር መፍታት ለባለስልጣናቱ አልተዋጠላቸውም-ይላሉ ምንጮች፡፡ የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የመፈታት ጉዳይ ቁጥራቸው ከፍ ባለ ባለስልጣናት በተለይም በህወሓት አመራሮች ዘንድ ተቃውሞ እንደገጠመው ከመረጃ ምንጮቹ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታም፤ ሌሎች የፖለቲካ እስረኞችን የመፍታቱ ነገር አሁንም ባለስልጣናቱን ወደ አንድ ስምምነት እንዳላመጣ ተጠቁሟል፡፡ ከጋዜጠኞች መካከልም የትኞቹን ፈትቶ የትኞቹን መተው እንደሚያስፈልግ ስምምነት ላይ ያልተደረሰ ሲሆን፤ አገዛዙ በእምነታቸው ውስጥ ጣልቃ መግባቱን ተከትሎ ተቃውሞ በማሰማታቸው የታሰሩ የኃይማኖት መሪዎችን የመፍታቱ ጉዳይም እስካሁን መቋጫ ሀሳብ አላገኘም፡፡ በተለይም፤ ባለፈው ዓመት ከተወሰኑ የኮሚቴው አባላት ጋር ሳይፈቱ የቀሩ እና አሁንም በእስር ላይ የሚገኙ የሙስሊም መፍትኤ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ጉዳይም ሌላው የባለስልጣናቱ መነታረኪያ አጀንዳ ሆኖ መቀጠሉም ታውቋል፡፡ እነማን ይፈቱ?… የሚለው ጥያቄ አሁንም መቋጫ አላገኘም ተብሏል፡፡
አገዛዙ እያደነ ያሰራቸው የፖለቲካ እስረኞች በርካታ መሆናቸው፣ ማንን ፈትቶ ማንን እንደሚተው፣ አልያም ሁሉንም ለመፍታት አወዛጋቢ ነገር ውስጥ እንዲገባ አስገድዶታል-እንደ መረጃዎች ገለጻ፡፡ የፈሰሰ ውሃ የሚታፈስ ቢሆን ኖሮ፣ የኢህአዴግ ሹማምንት ‹‹የፖለቲካ እስረኞችን አንፈታለን›› ብለው የተናገሩትን ቃል መልሰው ቢውጡት ደስ ይላቸው ነበር ሲሉ የገለጹ ታዛቢዎች፤ ‹‹እንደዛ ያሉት አምልጧቸው ነው!›› በማለት ገዥው ፓርቲ በገዛ እጁ የገባበትን ቅርቃር ገልጸውታል-ታዛቢዎቹ፡፡ እንደ ባለስልጣናቱ መወዛገብ እና አለመግባባት ከሆነ፣ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የሚፈታ የፖለቲካ እስረኛ አይኖርም ሲሉ ጠቁመዋል-ምንጮች፡፡
BBN Daily January 12, 2018