መንግስት ቅስቀሳውን ለማስተጓጎል ከ28 የአንድነት ፓርቲ አባላትን አስሯል
አንድነት ፓርቲ ዛሬ በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች የተሳካ የመኪና ላይና የቤትለቤት ቅስቀሳ ሲያደርግ ዋለ፡፡ መንግስት ቅስቀሳውን ለማስተጓጎል ከ28 አባላትን አስሯል፡፡ ፓርቲው የተከራያቸው የቅስቀሳ መኪኖች ታርጋቸውን በመፍታት ዳግመኛ ስራ እንዳይሰሩ በትራፊክ እንዲቀጡ ቢደረግም የመኪና ባለቤቶቹ ፣ ሾፌሮቹና ረዳቶቻቸው “ስራችን ስለሆነ ብቻ ሳይሆን ጭምር ዓላማችሁንም ስለምንደግፍ ከጎናቹ ነን ምንም አይነት ነገር ቢመጣ ወደ ኋላ አንልም” ብለዋል፡
#millonsofvoicesforfreedom#Ethiopia #UDJ
15 የሚሆኑ የአንድነት ፓርቲ አባለት ዛሬ ህገወጥ እስር ተፈፀመባቸው የተቀሩት ስኬታማ ቅስቀሳ በማድረግ ላይ ናቸው
አንድነት ፓርቲ በመጪው እሁድ መስከረም 19 ከ33ቱ ፓርቲዎች ጋር ለሚያደርገው ሰላማዊ ሰልፍ የመኪና ላይ ቅስቀሳ ሲያደርጉ የነበሩ 15 አባላቱ ህገወጥ እስር ተፈፀመባቸው፡፡ አባላቱ ከስድስት ኪሎ ወደ አራት ኪሎ በሚወስደው ጎዳና በመኪና ላይ እየቀሰቀሱ ባለበት ወቅት ሚኒሊክ ት/ቤት ፊትለፊት የፖሊስና የደህንነት ኃይሎች የሚተላለፈውን መኪና መንገድ በመዝጋት ቅስቀሳውን አደናቅፈዋል፡፡
በስፍራው የነበሩ በርካታ ሰዎች “ቀስቃሾቹ ህጋዊ ወረቀት ይዘዋል፤ልቀቋቸው” በማለት ተቃውሞ አሰምተዋል ከአንድነት ፓርቲ ጎን እንደሚቆሙም ተናግረዋል፡፡ ፖሊስ 15 የሚሆኑትን የቅስቀሳ ቡድን አባላት ወደ ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ ወስደዋቸዋል፡፡ የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች አባላቱ ወደ ታሰሩበት 2ኛ ፖሊስ ጣቢያ በመሄድ ረ/ኢ መንግስቱ ለማ የተባሉትን የፖሊስ ጣቢያው ኃላፊ የታሰሩት አባላት እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡ ኃላፊውም “ህጋዊ ሰልፍ እንደምታደርጉ እናውቃለን ይቀስቅሱ የሚል መመሪያ አልደረሰንም ብለዋል፡፡ አመራሮቹ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነርንና የከተማዋን መስተዳድር ሃላፊዎች ለማነጋገር ተንቀሳቅሰዋል፡፡
በተለያየ አቅጣጫ የተሰማሩት ሌሎቹ የአንድነት ፓርቲ ቅስቀሳ ቡድን አባላት ስኬታማ የመኪና ላይ ቅስቀሳ በማደረግ ላይ ናቸው፡፡