(የፎቶ ምንጭ ሐራ ተዋሕዶ ድረገጽ)በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀ/ስብከት ወንጪ ወረዳ ሐሮ ወንጪ ቀበሌ በሚገኘው የሐሮ ወንጪ መልአከ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል አንድነት ገዳም ላይ የቦምብ ጥቃት መፈጸሙን ሐራ ተዋሕዶ ድረ ገጽ ዘገበ። እንደ ድረ ገጹ ዘገባ “ጥቃቱ የተፈጸመው ጳጉሜ 4 ቀን 2005 ዓ.ም ምሽት 5፡00 ላይ ወደ ገዳሙ ቅጽር በተወረወረው ቦምብ ነው፡፡”
በገዳሙ የኪዳነ ምሕረት፣ ቅዱስ ገብርኤል፣ ቅዱስ ዑራኤልና ቅድስት አርሴማ ታቦታት መኖራቸውን የገለጹት የገዳሙ አበምኔት መልአከ ሰላም ቆሞስ አባ ገብረ እግዚአብሔር ኣብርሃ፣ የተወረወረው ቦምብ በገዳሙ ቅጽር ውስጥ ቢፈነዳም በመነኰሳቱ ላይ ያደረሰው ጉዳት አለመኖሩን ለዜና ሰዎች ተናግረዋል ያለው የድረ ገጺ ዘገባ “የአንድነት ገዳሙ አስተዳደር በቁጥር 17/2005 በቀን ፭/፲፫/፳፻፭ ለሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ፣ ለወንጪ ወረዳ መስተዳደርና ፖሊስ ጽ/ቤት በጻፈው የድረሱልን ጥሪ÷ ከዚህ ቀደም የገዳሙን ይዞታ በመጋፋት፣ መነኰሳቱና መናንያኑ ገዳሙን ለቀው እንዲሄዱ ተደጋጋሚ ዛቻና ስድብ በማሰማት የሚታወቁ 18 ግለሰቦችን በስም ለይቶ በመዘርዘር በጥቃቱ አድራሽነት እንደሚጠረጥራቸውና በቁጥጥር ሥር ውለው ሕጋዊ ርምጃ እንዲወሰድባቸው ጠይቋል፡፡ በስም ከተዘረዘሩት 18 ግለሰቦች መካከል ጌቱ ታደሰ እና መኰንን ካሳ የተባሉ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች የኾኑ የቀበሌው ነዋሪዎች በዋና አስተባባሪነት ተጠቅሰዋል፡፡” ብሏል።
ሀራ ጨምሮም “ደብዳቤው ‹‹ፀረ ሃይማኖት የኾኑ ግለሰቦች›› ሲል የገለጻቸውና በቡድን የሚንቀሳቀሱት እኒህ አካላት፣ በገዳሙ ላይ ከዘጠኝ ጊዜ በላይ የተለያዩ ጥቃቶችን በገዳሙና በገዳማውያኑ ላይ በማድረስ ንብረት ማውደማቸውንና መነኰሳቱን ማሳደዳቸውን ጠቅሷል፡፡ ‹‹ለቀበሌው ብዙ ጊዜ አመልክተናል፤ ከአቅሜ በላይ ነው በማለቱ መፍትሔ ሳናገኝ እስከ አሁን አለን›› በማለት ከግለሰቦቹ ጥቃት ባሻገር አስተዳደራዊ በደልም እየተፈጸመ እንደሚገኝ ደብዳቤው አጋልጧል፡፡” ብሏል።
እንደ ድረ ገጹ ዘገባ የወረዳውና ቀበሌው ባለሥልጣናት በተገኙበት ነሐሴ ፳፱ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም ከነዋሪው ጋራ በተደረገ ውይይት ሕዝቡ በቡድን እየተንቀሳቀሱ በገዳሙ ላይ ጥቃት የሚያደርሱ ግለሰቦችን የጠቆመ ቢኾንም ተገቢው ርምጃ ባለመወሰዱ÷ ግለሰቦቹ ገዳሙ በሚገለገልበት የውኃ ታንከርና የሶላር ቴክኖሎጂ ላይ ባደረሱት ጉዳት ሲስተሙ ለብልሽት ተደርጓል፤ መነኰሳቱ በሱባኤ ላይ ባሉበት ቀን ለቀን ወደ ገዳሙ ክልል ገብተው በይዞታው ላይ ችግኝ ከመትከል፣ የገዳሙ መውጫና መግቢያ በኾነ ቦታ ላይ አጥር ከማጠር አልተከለከሉም፤ ገዳማውያኑንም ‹‹ከዚህ ቦታ ባትመጡ ይሻል ነበር፤ ለዛሬ ብቻ ነው የምትኖሩት፤ ብትውሉ አታድሩም›› እያሉ በስልክና በአካል በተደጋጋሚ ዛቻና ስድብ ከማስፈራራት አልታቀቡም፡፡ ‹‹በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በየዕለቱ ጨለማን ተገን በማድረግ የሚሰነዘርብን ጥቃት በዘመናዊ የጦር መሣርያ ጭምር የታገዘና በቀጣይም እየተጠናከረ እንደሚሄድ ያሳያል›› ያለው የገዳሙ አስተዳደር÷ ነሐሴ ፲፬ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም ከሌሊቱ 7፡40 ዘመናዊ የጦር መሣርያ ታጥቀው ወደ መናንያኑ መኖርያ የመጡት ግለሰቦቹ በመናንያኑ መኖርያዎች ላይ የድንጋይ ውርጅበኝ ማዝነባቸውን፣ ጥይት መተኰሳቸውን፣ ገዳሙን በጥበቃ እንዲያገለግሉ የተቀጠሩ የአካባቢው ተወላጆች ሥራቸውን እንዲተዉ ያልተሳካ ሙከራ ማድረጋቸውን አስታውሷል፡፡
ሀራ ዘገባውን ቀጥሎ “ገዳሙ ይዞታውን በሕግ ያረጋገጠበት ደብተር እንዳለው የጠቀሰው አስተዳደሩ የሹራብ ሽመና፣ የዶርና እንስሳት ርባታን ጨምሮ ራሱን የሚያግዝበት የልማት ጅምሮችና ዕቅዶች ቢኖሩትም ፍትሕ እያጡ በሚሰደዱት መነኰሳት ምክንያት ጥረቱ እየተሰናከለ ነው፤ በገዳሙ ምሥረታ ከነበሩት 15 መነኰሳት መካከልም ጸንተው የቀሩት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ወረዳው በተለይ ከ፳፻፬ ዓ.ም ጀምሮ ከገዳሙ ለሚቀርቡለት አቤቱታዎች ሁልጊዜ ተስፋ ይሰጠናል እንጂ የተጨበጠ ነገር አላስገኘልንም፤ ትኩረትም አይሰጡትም ያለው አስተዳደሩ÷ ‹‹መንግሥት ለሃይማኖታችንና ለገዳማችን ልማት የማይተኙልንን ፀረ ሃይማኖት የኾኑ ግለሰቦች›› በአስቸኳይ በቁጥጥር ሥር እንዲያውልና ሕጋዊ ርምጃ እንዲወስድባቸው ጠይቋል፡፡ ብሏል።