በምዕራብ ጎጃም መራዊ ላይ የታሰሩት ወጣቶች ከፍተኛ ድብደባ ተፈፀመባቸው

November 25, 2015

• ሁለቱ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ናቸው

(ነገረ ኢትዮጵያ) ህዳር 4/2008 ዓ.ም በምዕራብ ጎጃም ዞን መራዊ ከተማ የታሰሩት 8 ወጣቶች ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈፀመባቸው ምንጮች ለነገረ ኢትዮጵያ ገለፁ፡፡ ህዳር 4/2008 ዓ.ም በሌሊት ቤታቸውን ተበርብሮ ከታሰሩት መካከል በተለይም የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች የሆኑት አቶ መኳንንት ፀጋዬ እና አቶ እያዩ መጣ ከፍተኛ ድብደባ እንደደረሰባቸው ታውቋል፡፡ ህዳር 4/2008 ዓ.ም ጣቢያ ዘጠኝ ተብሎ ወደሚታወቀው እስር ቤት ተወስደው እንደተደበደቡ የገለፁት ምንጮቹ ህዳር 9/2008 ዓ.ም ፍርድ ቤት ቀርበው ወደ ማረሚያ ቤት እንዲዛወሩ ትዕዛዝ ቢሰጥም ፖሊስ ባህርዳር ከተማ በሚገኘው ጣቢያ ዘጠኝ የተባለ እስር ቤት በመውሰድ እስከ ህዳር 14/2008 ዓ.ም ከፍተኛ ድብደባ ፈፅሞባቸዋል፡፡
ፖሊስ እስረኞቹን ወደ ማረሚያ ቤት እንዲያዛውር ትዕዛዝ ተሰጥቶት የነበር ቢሆንም እስረኞቹ ፍርድ ቤት ቀርበው ጣቢያ ዘጠኝ በተባለው እስር ቤት ከፍተኛ ድብደባ እንደደረሰባቸው በመግለፃቸው ‹‹ለፍርድ ቤቱ ለምን ተደበደብን ብላችሁ ተናገራችሁ?›› በሚል ለተጨማሪ 5 ቀናት ድብደባው እንደተፈፀመባቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡ እስረኞቹ ድብደባው የሚፈፀምባቸው ‹‹ለምን የተቃውሞ እንቅስቃሴያችሁን አታቆሙም? ከተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ጋር ያላችሁን ግንኙነት ለምን አታቆሙም?›› እየተባሉ መሆኑንም ምንጮች ገልፀዋል፡፡
ህዳር 4/2008 ዓ.ም ታስረው ድብደባ የተፈፀመባቸው እስረኞች፡-
1. መኳንንት ፀጋዬ
2. እያዩ መጣ
3. መምህር ሀምታሙ ጥላሁን
4. ስማቸው ማዘንጊያ
5. ቄስ ዘላለም ሞትባይኖር
6. አረጋዊ መጣ
7. ሽባባው የኔዓለም እና
8. አብርሃም ተስፋ ሲሆኑ አብርሃም ተስፋ የኢህአዴግ አባል እንደሆነ ታውቋል፡፡

Previous Story

Hiber Radio: በሊቢያ በግፍ ለተገደሉ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን እጁ ያለበት ያሸባሪዎች መሪ አሜሪካ በወሰደችው ጥቃት ሳይገደል እንዳልቀረ ተገለጸ | የሎስ አንጀለስ ፖሊስ አንድ የቀድሞ የኢትዮጵያን መኮንን አፋልጉኝ አለ | ዶ/ር ኑሩ ደደፎ ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር ይናገራሉ | የአርበኞች ግንቦት 7 በሳን ሆሴ የተደረገ የገቢ ማሰባሰቢያ ለነጻነት ትግሉ የኢትዮጵያውያን ምላሽ | የኢትዮ-ኬኒያ ድንበር ወታደራዊ ውጥረት አይሏል፣ኢትዮጵያ የድንበር ኬላዎቿን ዘጋች… ሌሎችም ዜናዎች አሉ

Next Story

ከመጠምጠም መማር ይቅደም | መስፍን ወልደ ማርያም [ፕሮፌሰር]

Go toTop