ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ላልተወሰነ ጊዜ ወደ ቃሊቲ ተዛወረ

September 17, 2014

(ነገረ ኢትዮጵያ) በሽብርተኝነት ክስ ጥፋተኛ ነህ ተብሎ የአስራ አራት አመት እስር የተፈረደበት ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ በእስር ከሚገኝበት የዝዋይ እስር ቤት ላልተወሰነ ጊዜ ወደ ቃሊቲ ተዛወረ፡፡

የጋዜጠኛ ውብሸት ባለቤት ወ/ሮ ብርሃኔ ተስፋዬ ለነገረ ኢትዮጵያ እንደገለጸችው ውብሸት ከዝዋይ ወደ ቃሊቲ ከተዛወረ ቀናት ተቆጥረዋል፡፡ ‹‹ሆኖም ግን ብዙ ሰዎች ውብሸት ወደ ቃሊቲ መዛወሩን መረጃው የላቸውም›› ያለችው ወ/ሮ ብርሃኔ፣ ‹‹አሁን ውብሸት ቃሊቲ በፊት ለፊት በር በኩል ዋይታ ቤት በሚባለው በኩል ይገኛል፡፡ ከሰኞ እስከ አርብ ሙሉ ቀን ሊጠይቀው የፈቀደ ሁሉ መጠየቅ ይችላል›› ብላለች፡፡

ውብሸት ወደ ቃሊቲ የተዛወረበት ምክንያት የቤተሰብ ጉዳይ ስላለበት መሆኑን የጠቀሰችው ወ/ሮ ብርሃኔ ባለቤቷ ቃሊቲ የሚቆየው ላልተወሰነ ጊዜ መሆኑን ገልጻለች፡፡ ‹‹እስከ መቼ ቃሊቲ እንደሚቆይ ባላውቅም መስከረም 29 ቀጠሮ ስላለው እስከዚያው በዚሁ እንደሚቆይ እገምታለሁ›› ብላለች፡፡
ጋዜጠኛ ውብሸት የአንድ ልጅ አባት ሲሆን ቀደም ሲል ዝዋይ እስር ቤት እያለ ልጁን ለማየት ፈተና እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ ‹‹አሁን ለጊዜውም ቢሆን ልጃችንን ይዠ ስለምጠይቀው ልጁን ቶሎ ቶሎ ማየት ችሏል›› ስትል ወ/ሮ ብርሃኔ ለነገረ ኢትዮጵያ ተናግራለች፡፡
የውብሸት ልጅ ፍትህ ውብሸት ይባላል፡፡ ይህ ህጻን ‹‹እኔም ሳድግ እንደ አባቴ እታሰራለሁ?›› ሲል መጠየቁ ይታወሳል፡፡

በሌላ በኩል ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ በእስር ቤት ሆኖ የጻፈው ‹‹የነጻነት ድምጾች›› መጽሐፍ ለንባብ መብቃቱን ባለቤቱ ወ/ሮ ብርሃኔ ገልጻለች፡፡

Previous Story

Health: የሰውነት መቆጣት (አለርጂ)

Next Story

Health: ‹‹አርትራይተስ››:- ዛሬም ቢሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በዚሁ በሽታ ይሰቃያሉ

Go toTop