በፕሮፌሽናል እግርኳስ ተጨዋቾች ማህበር በሚደረገው ዓመታዊ ምርጫ ላይ በዘንድሮው ምርጥ 11 የተካተቱትን ተጨዋቾች ልብ በሉ፡፡ ፔትር ቼክ፣ ሉክ ሾው፣ ጋሪ ኬሂል፣ ቨንሳ ኮምፓኒ፣ ሺመስ ኮልማን፣ አዳም ላላና፣ ያያ ቱሬ፣ ስቲቭን ዤራርድ፣ ኤዴን ሃዛርድ፣ ሉዊስ ሱአሬዝ እና ዳንኤል ስተሪጅ ናቸው፡፡ 11ዱ ተጨዋቾች የሚያመሳስላቸው አንድ አብይ ነጥብ ቢኖር ሁሉም እየተጫወቱበት ወዳለው ክለብ የመጡት ዘንድሮ አይደለም፡፡ ቢያንስ ቢያንስ አምና የፈረሙ ናቸው፡፡ በዚህ ምርጫ ላይ ዘንድሮ የፈረመ ተጨዋች በምርጥ 11 ውስጥ ሳይካተት ሲቀር ባለፉት 10 ዓመታት ውስጥ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ለተጨዋቾች ዝውውር 760 ሚሊዮን ፓውንድ አውጥተዋል፡፡ ሪከርድ ቢመዘገብም በተጠቀሰው ገንዘብ ከተገዙት ተጨዋቾች መካከል አንዱ እንኳን ነጥሮ በመውጣት በምርጥ 11 ውስጥ መካተት አልቻለም፡፡
ከ760 ሚሊዮን ፓውንዱ ውስጥ 250 ሚሊዮን ፓውንድ የተከፈለው ለስምንት ተጨዋቾች ነው፡፡ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በነፍስ ወከፍ 25 ሚሊዮን ፓውንድና ከዚያ በላይ ተከፈለባቸው ተጨዋቾች ብዛት ስምንት ደርሷል፡፡ ገንዘብ የግድ ስኬትን ይገዛል ማለት አይቻልም፡፡ ሉዊዝ ሱአሬዝ ለብቻው ከስምንቱ በላይ ጎሎችን አስቆጥሯል፡፡ የሊቨርፑሉን አጥቂ ምርጥ ውድድር ዘመን ወደ ጎን እንተወውና የስምንቱን ታላላቅ ግዢዎች ውጤታማነት እንመልከት፡፡ እነዚህ ተጨዋቾች የበለጠውን ጎል እንዲያስቆጥሩ የተገዙ ቢሆንም በውድድር ዘመኑ እያንዳንዳቸው በአማካይ 35 ጎል ብቻ አግብተዋል፡፡ ሜሱት ኦዚል፣ ሁዋን ማታ፣ ፈርናንዲንሆ፣ ዊልያም ማርዊን ፌቫይኒ፣ ሮቤርቶ ሶልዳዶ፣ ኤሪክ ላሜላ እና ስቲቭን ዮቬቲች ገንዘብ ባክኖባቸዋል? ወይስ በፕሪሚየር ሊጉ ላይ ከፍ ያለ ተሰጥኦ ያላቸው ተጨዋቾች በዝተው የእነዚህን ብቃት አጉልቶ ለማየት ተችግረናል? የትኛውም የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አድናቂ ሁለተኛውን አማራጭ በመልስነት አያቀርብም፡፡ ከ25 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ ከተከፈለባቸው ስምንቱ ተጨዋቾች መካከል ፈርናንዲንሆና ዊልያን ብቻ የወጣባቸውን ዋጋ የሚመጥን አገልግሎት ወደመስጠቱ ቀርበዋል፡፡ ስለተቀሩት ዝም ማለት ይሻላል፡፡
የተከላካይ አማካዩ ፈርናንዲንሆ ብቃትና ተሰጥኦ በስታስቲክሳዊ ትንተና የሚረጋገጥ አይደለም፡፡ በማኑኤል ፔሌግሪኒ ቡድን ውስጥ የተጋጣሚን ተከላካይ ክፍል ለመጠርመስ የሚያስችልን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማስጀመር ቁልፉን ሚና የሚወጣው ብራዚላዊው ነው፡፡ ለማንቸስተር ሲቲ ኃያልነት የፈርናንዲንሆ አስተዋፅኦ የተረጋገጠ ድጋፍ መሆኑን የሚሟገት የለም፡፡
ኦዚል፣ ማታ እና ዊልያን ለወደፊቱ ክለቦቻቸው ሊጠቀሙባቸው የሚችሉ ተጨዋቾች መሆናቸውን የሚሟገት የለም፡፡ ከሚቀጥለው የውድድር ዘመን አንስቶ ለረጅም ጊዜ የክለቦቻቸው መመኪያ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ለወደፊቱ ክለቦቻቸውን የሚያኮራ አገልግሎት ይሰጡ ዘንድ መነሳሻ እንዲሆኗቸው ያያ ቱሬ፣ ዴቪድ ሲልቫ እና ዴቪድ ሉዊዝን መመልከት ይችላሉ፡፡ ሶስቱም ተጨዋቾች ለእያንዳንዳቸው ከ25 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ መዋዕለ ንዋይ የፈሰሰባቸው ሲሆኑ በፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ዓመት ላይ ለመልመድ ተቸግረው ነበር፡፡
ሆኖም ለሚቀጥለው ዓመት በበለጠ ብቃት ብቅ ይላሉ ብሎ ዋስትና መስተት አይቻልም፡፡ ጆዜ ሞውሪንሆ ወፈፍ ካደረጋቸው በድንገት ኦስካር፣ ሃዘርድ፣ አንድሬ ሹርለ፣ መሐመድ ሳላህና የመሳሰሉትን በክለቡ ለማቆየት ወይም ሌላ ለመግዛት ሲሉ ዊልያንን ሊሸጡት ይችላሉ፡፡ የማንቸስተር ዩናይትዱ አዲሱ አሰልጣን ሉዊ ቫን ሀል አዲሱን ቡድናቸውን በማታ ዙሪያ ሊገነቡ ያቅዱ ይሆናል፡፡ ወይም ማታን አልፈልገውም በሚል ሸጠውት በምትኩ የተመኙትን ተጨዋች ሊያስፈርሙ ይችላሉ፡፡
ምናልባት ላሜላ እና ዮቬቲች በውድድር ዘመኑ በቋሚነት ርቀው ለመቆየታቸው መጎዳታቸውን በሰበብነት ያቀርቡ ይሆናል፡፡ እንዲህ አይነቱ ሰበብ ለፌላይኒ እና ሶልዳዶ ሊቀርብ አይችልም፡፡ ሁለቱ ተጨዋቾች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፕሪሚየር ሊጉ ላይ በከፍተኛ ገንዘብ ተገዝተው እንደህ ነው የሚባል አገልግሎት መስጠት ያቃታቸው ተጫዋቾች ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ፈርናንዶ ቶሬስና ሮቢንሆን ጨምረን የወጣባቸውን ከፍተኛ ገንዘብ በውጤታማነታቸው መመለስ ያልቻሉ ተጨዋቾች ተደርገው በግንባር ቀደምትነት ይወሰዳሉ፡፡
መቼም ከ25 ሚ.ፓ. በላይ ወጪ የተደረገበት ተጨዋች ሁሉ ግድ ደምቆ መታየት አለበት የሚል እምነት ላይኖር ይችላል፡፡ ሆኖም 250 ሚሊዮን ፓውንድ ከወጣባቸው ተጨዋቾች መካከል አብዛኛዎቹ የተጠበቁትን ያህል ሆነው መገኘት አለባቸው፡፡
በ2012/13 (አምና) በፕሪሚየር ሊጉ የተጨዋቾች ዝውውር ከ25 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ ከወጣባቸው ሁለት ተጨዋቾች የውድድር ዘመኑን በድንቅ ውጤታማነት አጠናቀዋል፡፡ ሮቢን ቫን ፔርሲ (26 ጎሎችን ያስቆጠረና የፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ማህበር ኮከብ ተጨዋች ተብሎ የተመረጠ)፣ ኤዴን ሃዛርድ (14 ጎሎችን ያስቆጠረ፣ ጎል የሆኑ 10 ኳሶችን ያቀበለና በማህበሩ ምርጥ 11 ውስጥ የተካተተ) ይጠቀሳሉ፡፡ ቀደም ባለው ዓመት (ካቻምና) በተመሳሳይ ዋጋ የተገዙ ሁለት ተጨዋቾች ብቻ ነበሩ፡፡ ሁለቱም ስኬታማ ዘመን አሳልፈዋል፡፡ ሰርጂዮ አጉዌሮ (23 ጎሎችን ያስቆጠረ) እና ማታ (ስድስት ጎሎችን ያስቆጠረና ጎል የሆኑ 16 ኳሶችን ያቀበለ) ናቸው፡፡
ትንንሾቹን ክለቦች ብንመለከትም እንደ አቅማቸው ከፍተኛ ሂሳብ የተከፈሉባቸው ተጨዋቾቻቸውም አልተሳካላቸውም፡፡ ኖርዊች ሲቲ የራሱን የዝውውር ሪከርድ ሰብሮ ሪኪ ቫን ቮልፍቪንኬልን በ75 ሚሊዮን ፓውንድ ቢያስፈርምም ከአጥቂው ያገኘው አንድ ጎል ብቻ ነው፡፡ ዌስትሃምም አንዲ ካሮልን በቋሚ ዝውውር ሲያስፈርም 15 ሚሊዮን ፓውንድ ከፍሎበታል፡፡ ለዳ ኦዝቫልዶ ሳውዛምፕተን 15 ሚሊዮን ፓውንድ ከፍሎ የእርሱን የዝውውር ሪከርድ አሻሽሏል፡፡ ሆኖም ኦዝቫልዶ ለሳውዛምፕተን ለመጨረሻ ጊዜ የተሰለፈው በዲሴምበር ወር ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ጭራሹኑ በጃንዋሪ ክለቡን ለቅቋል፡፡ ፉልሃምም እንዲሁ ክስታስ ሜትሮግሉ ለተባለው ተጨዋቹ ግዢ የራሱን ሪከርድ ሰብሯል፡፡ የግሪኩ አጥቂ ግን በሊጉ ላይ ሶስት ጨዋታዎችን ብቻ ከማድረግ ማለፍ አልቻለም፡፡ የለንደኑ ክለብ በፕሪሚየር ሊጉ ላይ መቆየት ህልሙ በመጨረሻ ጨንግፎ ወደ ቻምፒዮንሺፑ ተሰናብቷል፡፡
በመጪው የውድድር ዘመን ዘንድሮ ከተገዙት ተጨዋቾች የበለጠ ማግኘት ይቻል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ዳንኤል ሌቪ እና ኢቫን ጋዚዲዝን ለመሳሰሉት ገንዘብ ከፋዮች ዋስትና መስጠት ይቸግራል፡፡ ፈጥነው ውጤትን የሚፈልጉ ሰዎች ናቸውና፡፡