April 2014
የትንሳኤ ጥሪ
ጋዜጣዊ መግለጫ
ዉድ ወገኖቻችን !
ኢሕአፓ ከተመሰረተ ይሄዉና አርባ ሁለት አመቱን አስቆጠረ ።ለድርጂቱ መመስረት ዋና ዋና ናቸዉ የሚባሉት የሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት ጥያቄና የመሰረታዊ መብቶች ጥያቄ ግን አሁንም መልስ አላገኙም፣ እንዲያዉም ከመሰረታዊ የሕዝብ መብቶች ጥያቄ ባሻገር ባደጋ ላይ የወደቀዉን የሃገር ሉዓላዊነት ጥያቄ ለመመለስ ትግል ግድ እየሆነ መጥቶአል።
ዛሬ ኢሕአድግ/ወያኔ በሚከተለዉ የፖለቲካ መስመር ምክንያት እየተበረታቱ በቋንቋና በሃይማኖት ክልል ተሰባስቦ መደራጀት በመስፋፋት ላይ ነዉ።በዚህም ምክንያት ጥራት ያለዉና ጠንካራ ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍሎች በማሰባሰብ ትግሉን የሚመራ ድርጅት ጎልቶ ሊወጣ አለመቻሉ አሳዛኝ ክስተት ሆኗል።
ያ ትዉልድ በኢትዮዽያዊነቱ በመኩራት ለመላዉ የኢትዮዽያ ህዝብ መብት መከበር ያደረገዉ ትግል እንደ ትልቅ ትዝታ በየቦታዉ የሚነሳ ቢሆንም ከመሰዋአትነት የተረፉት የዚያ ትዉልድ አካሎች በልዩ ልዩ ምክንያት አሁንም እየተከፋፈሉ በመምጣታቸዉ “ምነዉ የጀመሩትን ትልቅ አላማ ከግቡ ለማድረስ ተቻችለዉ ትግላቸዉን አይቀጥሉም? የከፈሉት መሰዋአትነት ሳያንስ ለምን ታሪካቸዉን አያስከብሩም? ምነዉ ተክቶን ታጋይ አልፎአል የኛም ትግል ይቀጥላል ፣ልጔዝ በድል ጎዳና በተሰዉት ጔዶች ፋና”እያሉ በመዘመር የገቡትን ቃል ኪዳን ለምን ከፍፃሜ አያደርሱም?” በማለት የሚጠይቀዉ የሕብረተሰብ ክፍል ቀላል አይደለም።
በተለይም ደግሞ አዲሱ ትዉልድ እንደ ዓረዓያ ሆኖ የሚታይ ኃይል ከፊቱ ማየት በመፈለጉ ከዚያ ቅን አገርና ወገን አፍቃሪ ትዉልድ ከፍተኛ ሥራ ሲጠብቅ ከግምት በታች ሆኖ መገኝቱ ለህሊና ሰላም የሚሰጥ ጉዳይ ሆኖ አልተገኝም። አዎ ምንም እንኳን የመከፋፈል ችግር ቢገጥመዉም በኢሕአፓ ሥም ተሰልፈዉ የሚታገሉ ሐይሎች እንዳሉ ሁላችንም የምናዉቀዉ ገሀድ ነዉ።በሌላ በኩል ደግሞ ከድርጂት ዉጭ ሆነዉ ለትገሉና ለድርጂቱ በነበራቸዉና አሁንም በላቸዉ ቀና አመለካከት ልባቸዉ የሚቃጠል በጣም በርካታ የዚያ ትዉልድ አካሎች መኖራቸዉ የሚካድ አይደለም።
ታዲያ ይህን ሁኔታ የተገነዘብን የዚያ ትዉልድ አካሎች ያን ጀግና ኢትዮጲዊ ትዉልድ እንደገና አሰባስቦ መንቀሳቀስ ቢቻል ለኢትዮዺያና ለኢትዮዺያዉያን ትልቅ ጥቅም ያስገኛል የሚል ሙሉ እምነት ስለአለን ይህን ስብስብ ጀምረናል።
ይህ እንቅስቃሴ ለዚያ ባለራዕይ ትዉልድ የትንሳኤ ጥሪ ከመሆኑም ባሻግር አዲሱን ትዉልድ በተአምር ከመስዋእትነት ከተረፈዉ ከዚያ ትዉልድ ጋር እንደ ድርና ማግ አስተሳስሮ ለአገር ሉዓላዊነትና ለመላዉ ህዝብ መብት መከበር ሁሉንም የኢትዮዺያ ልጆች የሚያሳትፍ እንደ ጎሞራ እሳት የሚቀጣጠል ትግል ለመፍጠር አስተዋፅኦ ያደርጋል የሚል ፅኑ እምነት አለን።
ስለዚህ ያ ትዉልድ ላደረገዉ ትግል አክብሮት ያለዉ፣ ለከፈለዉም መሰዋትነት የሚቆረቆር፣በቅንነት የተከፈለዉ የመስዋእትነት ታሪክ ሲበላሽ አላይም የሚል፤ ለሃገሬ የወደፊት እጣ ፋንታ እጄን አጣጥፌ ፣አፌን ቆልፌ፣ለወሬ ተሰልፌ፣ በተግባር ሰንፌ መቀመጥ በቃኝ ያለ፣መላዉ የኢትዮጲያ ህዝብ በእኩልነት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብተቶቹ ተከብረዉ እንዲኖር የምትፈልጉ፣ኢትዮጵያ እንደ ሃገር ሉአላዊነትዋ ተከብሮ መቀጠልዋን የትወዱ፣ የዚያ ትዉልድ አካሎች በዚህ እንቅስቃሴ ንቁ ተካፋይ እንድትሆኑ በአክብሮት ጥሪያችንን እናቀርባለን።
እንቅስቃሴዉ አንዱን ከዉስጥ አንዱን ከዉጭ የሚያስቀምጥ ሳይሆን ሁሉንም የዚያ ትዉልድ አካሎች በእኩልነት የሚያይና የሚጋብዝ በመሆኑ በተጠቀሰዉ የኢሜል (e-mail) እድራሻ በመጠቀም በቀጥታ በዚህ እንቅስቃሴ መሳተፍ የምትችሉ መሆኑን እንገልጻለን።በቂ ዝገጅትም ካደረግን በኃላ የተሟላ ሥብሠባ በማድለግ በጋራ የምንሄድበትን አቅጣጫ የምንወስን መሆኑን ከወዲሁ እንገልጣለን።
ይህንን ስብስብ እንድንፈጥር ካነሳሱን ዓላማዎች በጥቂቱ :
1/አሁን በመታገል ላይ ባሉት የኢሕፓ አካሎችና ከዉጭም ባሉት ቆራጥ የኢሕአፓ ልጆች ማህከል መከፋፈሉ ቀርቶ ተሰባስበዉ ጠንካራ ኃይል ሆነዉ የሚወጡበትን ምንገድ ለማመቻቸት።
2/በጥናት ላይ የተመሰረተ እስከተቻለ ድረስ ሁሉን ጔዶች እና ሁሉንም እካባቢዋች ያካተተ ታሪካችን እንዲጻፍ ለማስተባበር የሚፅፉትንም ለመደገፍ።
3/በኢሕአፓ የትግል ታሪክና መታሰቢያዎች ዙራያ የሚሰሩ ሥራዋችን በመተባበር ለመሰራት።
4/በትግሉ መሰዋዓትነት የከፈሉትን ጔዶች የህይወት ታሪክ በማፈላለግና በማሰባሰብ ሥርዓት ባለዉ መልክ እንዲዘጋጁ ለማድረግ ከሚያደርጉም ሀይሎች ጋር ለመተባበርና ለመርዳት።
5/ድርጂታችን ባካሄደዉ ትግል ላይ የተለያዩ ፅሑፎችን (መፃህፍትና አርቲክሎችን) በመፃፍ የዚያን ጀግና ትዉልድ ታሪክ የሚያጠፉትን ኃይሎች ለመቋቋም።
6/በሃገራችን ጉዳይ ላይ ሰፊና መሰረት ያለዉ ዉይይት በማካሄድ የሃገራችን የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ አወንታዊ ኃይል ሆኖ ለመዉጣት መዘጋጀት። የሚሉት ጥቂቶቹ ናቸው
በዚህ ስብስብ ውስት ለመሳተፍ ለመደገፍና ለመገናኛት በዚህ e mail ተጠቀሙ
Tinsae@yahoogroups.com
ማሳሰቢያ
በዚህ ዓይነት ተመሳሳይ አላማ የሚንቀሳቀሱ ቡዱኖች ካሉ አብረን ለመስራት ሙሉ ፈቃደኞች መሆናችንን አስቀድመን እንገልጻለን
ሰለ ትብብራቸሁ እናመሰግናለን