የናይጄሪያው ስቴፈን ኬሺ በተጫዋችነትና በአሠልጣኝነት የአፍሪካ ዋንጫ በማግኘት ሁለተኛው ሰው ሆነ

February 11, 2013

(ከአሰግድ ተስፋዬ) የ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ባለቤት የሆነችው የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ስቴፈን ኬሺ በተጫዋችነትና በአሠልጣኝነት ዋንጫ በማንሳት ከአህጉሪቱ ሁለተኛው ሰው መሆን ችሏል። አሠልጣኙ ከእዚህ በተጨማሪም እ.ኤ.አ ከ1992 ወዲህ የአፍሪካ ዋንጫን ያነሳ የመጀመሪያው አፍሪካዊ አሠልጣኝም ሆኗል።

አሠልጣኝ ስቴፈን ኬሺ በ1994 በተደረገው የአፍሪካ ዋንጫ አረንጓዴ ንስሮቹን በአምበልነት በመምራት ለድል ማብቃት ችሏል። አሠልጣኙ ለናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን በተጫዋችነት በአምስት የአፍሪካ ዋንጫዎች ተጫውቷል።

የናይጄሪያን ብሔራዊ ቡድን ለሦስተኛ ጊዜ በአሰልጣኝነት እየመራ አገሩን ለሦስተኛ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ ባለቤት እንድትሆን ማስቻሉ እንደ ታሪካዊ ግጥምጥሞሽ ተወስዶለታል። በእዚህ ድሉ በተጫዋችነትና በአሠልጣኝነት ዋንጫ በማንሳት የግብጻዊውን ሞሐመድ ኤል ጎሐሪን ክብረ ወሰን ተጋርቷል።

ግብጻዊው ሞሐመድ ኤል ጎሐሪ በፈርዖኖቹ ተጫዋችነት እ.ኤ.አ በ1959 የአፍሪካ ዋንጫን ለአገሩ ያስገኘ ሲሆን፤ በአሠልጣኝነት ደግሞ በ1998 ዋንጫውን አንስቷል።

ስቴፈን ኬሺ በተጫዋችነትና በአሠልጣኝነት ዋንጫ በማንሳት ከአህጉሪቱ ሁለተኛው ሰው መሆን ከመቻሉም በተጨማሪ ከ21ዓመታት በኋላ የአህጉሪቱን ዋንጫ ያነሳ የመጀመሪያው አፍሪካዊ አሠልጣኝም ሆኗል። እ.ኤ.አ በ1992 ለመጨረሻ ጊዜ ዋንጫውን ያስገኙት አፍሪካዊ አሠልጣኝ የኮትዲቯር ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ይኦ ማርሻል ነበሩ።

ከትናንት በስቲያ በተደረገው የ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ናይጄሪያ በታሪኳ ለሦስተኛ ጊዜ ዋንጫ ለማንሳት የቻለችው የፍጻሜ ተፋላሚዋን ቡርኪና ፋሶን አንድ ለዜሮ በማሸነፍ ነው ። ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ከዋሊያዎቹ ጋር በምድብ ሦስት ተደልድለው የነበረ ሲሆን ፤ በምድብ ማጣሪያው ባደረጉት ጨዋታ አንድ ለአንድ በሆነ አቻ ውጤት መለያየታቸው ይታወሳል።

ለአረንጓዴ ንስሮቹ ለሦስተኛ ጊዜ ዋንጫ ያስገኘችውን የማሸነፊያዋን ብቸኛ ግብ ያስቆጠረው ሳንዴይ ምባ የተባለው ተጫዋች ሲሆን፤ ግቧም የተገኘችው የመጀመሪያው የጨዋታ ከፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ አምስት ደቂቃዎች ሲቀሩት ነው።

በጨዋታው ናይጄሪያዎች በተጋጣሚያቸው ቡርኪና ፋሶ ላይ ፍጹም የበላይነት የነበራቸው ከመሆኑ አንጻር ማሸነፍ ይገባቸዋል ። ቡርኪና ፋሶዎች በአንጻሩ በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ባገኙት የፍጻሜ ተፋላሚነት ጨዋታ ላይ እጅጉን ተዳክመው ታይተዋል።

ቡርኪና ፋሶዎች 29ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ማሸነፍ ባይችሉም ከእዚህ ቀደም በሻምፒዮናው የነበራቸውን ውጤት አልባ ተሳትፎ እጅጉን አሻሽለውታል። «ቡርኪናቤ» በሚል ቅጽል ስም የሚጠሩት ቡርኪና ፋሶዎች ከእዚህ ቀደም በነበራቸው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ከሜዳቸው ውጪ ካደረጓቸው ጨዋታዎች አንዱንም አሸንፈው አያውቁም። ሆኖም በአሰልጣኝ ፖል ፑት እየተመሩ በደቡብ አፍሪካው ሻምፒዮና የዋንጫ ተፋላሚ መሆን መቻላቸው አስደናቂ ውጤት ነው።

በተጫዋችነትና በአሠልጣኝነት ዋንጫ በማንሳት ከአህጉሪቱ ሁለተኛው ሰው መሆን የቻለው ስቴፈን ኬሺ የአፍሪካ ዋንጫ ከመጀመሩ በፊት የተጫዋቾች ምርጫን በተመለከተ ብዙ ትችቶች የቀረቡበት ቢሆንም ዋንጫውን በማንሳት ምርጫው ትክክለኛ መሆኑን ማስመስከር ችሏል ።

የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን በሻምፒዮናው ከጊዜ ወደ ጊዜ ምርጥ ብቃቱን እያሳየ መጥቶ ለዋንጫው ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷት የነበረችውን ኮትዲቯርን ካሸነፈ በኋላ «ዋንጫውን ይወስዳል» የሚለውን የበርካታ ተንታኞችን ግምት እውን አድርጓል ።

እ.ኤ.አ 2000በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ በመለያ ምት በካሜሩን ከተሸነፈ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለፍጻሜ የደረሰው የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ከጨዋታው መጀመሪያ አንስቶ በአጨዋወቱ ሙሉ የበላይነት አሳይቷል።

በጨዋታው ከተሰለፉት ተጫዋቾች መካከል የቼልሲው ቪክቶር ሞሰስ በሻምፒዮናው ከኔልስፕሬይት ውጪ ለመጀመሪያ ጊዜ በሌላ ሜዳ የተጫወቱትን የቡርኪና ፋሶን ተከላካዮች በተደጋጋሚ ከመፈተኑም በላይ እንዳይረጋጉ አድርጓቸዋል። የአጥቂ መስመር ተሰላፊዎቻቸውም ቢሆኑ ያን ያህል ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል ።

ቡርኪና ፋሶዎች በአፍሪካ ዋንጫ ከ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በፊት ያስመዘገቡት ምርጥ የሚባለው ውጤታቸው እ.ኤ.አ በ1998 አራተኛ ደረጃ ይዘው ያጠናቀቁበት ውድድር ሲሆን ፤ ናይጄሪያዎች በበኩላቸው እ.ኤ.አ 1980ውና በ1994 ድላቸው ላይ ሦስተኛ ድል አስመዝግ በዋል።

ከጨዋታው ፍጻሜ በኋላ አስተያየቱን የሰጠው የናይጄሪያው አሠልጣኝ ስቴፈን ኬሺ « ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት አሠልጣኝ ሆኜ ስሾም ትልቁ ህልሜ የነበረው ሁሉንም ናይጄሪያውያንን ማስደሰትና ጠንካራ ቡድን መገንባት ነበር። ጠንካራ ቡድን የመገንባቱ ሂደት ባይጠናቀቅም ጀምረነ ዋል። ዋንጫ በማግኘታችን ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል። በጨዋታው መጠናቀቂያ አምስት ደቂቃዎች ላይ ምን አስብክ ? ብላችሁ ብትጠይቁኝ በብራዚሉ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ አፍሪካን መወከል ለናይጄሪያ ምን ያህል ክብር እንዳለው አስብ እንደነበር እነግራችኋለሁ » ብሏል።

የቡርኪና ፋሶው አሠልጣኝ ፖል ፑት በበኩላቸው «በመጀመሪያው አጋማሽ ለተጋጣ ሚያችን ከፍተኛ ክብር ሰጥተናል» ካሉ በኋላ፤ በሁለተኛው አጋማሽ የሚችሉትን ሁሉ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

አሠልጣኙ እንደተናገሩት፤ ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎችን እያንዳንዳቸው ለ120 ደቂቃዎች መጫወታቸው ተጫዋቾቻቸው እንዲዳከሙ አድርጓል። ይህም ቢሆን ለሽንፈታቸው «መንስኤ ነው» ብለው አይወስዱትም።

በተያያዘ ዜና የናይጄሪያው አሠልጣኝ ስቴፈን ኬሺ ለአገራቸው ዋንጫ ያስገኙ ተጫዋቾችን አሞግሷል። አሠልጣኙ «ተጫዋቾቼ በሻምፒዮናው ባሳዩት ምርጥ ብቃት ኮርቻለሁ» ብሏል።

«ተጫዋቾቼ በጨዋታው ላይ ብቻ ከማተኮራቸውም በላይ ጥሩ ተጫውተዋል። ምርጥ ብቃት እንዳላቸውም አሳይተዋል » በማለት ተጫዋቾቹን ያሞገሰው አሠልጣኝ ፒተር ኦድሚዊንጊንና ኦባፌሚ ማርቲንስን የመሳሰሉ ታዋቂ ተጫዋቾችን በቡድኑ ባለማካተቱ ከአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን የደረሰበት ትችት ትክክለኛ አለመሆኑን ማሳየታቸውንም አክሏል።

Previous Story

ስለ ታምራት ሞላ ጥላሁን ገሰሰ እና ማህሙድ አህመድ ምን ብለው ነበር?

Next Story

Nigeria won the Africa Cup of Nations for the third time

Go toTop