እንደአጠቃላይ እውነት እርግዝና እጅግ አስቸጋሪና ከባድ ኃላፊነት ነው፡፡ ሰውን ሰው ውጦት ከደምና ከውኃ በልዩ መለኮታዊ ተዓምር በዘጠኝ ወራት ውስጥ አንድ ሰው ወደዚች ምድር ይመጣል፡ ሲመጣ ያለውን አበሣ ግን በተለይ እናት ናት የምታውቀው፡፡
የሚረገዝ ሁሉ አይወለድም፤ የሚወለድም ሁሉ አያድግም፡፡ የሚያድግም ሁሉ አይጠቅምም፡፡ አልሚ እንዳለ ሁሉ ሽሉ ውኃ ሆኖ ቢቀር እንደሚሻል የሚጠቁሙ አቢይንና መሠሎቹን መሠል ሰው መሣይ አጋንንት ይወለዳሉ፡፡ ይህም ትልቅ እርግማን ነው፡፡ ያኔ ምድር ራሷ ትንቀጠቀጣለች፡፡ ግፍ ይበዛባታል፡፡ ሰማያትም ይናወጣሉ፡፡
የኢትዮጵያ ነፃነት በኢትዮጵያ ማሕጸን ከተረገዘ ቆዬ፡ እንዳይወለድ ግን የነፍሰጡርነት ደምቡ፣ የምጥ መከራ ውርጅብኙ በዛና በሚጠበቀው ፍጥነት እናት ሀገራችን ይህን ለዘመናት የተሸከመችውን ጽንስ ልትገላገል አልቻለችም፡፡ እርግጠኛ መሆን የሚቻለን ግን ይወለዳል፡፡ ተስፋ ቆርጠን አንገታችንን ባቀረቀርንበት፣ ዙሪያችንን በድቅድቅ ጨለማ ተከበን በነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ አጣብቂኝ ውስጥ በምንገኝበት የመጨረሻ ቅጽበት ላይ ነፃነታችን ባልታሰበ ሁኔታ ይወለድና እልልታው አፍሪካን አልፎ በመላዋ ዓለም ይናኛል፡፡
ይህ ጽንስ ተንኮለኛ ቢጤ ነው፡፡ አሁን ሁላችንንም አጮልቆ እያዬ ዕብቁን ከምርቱ፣ ፍሬውን ከገለባ፣ ጅቡን ከአንበሣ እያጣራ በመለየት ላይ ነው፡ አሰስ ገሰሱ ሳይለይ የሚወለድ ነፃነት ለሾተላይ እንደሚጋለጥ ታሪክ በሚገባ ያውቃልና የምናውቀውን ዳኛቸው አሰፋ ከማናውቀው አቶ “ሀ” ለመለየት የሚደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል ወደድንም ጠላንም ትንሽ መቀጠሉና ድፍርሱ መጥራቱ አይቀርም፡፡ ብዙ ጉድ’ኮ እየታዘብን ነው፡፡
እንጂ እንደሰው ምኞትና ሃሣብ ቢሆን ኖሮ ነፃነታችን ተወልዶ የዜግነትና ሰብኣዊ መብቶቻችንን ማጣጣም ከጀመርን በትንሹ አንድ ዓመት ተኩል በሆነን ነበር፡ ግን ስለተመኙት ብቻ የሚሆን ነገር የለምና ገና እንቁልልጭ ላይ ነን፡፡ የነፃነት አዋላጆች ዓይነታቸው ብዙ ነው፡፡ የልምድ አዋላጆች አሉ፡፡ የሠለጠኑ አዋላጆች አሉ፡፡ ረጋ ያሉ እንዳሉ ችኩሎችም አሉ፡ ብዙ ክፍያ የሚጠይቁ ራስ ወዳድና ገብጋቦች የመኖራቸውን ያህል የነዚህ ተቃራኒዎችም አሉ፡፡ ሁሉንም የሚለየው ጊዜና ሁኔታ ከትግሥት ጋር ተጣምረው ነው፡፡
ፋኖ አንደኛው የነፃነት አዋላጅ ነው፤ ጥርጥር የለውም፡፡ ግን ይህ የኢትዮጵያ ተስፋ በሚጠበቀው ፍጥነት እንዳይጓዝ ተመረዘ፡ ሊወለድ ከማሕጸን ብቅ ያለን ጽንስ በጃንጥላ እጀታ አንገቱን ይዘው በጣጥሰው ሊያወጡት የሚፈልጉ የውሸት አዋላጆች ሲጠጉ ጽንሱ ብልጥ ሆነና ወደኋላው አፈገፈገ፥ ሚሊዮኖች በጉጉት እንደሚጠብቁት ያውቃልና ተስፋቸውን ማጨለም አልወደደም፡፡ መወለድ ባለበት ሰዓት ግን ይወለዳል፡፡ ከልካይ የለውም ያኔ፡፡ ፋኖ በመሠረቱ ግሩም ኃይል ነው፡፡ ግሩም ነገር ደግሞ በውስጡም በውጪም የሚፈልቅበት አጥፊ ጠላት ብዙ ነው፡፡ እናም ይህ ኃይል ያልተገራ የግል ፍላጎት ባሸነፋቸውና ከጠላት ጎራ በሠረጉ ሆዳሞች ክፉኛ እየተፈተነ ይገኛል፡ ጊዜ መስትዋት ነውና ተስፋ የጣልንባቸው ብዙዎች እየወደቁ አዳዲሶች እየተነሱ ትግሉ በግልጽም በኅቡዕም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በቅርቡም ዕልባቱን ያገኛል፡፡ ይህን ማንም ሊያስተባብለው የማይችል እውነት ነው፡፡ ግን ታዲያ ቆሞ ያለ የሚመስለው ይጠንቀቅ፡፡ መጽሐፉ ነው የሚለው፡፡ ጊዜው የፈተና ነውና፡፡
አማራ ሀብት ንብረት ማፍራቱ እንደቅንጦት ይቆጠርና ከምድረ ገጽ እንዲጠፋ ዓለም አቀፍ ዐዋጅ ታውጆበት ቤቱና ቀየው በድሮንና በታንክ እየታረሰ ባለበት በአሁኑ ወቅት ከዳግማዊ ግራዚያኒ ከአቢይ አህመድ ጎን ተሠልፎ አማራን የሚፈጅ አማራ ማየት ከማስገረም አልፎ የሣጥናኤልን እጅ እርዝማኔ ያሣያል፡፡ በዚያም ላይ በላም አለኝ በሰማይ የሥልጣን ሱስ ተለክፎ የትግል ጓደኞቹን በሥልጣን ይቀሙኛል አባዜ በመለከፍ ገና ከአሁኑ ደብዛቸውን በማጥፋት ሤራና ተንኮል የተጠመደ የፋኖ አመራርም በትግሉ ላይ ያለው አሉታዊ ዳፋ ቀላል አይደለም – ትግሉ አንድ እርምጃ ወደፊት ሲሄድ ሸሩና ተንኮሉ ሁለት እርምጃ ወደኋላ ይመልሰዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ ክስተት በርግጥ አዲስ አይደለም፡፡ ክርስቶስም በ30 አላድ በደቀ መዝሙሩ በይሁዳ አማካይነት ለጠላቶቹ ሊያውም በመሣም ተላልፎ ተሸጧልና፡፡ ስለሆነም ሆዳምነት ብዙም አያስደንቀን፡፡ በጊዜው መንቃትና ተገቢውን ጥንቃቄ ማደረግ ግን መብሰሉ የማይቀረውን ነገር ብዙ ማገዶ እንዳይፈጅ ለማድረግ ይረዳል፡፡ ሥልጣንን መውደድ፣ ገንዘብን ማፍቀር ሰውኛ ባሕርይ ነው፡፡ ግን መቼቶችን መረዳት ሲገባ በሬው ሳይገዛ በረቱን እንደሚከቡት ሌቦች ያለ ሁኔታ መከሰት የለበትም፡፡ ያሣፍራል፡፡ ያስንቃልም፡፡ “የት ይደርሳል የተባለ ጥጃ ሉካንዳ ደጅ ሲልከሰከስ ታዬ” በሚል ተረት የወረደ ስብዕናን ያከናንባልና ታጋዮች ከዚህ ነጥብ አኳያ ጠንቀቅ ቢሉ ጥሩ ነው፡፡ የሚናገሩትንም ይወቁ፡፡ በነፃነት ማግስት ሁሉም ነገር በሽ ነው፡፡ “እኔ እንደገሌ አይደለሁምና ይቺን የአመራር ቦታ ለማንም አላቀምስም” የሚሉት ፈሊጥ የ18ኛውና የ19ኛው ክፍለ ዘመን መታወቂያ እንጂ የ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገለጫ አይደለም፡፡ ባይሆን “ሕዝቡ በቀጥተኛ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሚመርጠውን እቀበላለሁ፤ ምርጫውን ለሕዝቡ እንተው…” ተብሎ በገደምዳሜም ይታለፋል፡፡ አይ! ምነው ሸዋ!! አሁንስ በዛ፡፡ አቢይን ለምን ጠላነው ታዲያ? መለስን ለምን ጠላነው? የደርጉን መንጌን ለምን ፊት ነሳነው? ከመንጌ በቀር ሌሎቹ ከዘረኝነታቸው በተጨማሪ የለዬላቸው አምባገነኖች ስለሆኑ አይደለምን? እናሳ – ብዔል ዘቡልን በብዔል ዘቡል ለመተካት ይሆን ትግላችን?
ፋኖ ራሱን ያጥራ፡፡ በቶሎም ይስተካከል፡፡ ገና ላልተጨበጠች አንዲት ወንበር ሲባል አዳሜ በጫካ ውስጥ አይራኮት፤ እርስ በርስም አይባላ፡፡ እውነቱን ለመናገር ለሥልጣን ፍለጋ ብሎ ጫካ የወረደ ካለ በፊቱኑ ባይወለድ ይሻለው ነበር፡፡ በዘምቦ ተባርቆ ለሚገኝ ሥልጣን ሲጃጃል ሕዝብ እያለቀ ነው፡፡ “በጊዜ የጮኸ ጅብ አያሣድረኝም” የተባለው እውነት ነው፡፡ ፋኖ የተለያዬ ግላዊ ፍላጎቶች ባሏቸው የጎጥ አመራሮች ተቧድኖ ሺህ ዓመት ቢታገል – በአቢይ አባባል – እውነት ነው የትም አይደርስም፡ በዚያ መልክ በተናጠል መጓዙ ለድል ካለማብቃቱም በተጓዳኝ አገዛዙ በፋኖ በሚደርስበት ያልተማከለ ጥቃት እየተበሳጨ ሕዝቡ ላይ የሚወስደው ዘግናኝ እርምጃ ሕዝቡን እያስቆጣ ከፋኖ ሊለየው እንደሚችል ማሰብ ይገባል፡፡ እንደውነቱ ከሆነ አራት ክፍለ ሀገር ይቅርና አንዱ ክፍለ ሀገር ሸዋ ብቻ ቢተባበርና አንድ ቢሆን ዳግማዊ ወያኔ ኦነግ/ኦህዲድን በጥቂት ሣምንታት ውስጥ ማስወገድ በቻለ ነበር፡፡ ከተሜው አሰፍስፎ የሚጠብቀው ፋኖን ነው፡፡ ፋኖ ደብረ ብርሃንንና ጎሃ ጽዮንን ቢያልፍ ኦነግ/ኦህዲድ በአዲስ አበባ ሕዝብ ጩኸት ብቻ በሽሽት ማዳጋስካር ሊደርስ ይችላል፡፡ ግን የምናወራርደው ሂሣብ አላልቅ አለና ነገሩ ሁሉ የእምቧይ ካብ እየሆነ መቀጠላችን ቢያንስ ለተወሰነ ጊዜ ግድ መሆኑ አልቀረም፡፡ ደግነቱ ይህም ታሪክ ይሆናል፡፡ ምን ታሪክ ያልሆነ አለ
በመጨረሻም ደብተራዎችና ካህናት፣ መጣፍ ገላጮችና ሞራ አንባቢዎች፣ ጠንቋዮችና እናቶች በተለይ እባካችሁን እረፉ፡፡ “ቀጣዩ ንጉሥ አንተ ነህ” እያላችሁ ለሚቀርቧችሁ ታጋዮችና አታጋዮች ሁሉ የተስፋ ዳቦ ስለምታስገምጧቸው ጫካው ሁሉ በነገሥታትና በጠ/ሚንስትሮች ተሞላና የአዛዥና ታዛዥ የዕዝ ሰንሰለት ተበጣጥሶ ክፉኛ ተቸገርን፡፡ ሰው ደሞ ሞኝ ነው፤ የሚነገረውን ሁሉ በቀላሉ ያምናል፡፡ አምኖም ለዚያ የጅሎች ምኞት ስኬት ሲል የማይጠነስሰው ሤራና ተንኮል የለም – ለዚህ አቢይን በምሣሌነት ማየት በቂ ነው – የእሱ እናት ንግርትስ እውን ሆኖ ፍዳችንን እየበላን ነው፤ የሌሎችን ቅዠት ግን አስቁሙልን – ይብቃን፡፡ አንዳንዴ ሳስበው የፖለቲከኞቻችን የመገዳደል መሠረት ይሄ የንግርት ጣጣ ይመስለኛል – ያልተጨበጠ ባዶ ተስፋ፡፡ ሀገርን ለመምራት ዕውቀትንና ችሎታን፣ ትምህርትንና የሀገርና የወገን ፍቅርን፣ የማስተዳደር ልምድንና ጥበብን ተላበሱ እንጂ በማይጨበጥ ትንቢትና በሥልጣን ፍቅር ታውራችሁ አገር አታፍርሱ፤ ሕዝብንም አታስለቅሱ፡፡ እንደኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ብዙ የሚያናግር መቼም የለም፡፡ አገርን በትክክል ማስተዳደር የማያቅተው ፈሪው ምሁር የሚስቱ ኩሽና ውስጥ ተደብቆ ምድረ ማይም ያለቆንጣጭ ያለገልማጭ አራት ኪሎን እየተቆጣጠረ እንደማሽን በሚቆጥራቸው ቅን ታዛዥ ወታደሮቹ ፈጀነ’ኮ – እነዚህ ማሽን ወታደሮች ደግሞ ግደሉ ሲባሉ “ለምን?” ሳይሆን “ስንት?” ብለው ነው የሚጠይቁ፡፡ ምን ይዋጠን? ሠላም ሁኑልኝ ለማንኛውም፡፡