የቀለም አብዮት – አሁንገና ዓለማየሁ

March 3, 2025
የቀለም አብዮት ምንድነው ቢሏችሁ
ጆርጂያ አዘርባጃን ዩክሬን ትላላችሁ?
ወይስ ነጭ ዓለምን በኖራ ሸፍኖ
ያፍሪካን ሥጋ ደም በሞራ አፍኖ
በነበረበቱ በጨለማው ዘመን
በተገመተበት ሰው በንብረት ተመን
የኢትዮጵያ ጀግና ቀለሙን በጥብጦ
ነጩን የብራና ገጽ በጦሩ ጫፍ ገልጦ
በጥቁር ሲጽፈው ታሪክን ገልብጦ
ታሪክን ገልብጦ ሲያኖር አዲስ ርዕዮት
ያ ነው ትላላችሁ የቀለም አብዮት?
ነው እንጂ!
ጥቁር ሰው ምኒልክ አድዋ ተራሮች ላይ
የነጭን ዝርያ በሾተል ሲያበራይ
ጥቁር በነጭ ላይ ታላቅ ድል ሲመታ
የደወለው ደወል የጮኸው እምቢልታ
የነጻነት ድምጸት በዓለም ዙሪያ ሁሉ እስረኛን ቀስቅሶ
ሰብሮ እንዲወጣ ጨቋኙን ደምስሶ
በቀለም ጭቆና የታፈነን ሁሉ
ከየታጎረበት ቀስቅሶ ደወሉ
ታግሎ እንዲያሸንፍ አበርቺ የሆነው
የቀለም አብዮት የአድዋው ጦርነት ነው!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

እንደ ኦሮሙማ መንጋ እሽቅንድር ያደረገው የለም!

Go toTop