የካቲት 16 ቀን2015 ዓም(23-02-2023)
የዛሬ 49 ዓመት ነው በዬካቲት 15 ቀን በአገራችን ተቀጣጥሎ የነበረውን ሕዝባዊ እንቅስቃሴ የወታደር ክፍሉ በራሱ ጥያቄ ብቻ (Camp Issue)ማተኮሩን ትቶ ሕዝባዊ ትግሉን እንዲቀላቀል በነበርኩበት በምድር ጦር አዬር ክፍል(Army Aviation) የሥራ ምድብ አብረውኝ ከነበሩት አባላት ውስጥ በጣም የሚቀርቡኝን አግባብቼ ይድረስ ለጦር ሃይሎች ለፖሊስ ሠራዊትና ለብሔራዊ ጦር በሚል እርእስ ጽሑፉ በማዘጋጀት በሚስጢር በዬጦር ሰፈሩ እንዲሰራጭ የተደረገው።ስለስርጭቱና ዝግጅቱ በዝርዝር ወደፊት ሙሉ ታሪኩን በመጽሓፍ መልክ ለማቅረብ ስላሰብኩኝ ለጊዜው በመቆጠብ የነበረው ሁኔታ አሁን ካለው ሁኔታ ጋር እንዴት እንደሚመሳሰልና እንደሚለያይ፣የቀድሞው ወታደር ምን እንደነበረና ከአሁኑ ወታደር ጋር ያለው ምስስልም ሆነ ልዩነቱ ምን እንደሆነ በማንሳት ላልነበረው ትውልድ ቅንጣቢ ታሪክ በማቅረብ እራሱን ፈትሾ የሚጠበቅበትን ግዳጅና የታሪክ አደራ ተገንዝቦ እንደቀድሞ አባቶቹ ሰልፉን እንዲያስተካክል ለማሳሰብ ይህንን አጭር ጽሑፍ ለማቅረብ ሁኔታው አስገድዶኛል።
ዘመናዊ የአገር መከላከያ ባልነበረበት ዘመን ዜጋ ስለአገሩ አንድነት፣ ክብርና ልዑላዊነት ሁኔታውና አቅሙ በፈቀደለት መጠን የድርሻውን ተወጥቷል።የአገር አንድነት ጥያቄና አደጋ ውስጥ በገባበት ወቅት እርስ በርሳቸው በከባቢ ሥልጣን ይዋጉና ይጨቃጨቁ የነበሩት መሳፍንቶች የውጭ ጠላት በመጣባቸው ጊዜ ሁሉንም ነገር ወደጎን አድርገው ያሰባሰቡትን ጭፍራ ፣ጋሻና ጦር፣ሰይፍና ጎራዴ የታጠቀ ተዋጊ እየመሩ ሃይላቸውን አስተባብረው በመነሳት የረጅም ዘመን ታሪክ ባለቤት የሆነችውን አገራቸውን ከመጣው ወራሪ ሃይል አድነው ለእኛ አስረክበዋል።ጌዜው እዬተለወጠ ሲመጣ የክልል መሳፍንት አገዛዝ ተደምስሶ፣በአንድ መንግሥታዊ አወቃቀር ሲተካ ሕዝባው ጦሩም በዘመናዊ አደረጃጀት የውትድርና ተቋም ለመያዝ በቃ።
በዘመናዊው የውትድርና ተቋም የሚሰማራው ዜጋ እንደ ቀድሞ አባቶቹ ህይወቱን ገብሮ የአገርን ክብርና ልዑላዊነት ለማስከበር፣ዳርድንበሩን ከውጭ ወራሪ ሃይል ለመከላከል፣ የአገሩን ሰንደቅ ዓላማ ጨብጦ ቃልኪዳን በመግባት በራሱ ፈቃድና ፍላጎት እንዲሁም ምርጫ በመከላከያ ተቋም ውስጥ የሚገባ ፣ከሕዝቡ አብራክ የወጣ አገር ወዳድ ዜጋ ነው።በመከላከያ ተቋም ውስጥ ለመግባት የሚጠዬቀው የትምህርት ደረጃ፣የሰውነት አቋምና የጤና መሟላት ብቻ ነው። ጎሳ፣ቋንቋና እምነት ለሙያው የሚጠዬቁበት ቅድመ ሁኔታዎች አይደሉም። ቦታም የላቸውም።ወታደር በዜግነቱ እንጂ በጎሳ ማንነቱ አይመለመልም።ከልዮ ልዩ ጎሳዎች የተወለዱ ዕድሜና ችሎታቸው የፈቀደላቸው ሁሉ በራሳቸው ምርጫ ወታደር ይሆናሉ እንጂ ተገደው አይገቡም።የጎሳ ቋንቋቸውንና ማንነታቸውን ይዘው ግን ለአንድ አገራዊ ዜግነታቸው ተገዥ በመሆን ብሔራዊ ቋንቋ እዬተናገሩ የሚግባቡ፣ ለአንድ ዓላማ የተሰለፉ፣ኑሯቸውም ሞታቸውም የማይለያያቸው ቤተሰቦች ናቸው።
ይህ ዓለም አቀፋዊ ሕግን የተከተለ ብሔራዊ የውትድርና ተቋም አመሠራረት ሲሆን በኢትዮጵያም በዘመነ መሳፍንት ጊዜ የነበረው የጭፍራ ተዋጊ ከስርዓቱ ጋር ተወግዶ በአንድ ስርወመንግሥት ስር የሚታዘዝ ወታደራዊ ተቋም ሊገነባ ችሏል። ወታደር የአገርና የሕዝብ መከታና ጠበቃ እንጂ የአንድ የተወሰነ ቡድን ወይም በሚመጣና በሚሄድ የመንግሥት መሪዎች ፍላጎትና ጥቅም የሚሽከረከር የግል አሽከር አይደለም።ከብሔራዊ ግዳጁ ጎን ለጎን ፣ለእናት ለአባቱ፣ለእህት ለወንድሙ ፣ግብር እዬከፈለ ደመወዙን ለሚችለው ሕዝብ፣ ደህንነትና መብት ይቆማል።የሕዝቡ ችግር ችግሩ ነው።ሕዝብ ከተቸገረ፣ሰላም ከተናጋ የሱም ሰላምና ኑሮ ይናጋል።የሚኖረው ከህብረተሰቡ ጋር እንጂ ለብቻው በተነጠለ ደሴት ውስጥ ስላልሆነ ጉዳቱንም ፣ሃዘኑንም ደስታውንም ይካፈላል። ይህ የጤነኛና የትክክለኛ ወታደር መመሪያ ሕግ ነው።ከዚህ ውጭ ሌላ ተግባር ውስጥ የሚገባ፣ ለሆዱ የሚገዛ፣ለተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል ጥቅምና ሥልጣን የሚቆም በተለይም በጎሳና በሃይማኖት ረድፍ ውስጥ ተሰልፎ አንዱን ደግፎ ሌላውን የሚያጠቃ ከሆነ ወታደር ሳይሆን ፣ ዃላቀር የግለሰቦች አሽከር፣የታጠቀ አሸባሪና ዘራፊ ነው። በሕዝብ ላይ ግፍ የሚሠራ፣ለህሊናው ያላደረ ጨካኝ ፣አስፈሪ፣የተጠላና የተናቀ ታሪክ ሲወቅሰው የሚኖር ፍጡር ይሆናል።
ውትድርና ከጦርነትና ከውጊያ ችሎታና ጥበብ(Military science) ጋር ከተያያዙት አሰላለፎች ባሻገር የተለያዩ እውቀቶችንና ሙያዎችን የሚቀስሙበት ተቋም ነው።የሕግ ጠበቃ፣መሃንዲስነት፣ሃኪምነት፣—ወዘተ ሙያን ያገኙበታል።በሰላምም ሆነ በጦርነት ጊዜ፣ጡረታም ወጥተው ሆነ ሳይወጡ ለሕዝቡ የሚያበረክቱት አገልግሎት ብዙ ነው።እንደ አገሩ እድገትና ሥልጣኔ የወታደር ሙያም እያደገ ይሄዳል፤በምርምርና በፍልስፍና የአዳዲስ ግኝቶች ባለቤት የሚሆኑበት ዘርፍ ነው። የጠፈር ጉዞና የዘመናዊ መገናኛ ጥበብ በአብዛኛው የተጠነሰሰውና የተጀመረው ከወታደራዊ ተቋም እንደሆነ አይካድም።
ከሃምሳ ዓመት በፊት በአገራችን በኢትዮጵያ የነበረው የወታደር ተቋም ለብዙዎች የሙያ ትምህርት ቤት ሆኖ አገልግሏል።ብዙ የሕክምና ዶከሮችና ነርሶችን፣የሕግ ጠበቃዎችንና ዳኞችን፣ መሃንዲሶችን የሲቪል አቪዬሽን ባለሟሎችን፣አብራሪዎችን፣ቴክኒሻኖችን አፍርቷል።
ይህንን ታሳቢ በማድረግ ነበር እኔና ጓደኞቼም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታችንን ለማጠናቀቅ ጥቂት ወራት እንደቀረን፣ ለመልቀቂያ ፈተና (ማትሪክ)ተመዝግበን ባለንበት በዬካቲት ወር 1963 ዓም የምድር ጦር አዬር ክፍል (Army Aviation) ያዘጋጀውን የመግቢያ ፈተና አልፈን ለመቀላቀል የቻልነው።ከአንድ ትምህርት ቤት መሆናችን ብቻም ሳይሆን በዬዓመቱ በአንድ ክፍል ውስጥ የነበርን በመሆናችን ይበልጥ ለመግባባትና ለመተማመን ዕድል ሰጥቶናል።
በመድሃኔ ዓለም ት/ቤት ባሳለፍናቸው ዓመታት በተማሪው ትግል ውስጥ የተሳተፍን መሆናችን በገባንበት ወታደራዊ ክፍል የባህል ለውጥ ለማምጣት ግንባር ቀደም ሚና ለመጫወት አብቅቶናል።ወታደር ያሉትን ተቀብሎ ፣ስነሥርዓት በሚል ሽፋን ለምን ብሎ ሳይጠይቅ ግዳጁን መፈጸም ያለበት ታዛዥ ነው የሚለውን የተለመደ መመሪያ የተዳፈርንና በወታደር ክፍል ውስጥ ሆኖ የማያውቅ የአድማ እምቢባይነትን፣በአንeነት መቆምን ያሳዬነው ገና በገባን በ15ኛው ቀን ላይ ነበር።ዝርዝሩን አልፈዋለሁ።ይህም በአንጋፋዎቹ የተጠላን በብዙዎቹ ግን የተወደድን አድርጎናል። በዕድሜ አነስተኞች ብንሆንም በትምህርት ደረጃችን ካለፉት ቅጥሮች የተሻልን ነበርን።አስራ አንደኛ ክፍል ሆነን የጥላሁን ግዛው ሞት የነበረውን የተማሪ ትግል ይበልጥ መጠናከር ብቻም ሳይሆን በተማሪው ላይ የፖለቲካ አስተሳሰቡን አሳድጎታል።ያን መንፈስ ይዘን ነው ከወታደሩ ዓለም የተቀላቀልነው።
ይህች ባቄላ ካደረች አትቆረጠምም ተባለና ለቅጣት ወደፍቼ ለሦስት ወራት ተልከን ነበር።ምንም እንኳን ከገባንበት የሥራ ዘርፍ አንጻር የማይመለከተን ቢሆንም በፍቼ ማሰልጠኛ ካምፕ የእግረኛ ጦሩን ዲሲፕሊንና የውጊያ ስልት ለመማር ችለናል።ይህም በመሥሪያ ቤቱ የመጀመሪያዎቹ አድርጎናል።
የአገራችን የፖለቲካ፣ የኤኮኖሚና ማህበራዊ ቀውስ ይበልጥ እዬጎላ፣የዴሞክራሲ ጥያቄ እያስተጋባ ሲመጣ አገራችንን ሕዝባዊ ተቃውሞ አጥለቀለቃት።የዓለም አቀፉ የነዳጅ ዋጋ ያስከተለው የኑሮ ውድነት፣ድርቅና በተያያዥ ምክንያቶች የብዙ ሰው ህይወት ሲጠፋ፣ከነበረበት ቦታ ተፈናቅሎ በዬከተማው ሲሰደድ፣የኤርትራ ተገንጣዮች እዬተጠናከሩ መምጣትና ውጥረት መጨመሩ ፣የሁሉም ማህበረሰብ ኑሮ መናጋት፣የወታደሩ በዬፊናው የደመወዝና የስንቅና ትጥቅ ጥያቄ፣የመምህራኑና የሠራተኛው የደመወዝና የመብት ጥያቄ፣የተማሪው መሬት ላራሹና ሕዝባዊ መንግሥት ጥያቄ፣የታክሲ ነጁ፣የሙስሊሙ፣የቀሳውስቱ፣ምኑ ቅጡ ሁሉም በዬፊናው ብሶቱን በማሰማት አደባባይ ወጥቶ በአቶ አክሊሉ ሃብተወልድ ይመራ የነበረውን መንግሥት ወጥሮ ያዘው። በዚህ ጊዜ ነው ወታደሩ ከራሱ ጥያቄ ወጥቶ የማህበረሰቡን ጥያቄ ይዞ መቆም እንዳለበት በመረዳት የትግሉ አካል ለማድረግ የጥሪው ደብዳቤ የተሰራጨው።
በመጀመሪያ በተበታተነ መልኩ ለውስጣዊ የካምፕ ጥያቄ የሚያነሳውን የወታደር ክፍል ለምሳሌም ለንጹህ ውሃና ምግብ(እህል) አቅርቦት፣ለልጆች ትምህርት ቤት፣ጥያቄ አንስቶ አለቃዎቹን ላገተው ለ4ኛ ክ/ጦር የመድፈኛ ሻለቃ ለነገሌ ጦር የበታች ሹማምንት ድጋፋችንን ውስጥ ለውስጥ እዬላክን በተመሳሳይም ኤርትራ ውስጥ በጦር ሜዳ ላይ ለተሰማራው ለሁለተኛ ክ/ጦር የደሞዝ፣የትጥቅና ስንቅ፣እንዲሁም የዓመት እረፍት ጥያቄ ተመሳሳይ ድጋፍና አብሮነታችንን እዬገለጽን የትግል አጋርነት ለመመስረት ቻልን።ደብረዘይትም ይንቀሳቀስ ከነበረው አዬር ሃይል ጋርም እንዲሁ ውስጥ ውስጡን የትግል አጋርነት መሰረትን። የእኛ ክፍል የምድርጦር አዬር ክፍል ምንም እንኳን የአባላቱ ቁጥር ከአዛዡ እስከታችኛው ድረስ ያለው ከ150 ባይበልጥም ፣በቀላሉ የሚግባባ፣የበታችና የበላይ ሳይባል፣በአንድ ገበታ የበላ፣በአንድ ክበብ የተዝናና አብዛኛው ወጣት ፣የማዕረግና የደሞዝ ልዩነት ቢኖርም ሁሉም ወደፊት የሚደርስበት መሆኑን አውቆ፣ የቤተሰብ ግንኙነት የነበረው ነበር።ሁለት የሥራ ዘርፎ ሲኖሩት በአብራሪነት በዕድሜና በሹመት ገፋ ያሉት ከአዬር ሃይሉ፣ወጣቶቹ ደግሞ ከሐረር አካዳሚ ተመርጠው መጥተው የሰለጠኑ ናቸው። ከዬትምህርት ቤቱ ደግሞ ለቴክኒሻንነት የተመለመሉ ነበሩ።እኔና ጓደኞቼ ከዚያ ውስጥ ነን። በበራሪና በቴክኒሻኑ መካከል መከባበርና መተባበር እንጂ መናናቅ አልነበረም። ከቴክኒሻኑም ውስጥ ለበረራ የሚሰለጥኑ ስለነበሩ ወሳኙ የትምህርት ብቃቱ ብቻ ነበር።
ከሁሉም ክፈለ ጦሮች ጋር በቀላሉ የሚገናኝና የአዬር ፣የሎጅስቲክስና የአስቸዃይ(ኢመርጀንሲ) አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ በሁሉም የእምድር ጦር ክፍሎች ዘንድ የተወደደና የተከበረ ክፍል ነበር፣ከአዬር ሃይሉ ጋር ባለው የሙያ ምስስልና ስልጠናም ከአለባበስ ጀምሮ ተመሳሳይ ነው። ሲጀመር አቪዬሽኑ የተወለደው በአዬር ሃይሉ ማህጸን ውስጥ በደብረዘይት ከተማ ነበር።ከዚያ በዃላ ነው ወደ ዱሮው አውሮፕላን ማረፊያ የአሁኑ ጦር ሃይሎች ግቢ የተዘዋወረው።ይህም የዬካቲቱ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ሲጀመር በቅርበት ለመከታተልና ከሚንቀሳቀሱትም ጋር በመገናኘትና በመወያዬት የድጋፍ ጽሑፎች እያዘጋጀን በሄሊኮፕተር ለመርጨት መልካም አጋጣሚ ሆኖልናል። ለመጀመሪያው ለዬካቲቱ ወታደራዊ እንቅስቃሴ የዕዝ ማእከሉ የአርሚ አቪዬሽን ዋና መምሪያ ነበር።ከዚህ መምሪያ ነው በአዲስ አበባ የተሰማራዊ የአራተኛና የአምስተኛ ክፍለጦር ትእዛዝና ግዳጅ ይቀበል የነበረው።
በየካቲቱ ወታደራዊ እንቅስቃሴ በክብር ዘበኛና በፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ በኩል ምንም አይነት ተሳትፎ አልነበረም።የሚረጩት ወረቀቶችም ከብዙሃኑ እጅ እንዳይገቡ ከፍተኛ ቁጥጥር ከመደረጉም በላይ አዬር ሃይልና የምድር ጦር ንጉሠ ነገሥቱን ከዳ የሚል ወሬ በማናፈስ ለእርስ በርስ ጦርነት ዝግጅትና ቅስቀሳ ይደረግ ነበር።ሁኔታው የ1953 የታህሳሱን መልክ ስለያዘ እንቅስቃሴውን ለማቆምና ለንጉሠ ነገሥቱ ጥያቄያችንን ለማቅረብ ተገደድን። እኔ የእንቅስቃሴው አንዱ መሪና አስተባባሪ ስለነበርኩ፣የፕሮፓጋንዳና የፅሁፉም ሥራ እኔ ላይ ስለወደቀ ለንጉሠ ነገሥቱ ከዚህ በታች ያለውን ደብዳቤና ጥያቄ አዘጋጅቼ፣ሁሉም ደግፎና ተቀብሎት ለጊዜው በጥበቃ ሥር የነበሩትን ጥቂት ባለሥልጣኖች ይዘን ወደ ቤተ መንግሥት አመራን።የደብዳቤው ይዘት ንጉሠነገሥቱን ለመገልበጥ እንዳልሆነ በሚገልጽ መልኩ የክብርዘበኞችን ልብ እንዲማርክ ሆኖ በመዘጋጀቱ በቀጣዩ ጊዜ ላደረግነው እንቅስቃሴ የክብር ዘብ አባላትን ለማካተት እረድቶናል። ነገሩን ላሳጥረውና ደብዳቤውን የሰጠሁት ጓደኛዬ ግርማ ፍስሃ ለንጉስ ሃይለሥላሴ አንብቦ የጥያቄያችን ዝርዝርም ለቤተመንግሥቱ ሊጋባ ለጀነራል አሰፋ ደምሴ ተሰጠ።መልሱን በመከላከያ ሚኒስትሩ በጀነራል አብይ አበበ በኩል ትሰማላችሁ ተባልን።
ለማንኛውም ደብዳቤዎቹ የሚከተሉት ናቸው
እነዚህ ከላይ የሚታዩት ጥያቄዎች እስከአሁን ድረስ መልስ አላገኙም።የበፊቱም ሆነ የአሁኑ ጥያቄ ተመሳሳይ ነው።የዴሞክራሲ ጥያቄ ተነስቶ መልስ ሳይሰጠው ይኽው 50 ዓመት ሊሞላው ነው።ከ50 ዓመት ወዲህ ግን አገር ያልነበሩት አገር ሆነው የዕድገትና የሰላም ምሳሌዎች ሆነዋል፤ለእኛም እርዳታ ለጋሾች ለመሆን በቅተዋል።በኛው ጥፋትና ስህተት መልካም አገር ይዘን የድህነት፣የርሃብ፣የግጭትና የስደት ምልክቶች ሆነናል።ከዚያም አልፎ አገር አፍርሶ ለመበታተን ግብግብ ይዘናል።ዓለምም በትዝብትና በንቀት ዓይኑ ይመለከተናል።
የደብዳቤዎቹ ኮፒዎች ከኔጋር ላለፉት 49 ዓመታት ሲንከራተቱ የኖሩ ሲሆን ወደፊት ለታሪክ በብሔራዊ አርካይቭ ውስጥ የመቀመጥ እድል ይኖራቸዋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።ለጊዜው ግን የፎቶግራፍ ኮፒዎቹን ለአሁኑም ትውልድ በተለይም ለወታደሩ ክፍል ምሳሌና ትምህርት ይሆናል በማለት ከዚህ ጋር አያይዤዋለሁ። የዚህም ጽሑፍ ዋና መልእክቱ ወታደር ማለት ከጎሳና ከሃይማኖት በላይ ማንነት ያለው፣ ከሕዝብ ያልተነጠለ፣ የሕዝብ ጥያቄ ጥያቄው የሆነ፣ለአገር አንድነትና ልዑላዊነት የቆመ፣ መሆኑን ያለፈውን ታሪክ በማቅረብ ለማስገንዘብ ነው።እንደ አለመታደል ሆኖ ግን በአሁኑ ጊዜ በተለይም ላለፉት 32 ዓመታት የአገር መከላከያ የሚባለው ተቋምና ወታደር ብሔራዊ ገጹንና ክብሩን ተገፎ በጎሰኞች የሚሽከረከር ፣የቡድኖች ክብር ዘበኛ በመሆኑ ያገራችን አንድነትና ልዑላዊነት ብቻም ሳይሆን የራሱ የወታደሩ እጣ ፈንታ በአስጊ ሁኔታ ላይ ይገኛል።ወደ ቀልቡ ተመልሶ በብሔር- ብሔረሰብ ስም ሕዝብና አገር የሚያምሱትን፣ቡድኖችና ሥርዓታቸውን አሶግዶ እንዳለፉት አባቶቹ ኢትዮጵያን በማዳን ብሔራዊ ግዳጁን እንዲወጣ ለማሳሰብ ይህንን መልእክት ከነታሪኩ ለማስተላለፍ ያለው ሁኔታ አስገድዶኛል።
በዬካቲት 1966 የቀረቡት ሕዝባዊ የዴሞክራሲ ጥያቄዎች አሁንም አልተመለሱም። በወታደራዊ አምባገነን ሥርዓት ተደፍጥጠው በወያኔ መራሹ ኢሕአዴግም ዘመን ተረግጠው አሁን በሥልጣን ላይ ባለው ኦነጋውያን ስብስብ ተረኛ ቡድንም ይበልጥ ሰብአዊ መብት ሳይቀር እዬተጣሰ መጥቷል።ይህንንም ሲያደርግ በጎሳ ለያይቶ ባሰለፈው ወታደራዊ ክንፍ በመተማመን ነው።
ለአገር ልዑላዊነትና አንድነት ፣ለወገን ክብር እቆማለሁ፣ለታሪኬም አስባለሁ፣በዘመናዊ አስተሳሰብና ፣በእውነተኛ ወታደራዊ ስነምግባር የታነጽኩ ወታደር ነኝ የሚል፣ የእኛን የቀድሞዎቹን ወታደሮች ፈለግ ተከትሎ የአገርን አንድነትና የሕዝብን አብሮነት ለማስቀጠል የሚሻ፣ በጎሳ እይታና ጠባብነት ለያይተው ሊያጫርሱት የሚዳክሩትን ባለሥልጣኖችና የዘረጉትን ሥርዓት ለማሶገድ ከሕዝቡ ጎን እንዲሰለፍ እንደ ዛሬ 49 ዓመቱ የ1966 ዓም የካቲት ጥሪዬ በዘንድሮውም 2015ዓም የካቲት ይህንን ጥሪ አስተላልፋለሁ። እርዕሱንም ይድረስ ለወታደር ከወታደር ያልኩት የሙያ ሰንሰለቴ ያቀራርበኛል፣ለመደማመጥና ለመግባባት በር ይከፍታል በማለት ነው።ከሁሉም በላይ ግን የኢትዮጵያ ወታደርና የመከላከያ ተቋም አሁን ካለበት ዝቃጭና ወራዳ የጎሰኝነት አሰላለፍ ወጥቶ ወደ ነበረበት ቁመናና ክብር እንዲመለስ ካለኝ ጉጉትና ፍላጎት በመነሳት ነው።እንደኛ ጊዜ እንቅፋት የሚሆኑትን አዛዦች በቁጥጥር ስር በማድረግ ለሥርዓቱ አልገዛም ባይነቱን መግለጽ ያለበት፣ለልጅ ልጆቹ የሚያኮራ ታሪክ የሚያወርስበት ጊዜው አሁን ነው።ከሙያ ማህበራትና፣ የማህበረሰብ ክፍሎች፣ከእምነት ተቋማት ጋር በመተባበር ብሔራዊ የትብብር መድረክ በማቋቋም የጋራ አመራር ያለው አካል መፍጠር ለትግሉ መሳካት ዋስትና ነው። የዳግማዊ የካቲትን ታሪክ እንዲደግመው ዛሬም እንደ ትናንቱ ወታደራዊ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ።
ላቀረብናቸው ጥያቄዎች መልስ ማግኘቱ ቀረና አስተባባሪ ናቸው የምንባለውን ሰዎች መቀጣጫ ለማድረግ ሴራ እዬተጎነጎነ መሆኑን ሰማን።ለሁለተኛ ጊዜ ክብር ዘበኛንም በማካተት እንቅስቃሴ ለማድረግ ወስነን ስምሪት ሊጀመር ሲል በውስጣችን ከነበሩት መሃል አንዱ የአዬር ወለድ አባል ምስጢሩን አሾልኮ በመንገሩ አዬር ሃይሉ በአዬር ወለድ ተከበበ፤ሌሎቻችንም ከዬቦታው ተለቅመን ከወታደር እስር ቤት ውስጥ ገባን።ከ150 በላይ ምስክር ቀረበ ተብሎ፣በዬስማችንም ከሊቢያ ገንዘብ ተልኮላቸዋል የሚል የፈጠራ ማስረጃ አዘጋጅተው ከፍተኛ ቅጣት በወታደራዊ ፍርድቤት ሊሰጠን እንደታቀደ ሲሰማ፣ያልታሰሩት ጓደኞቻችን ተዘጋጅተው ጊዜ በመጠባበቅ ላይ ስለነበሩ በተገኘው አጋጣሚ ተንቀሳቅሰው የጦር ሃይሎች ፣የፖሊስ ሠራዊትና ብሔራዊ ጦር አስተባባሪ ኮሚቴን በዃላ ላይ ደርግን መሠረቱ። ለደርግም መፈጠር ምክንያት የሆኑት ዋናዋና ተዋንያኑ ከዚሁ ከምድር ጦር አዬር ክፍል የተገኙት ከአንድ ትምህርት ቤት ከመጣነው መሃል የቅርብ ጓደኞቼ ናቸው።ዝርዝሩ እረጅም ቢሆንም በጥቂቱ የሚከተለውን ይመስላል።
በመጀመሪያው ወታደራዊ እንቅስቃሴ የተነሳ የአድማው መሪዎች ተብለን ከአቪዬሽን እኔ፣ዩሃንስ ወ/ጊዮርጊስ፣ዩሃንስ ወርቅነህ፣ተስፋዬ ተገኝና ጌታቸው ሚደቅሳ፣ከሌሎቹ የጦር ክፍሎች ማለትም ከአዬር ሃይል፣ከአራተኛ ክፍለጦር፣ከክብርዘበኛ ፣ከአዬር ወለድ በአጠቃላይ 21 ሰዎች በልጅ እንዳልካቸው መኮንን በሚመራው መንግሥት እስር ቤት ታስረን ለመቀጣጫ ከባድ ቅጣት ለመቀበል ባለንበት የጦር ፍርድ ቤት ሂደት የቀሩት ጓደኞቻችን ግርማ ፍስሐ፣ዩሃንስ ፍትዊ፣ብዙአዬሁ አምሳሉ እንቅስቃሴውን ውስጥ ለውስጥ ማካሄድ ቀጠሉ።ሻለቃ አጥናፉ አባተን፣ሻለቃ ተፈራ ተ/አብን፣ሻምበል ስምአኒ ሰውነቴን በመገናኘት እኛ የጀመርነውን እንቅስቃሴ ለማስቀጠል ጊዜ ሲጠብቁ በሰኔ 21 ቀን 1966 ዓመ በተፈጠረ ሁኔታ(ወደፊት እገልጸዋለሁ) ንቅናቄውን ጀምረው ከዬክፍለጦሩና ከወታደር ክፍሎቹ 2 ተወካይ በመጥራት የአስተባባሪ ኮሚቴውን በዃላ ላይ ደርግን መሠረቱ ።በኮሚቴው ውስጥ በነበራቸው ግንባር ቀደም ሥራቸው ከአቪዬሽኑ አራት ሰዎች ከሌላው የበለጠ ውክልና ነበራቸው።በመጀመሪያ ላይ የነበሩት ጁኤክማን ግርማ ፍስሃ፤ጁኤክማን ዩሃንስ ፍትዊ፣ ሻምበል ገናናው መንግሥቴና ሲኤክማን ለገሰ ገ/ሥላሴ ነበሩ፣ በነሱ ጥረት እኛም በሰኔ 30 ቀን ከእስር ቤት ለመፈታት በቃን። እንደሌላው ክፍል በሁለት ሰው ብቻ ይወከሉ ተባለና ሻምበል ገናናውና ፣ሲኤክማን ለገሰ ገ/ሥላሴ ወጥተው በዩሃንስ ፍትዊና በተስፋዬ ታከለ ተተኩ። ከዚያ ቀን ጀምሮ የጦር ሃይሎች የፖሊስ ሠራዊትና የብሔራዊ ጦር አስተባባሪ ኮሚቴ የሚለው አደረጃጀት የመለዮ ለባሹ ብቻ መሆን የለበትም የሕዝቡንም ተወካዮች ያቀፈ ሕዝባዊ ኮሚቴ ይሁን የሚል ሃሳብ አንስተን ተወካዮቻችን እንዲያቀርቡ ተደረገ።ግን ተቀባይነት አላገኘም።ከዚያ ጀምሮ እኛም በበኩላችን ንዑስ ደርግ የሚል አቋቁመን ሌላው የጦር ክፍልም እንዲያቋቁም አደረግን። እንቅስቃሴያችንን ከወታደሩ አልፎ ከሲቪል ማህበራት ጋር ማስተሳሰር ጀመርን፣የተለያዩ ጽሑፎች እያወጣን መበተኑን ተያያዝነው።በወታደራዊው አስተባባሪ ኮሚቴና በእኛ መካከል የከረረ ጭቅጭቅና ልዩነት ተፈጠረ።በመጨረሻው መስከረም 2 ቀን ወታደራዊ መንግሥት ሲታወጅ የመጀመሪያ ተቃዋሚዎች ሆነን “ለውጥ ማለት” በሚል እርእስ ጽሑፍ አወጣን።ሕዝባዊ መንግሥት መቋቋም አለበት በሚለው አቋማችን ጸናን።ተወካዮቻችንንም እንደምናስቀር ገለጽን።የመሃንዲስና የክብር ዘበኛም ተመሳሳይ አቋም ወሰዱ።በዚህ ውዝግብ ውስጥ እንዳለን ሳናስበው በመስከረም ወር አጋማሽ ላይ የመሃንዲስና የእኛ ጦር ሰፈር ተከቦ መሪዎች ናቸው የተባሉ ከ10 በላይ የአቪዬሽን አባላት ተለይተው ወደ ክፍተኛ ምርመራ ሲወሰዱ ሌሎቹ ከመቶ በላይ የሚሆኑት በመኪና ተጭኖና በወታደር ታጅቦ ሆለታ ጦር ሰፈር እስር ቤት ለአንድ ወር ታሠሩ። የኮሚቴው ጸሃፊ የነበርኩት እኔና የኮሚቴው አባል የነበረው ሊኤክማን ጌታቸው ሚደቅሳ ሕዝባዊ ድርጅቶችን ለማነጋገር ወጥተን ስለነበር ሳንያዝ ቀረን። በደርግና በተቀዳሚ ሊቀመንበር በነበሩት በሌ/ጀነራል አማን አምዶም ሚካኤልና በነመንግሥቱ ቡድን መካከል የሥልጣን ጭቅጭቅ ተነስቶ የደርግ አባላት እንደ ታህሳሱ 1953 እነጀነራል መንግሥቱ ነዋይ ተስፋ በመቁረጥ መሞታችን ካልቀረ በሚል የመጨረሻ እርምጃ በጀነራል አማንና ባሰሯቸው ለአገራችን ብዙ የደከሙና ውለታ የሠሩትን ባለሥልጣኖች እንዲሁም የወታደር ክፍል ተቃዋሚዎቻቸው ላይ የጭካኔ እርምጃ በመውሰድ በታሪካችን ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ በጠቅላላው ከ60 የማያንሱት ላይ ግድያ ፈጸሙባቸው።ከአቪዬሽን ከታሰሩት ውስጥ አራቱ የአቪዬሽኑ አዛዥ ኮሎኔል ይገዙ ይመኔ፣ሻምበል በላይ ጸጋዬ ፣መቶ አለቃ ተስፋዬ ታከለና ጁኤክማን ዩሃንስ ፍትዊ ሲገደሉ ሌሎቹ ስድስቱ የኮሚቴው አባላት ሻምበል ፍቅሩ ወ/ሥላሴ፣ሊኤክማን ዩሃንስ ወ/ጊዮርጊስ፣ሊኤክማን ዩሃንስ ወርቅነህ፣ሲኤክማን ገበዬሁ ገብሩ፣ሲኤክማን ለገሰ ገ/ሥላሴና ጁኤክማን ብዙአዬሁ አምሳሉ እንዲሁም ተረኛ መኮንን የነበረውና ከበባውን የተቃወመውና ግብግብ የገጠመው ሻምበል ካሳዬ ክፍሌ ለ7 ዓመት በከርቸሌ ከታሰሩ በዃላ ተለቀው ከወታደራዊ ተግባር ተሰናብተው በሌላ መስክ ተሰማርተዋል። አሁን በህይወት የሌሉት ሻምበል ገናናው መንግስቴ በዃላ በሜ/ጀነራልነት ማዕረግ የአቪዬሽኑ አዛዥ ከሆነ በዃላ በ1982 መፈንቅለ መንግሥት ተጠርጥሮ ተረሽኗል።ብዙአዬሁ አምሳሉ ከደርግ በፊት ኢትዮጵያችን ትቅደም በሚል እርእስ ጽሑፍ እንዳዘጋጀ እስር ቤት መጥቶ ሲጠይቀኝ በይዘቱ ተነጋግረንበታል።ከእስር ቤት ከተፈታ በዃላ ከአዬር ሃይሉ ከማስተር ግርማ ዘለቀ ጋር በጎጃም በኩል ለመውጣት ሲሞክሩ የገበሬ ማህበር ሲከባቸው፣እራቸውን በያዙት ሽጉጥ ማጥፋታቸን ሰምቻለሁ።ብዙአዬሁ ከእስር ቤት ከወጣ በዃላ በዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ሶስተኛ ዓመት ተማሪ ነበር።
ካሳዬ ክፍሌ አሜሪካ ወጥቶ ሲኖር ቆይቶ በጤና ምክንያት አርፏል።ሊኤክማን ጌታቸው ሚደቅሳ አብረን ሱዳን ከገባን በዃላ በኢሕአፓ የትጥቅ ትግል ላይ ተሰውቷል ፣ ለገሰ ገ/ ሥላሴ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ አሜሪካ መግባቱን ሰምቻለሁ።ዩሃንስ ወ/ጊዮርጊስ፣ዩሃንስ ወርቅነህ፣ገበዬሁ ገብሩ፣ፍቅሩ ወ/ሰማያት በአገር ቤት ይኖራሉ።
አብረን በልጅ እንዳልካቸው መንግሥት ከታሰርነው መካከል ከአዬር ሃይሉ ማስተር አዬለሃይሌ በጤና ምክንያት ፣ሲቴክ ይገዙ በንቲ ከባሮ ቱምሳ ጋር ተይዞ ሲገደል ፣ሲ ቴክ አበበ አረጋ ደርግን ተጠግቶ በወዝ ሊግ ሴራ ጠነሰሰ ተብሎ ተረሽኗል።ሲቴክ ጌታቸው ገብረዬስና ደጀኔ ደምሴ አሜሪካ አገር ይኖራሉ። ከክብር ዘበኛም መቶ አለቃ ዳዊት ገብሩ መሞቱን ሰምቻለሁ።መቶ አለቃ ከበደ ቀጀላና ፣ሞላ ዘገዬ አገር ውስጥ ይኖራሉ።የሌሎቹን አላውቅም።ከደርግ ጋር ተቀላቅለው የከዱንም አልጠፉም።
በእስር ቤት ያወጣናቸው መዝሙሮች የሚከተሉት ናቸው የሁሉንም ግጥም የጻፍኩት እኔ ስሆን ዜማዎቹን ከዩሃንስ ወ//ጊዮርጊስና ከአበበ አረጋ ጋር በመተባበር አወጣን።
1ኛ ተነሳ ተራመድ
ተነሳ ተራመድ ክንድህን አበርታ፣
ላገር ብልጽግና ለወገን መከታ።
ባስተዳደር ጉድለት እዬተማረረ፣
ስንቱ ኢትዮጵያዊ እንደወጣ ቀረ።
ባላባት ጭሰኛ ማለቱ ለምን ነው፣
ልዩነት የለውም የሰው ልጅ እኩል ነው፣
ሁሉም ባለድርሻ ያገር ባለቤት ነው።
በገዛ ሃገሩ ተብሎ ጭሰኛ፣
መገበር ቢያቅተው ሆነ ስደተኛ።
መብቱን ለማስከበር ቆርጦ በተነሳ፣
ሽፍታ እዬተባለ በዛበት አበሳ።
2ኛ ስማኝ ያገሬ ሰው
ስማኝ ያገሬ ሰው ባንድ ላይ ተነሳ፣
ድር ከተባበረ ይጥላል አንበሳ።
እስላም ወይ ክርስቲያን ሳይባል በሙሉ፣
የጎሳ ልዩነት ሳይኖር በመሃሉ፣
ያገርን ነቀርሳ መንግላችሁ ጣሉ።
ጭቁኑ ገበሬ ማረሻህን ሳለው፣
አረምና እሾሁን መንጥርና ጣለው።
3ኛ ይኖራል
ይኖራል ይኖራል ይህም ኑሮ ሆኖ፣
ያለማው ሲወቀስ አጥፊው ተመስግኖ።
አገር የበደለው አይልመድህ ሲባል፣
ላገሩ የሠራው እስር ቤት ይገባል።
የተገላቢጦሽ ሆነና ነገሩ፣
ተከሳሾች ነጻ ከሳሾች ታሰሩ።