![](http://amharic-zehabesha.com/wp-content/uploads/2022/08/299010213_5852190198147361_3434263022859082194_n.jpg)
የፓርቲው ምክትል ፕሬዝደንት አቶ አምኃ ዳኘው በንባብ ባሰሙት መግለጫ አቶ እስክንድር “ምንም የነገረን ነገር ባለመኖሩ፤ የት እንደሔደ እና በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ ባልታወቀበት ሁኔታ አድማጭን የሚያረካ መልስ መስጠት የሚቻልበት ሁኔታ አልነበረም” ብለዋል።
በአሜሪካ ሀገር የሚገኙት የአቶ እስክንድር ባለቤት እንዳልደነገጡ እና ከፓርቲውም ሆነ በውጭ አገር ከሚገኘው የድጋፍ ኮሚቴ ማብራሪያ እንዳልጠየቁ የጠቀሱት ምክትል ፕሬዝደንቱ በዚህ ምክንያት “የመታፈን አደጋ እንዳልደረሰበት ገመትን” ሲሉ ተናግረዋል። ፓርቲው አቶ እስክንድር ያሉበትን ሁኔታ ያሳውቁናል ብሎ በመጠባበቅ ላይ ሳለ በአሜሪካ ከሚገኘው የድጋፍ ኮሚቴ በኩል የመልቀቂያ ደብዳቤው ይፋ እንደሆነ አስረድተዋል።
አቶ እስክንድር የኢትዮጵያ መንግሥት “በባልደራስም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ በፈጠረው የለየለት አምባገነናዊ ጫና ሳቢያ በአባልነትም ሆነ በአመራርነት መሥራት የማልችልበት ደረጃ ላይ ደርሻለሁ” ሲሉ ሐምሌ 16 ቀን ተጽፎ ነሐሴ 5 ቀን 2014 በፓርቲው የተረጋገጠ የፌስቡክ ገጽ ላይ በተለጠፈ ደብዳቤ ገልጸው ነበር።
የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል እና የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ የሆኑት ወይዘሮ ቀለብ ሥዩም ከሐምሌ 16 ቀን 2014 ወዲህ አቶ እስክንድርን “በስልክም ይሁን በአካል አግኝተናቸው አናውቅም” ሲሉ ተደምጠዋል። መንግሥት አቶ እስክንድርን “እንዳላፈናቸው እና እንዳላሰራቸው” ፓርቲው እንደሚያምን የገለጹት ወይዘሮ ቀለብ ከቤተሰቦቻቸው “ደህና” መሆናቸው እንደተገለጸላቸው በዛሬው ዕለት በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስረድተዋል። ይሁንና አቶ እስክንድር ከአሜሪካ ከተመለሱ በኋላ “የተለያዩ የደህንነት መኪናዎች እና የተለያዩ ሰዎች” ይከታተሏቸው እንደነበር የገለጹት ወይዘሮ ቀለብ “ውጥረት እና ከፍተኛ ጭንቀት” ውስጥ ለመሆናቸው “ምልክቶች እንደነበሩ እናውቃለን” ብለዋል።
DW