ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የሕወሓትን አላማ ማስፈጸማቸውን እንዲያቆሙ ተጠየቀ

May 19, 2022

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ስልጣናቸውን አለአግባብ በመጠቀም የሕወሓትን አላማ ለማስፈጸም የሚያከናውኑትን ተግባር እንዲያቆሙ ስምንት ተቋማት ለዳይሬክተሩ በጋራ በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ ጠየቁ።

ደብዳቤውን የጻፉት የኢትዮጵያ ሕክምና ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማኅበር፣ ’አሜሪካን ኢትዮጵያን ፐብሊክ አፌርስ ኮሚቴ’ (ኤፓክ)፣ ’ኢትዮጵያን ዳያስፖራ ሃይ ሌቭል አድቫይዘሪ ካውንስል ኦን ኮቪድ-19’፣ ’ኢትዮጵያን ስኮላርስ ኢን ኖርዲክ ካንትሪስ’፣ የደቡብ አፍሪካ የሕክምና ማህበር፣ የሌሴቶ ሕክምና ማኅበር እና ‘ፒፕል ቱ ፒፕል’ የተሰኙ ተቋማት ናቸው።

በሰሜን ኢትዮጵያ ባለፈው 18 ወራት በነበረው ግጭት የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተሩ ፖለቲካዊና ግልጽ ወገንተኝነት ያለው አካሄድ መከተላቸውን ተቋማቱ ገልጸዋል።

በንግግርና በድርጊታቸውም ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ ላይ የተሳሳተና የተዛባ አቋም እንዲይዝ ማድረጋቸውን አመልክተዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ በሚሰጧቸው መግለጫዎች፣ በሚጽፏቸው ጽሑፎችና በማኅበራዊ የትስስር ገጾቻቸው በሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች ሕወሓት በአማራና አፋር ክልሎች በፈጸመው ድርጊትና በሕዝብ ላይ ባደረሰው መከራ ላይ ዝምታን መርጠዋል ብለዋል።

ሕወሓት ወረራ በመፈጸም በርካታ የጤና ተቋማትን ማውደሙንና መዝረፉን አስታውሰው ቡድኑ ንጹሃንን በመግደልና አስገድዶ በመድፈር ወንጀሎችን መፈጸሙን አመልክተዋል።

ዓለም ዐቀፍ ተቋማት ሳይቀሩ ሕወሓት በክልሎቹ የፈጸመውን ድርጊት በሚያወጡት ሪፖርት እየገለጹ በሚገኙበት ወቅት ዋና ዳይሬክተሩ በጉዳዩ ላይ መምረጣቸው ለአንድ አካል እንደሚደሉ በግልጽ የሚያሳይ እንደሆነ ነው ተቋማቱ በደብዳቤው ላይ የገለጹት።

ከጤና ሚኒስቴር ጋር በትብብር እንዲሰሩ በተደጋጋሚ ጊዜ ለሚቀርብላቸው ጥሪ ምላሽ አለመስጠታቸው የሚያሳዝን ተግባር መሆኑንም ተቋማቱ ጠቁመዋል፡፡

ሕወሓት ወደ ትግራይ ክልል የሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ እየተደረገ ያለውን ጥረት እያደናቀፈ እንደሚገኝ የጠቀሰው ደብዳቤው ዶክተር ቴድሮስ በአሜሪካ በነበራቸው ጉብኝት ከባለስልጣናትና ከሕግ አውጪ ምክር ቤት አባላት ጋር ያደረጉት ውይይት አላማው በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ለመጎትጎት እንደሆነ ጠቅሷል።

ጉብኝቱ የ’ኤችአር 6600’ እና ‘ኤስ 3199’ ሕጎች እንዲጸድቁ ግፊት ለማድረግ መሆኑን እንረዳለን ነው ያሉት ተቋማቱ።

ዶክተር ቴድሮስ የዓለምን ሕዝብ ጤና ለመጠበቅ የተሰጣቸውን ኃላፊነት የሕወሓትን አላማ ለማስፈጸም እየተጠቀሙበት ነው፤ በመሆኑም ከዚህም ድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል ብለዋል።

አፍራሽ የፖለቲካ እንቅስቃሴና የዘር ውግንናቸውን በመተው በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ጤና መጠበቅ ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩም ተቋማቱ ጠይቀዋል።

ዘጠኙ ተቋማት በአማራና አፋር ክልሎች በሕወሓት የወደሙ የጤና ተቋማትን መልሶ በማቋቋምና ሕክምና ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም በሥነ ምግባር ጥሰት እንዲጠየቁ በጥር ወር 2014 ዓ.ም ለድርጅቱ የበላይ ጠባቂ ቦርድ የቅሬታ ማመልከቻ ማስገባቱ ይታወሳል።

በማመልከቻው ላይ የኢትዮጵያ መንግስት በዋና ዳይሬክተሩ ላይ የሕግ እና የሙያዊ ሥነ ምግባር እንዲሁም የሞራል ጥያቄዎች እንዳሉት ገልጿል።

ዶክተር ቴድሮስ ለአንድ ወገን የያዙት አድሏዊ አቋም ከፍተኛ ኃላፊነት በያዙበት ቦታ ያላቸውን ሙያዊ ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ እንደሚከተው በማመልከቻው ላይ መጠቀሱን ኢዜአ ዘግቧል።

በኢትዮጵያ መንግሥት የቀረበውን ቅሬታ አስመልክቶ የዓለም ጤና ድርጅት እስካሁን የሰጠው ምላሽ የለም።

ዋልታ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

አምባ ገነኖችን እምቢኝ! የማለት ድፍረት!! (አሥራደው ከፈረንሳይ)

Next Story

ፋኖ ተሰማራ! ፍኖ ተሰማራ! እንደ አሳምነው ጽጌ፤ ገድል ሰርተህ ኩራ! ፋኖ ተሰማራ! ለክብርህ ተታገል፣ ለአንድነትህ ሥራ – ከደረጀ አያኖ

Go toTop