አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ
ግንቦት 6 ቀን 2014 ዓ.ም
አዲስ አበባ ሸዋ
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ስለሀገር እና ስለወገን በመታገላቸው ብቻ የሕወሓት አገዛዝ በፈጸመባቸው የግፍ እስር እና ተገቢ ህክምና በወቅቱ እንዳያገኙ መከልከሉን ተከትሎ ህይወታቸው ያለፈውን የአንጋፋው ሀኪም እና ፖለቲከኛ ፕ/ር አስራት ወልደዬስን 23ተኛ ዓመት መታሰቢያ ዘክሯል።
ግንቦት 6/2014 በአዲስ አበባ ቅድስ ስላሴ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን ከንጋት ጀምረው የተገኙት የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፕሬዝደንት አቶ ማሙሸት አማረ እና የድርጅቱ የፋይናንስ ክፍል ኃላፊ ዶ/ር ታዲዮስ ቦጋለን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች እና አባላት ከፕ/ር አስራት ወልደዮስ አድናቂዎችና ቤተሰቦች ጋር በመሆን በሀይማኖት አባቶች ጸሎትና በጧፍ ማብራት ስነ ስርዓት ዘክረዋቸዋል።
የፊደል ገበታ ቀራጩ እና ባለውለታችን የሆኑት የቀኝ አዝማች ተስፋ ገ/ስላሴ ልጅ አቶ አበበ ተስፋ እና ሌሎችም በመታሰቢያው የጸሎትና የጧፍ ማብራት መርኃ ግብሩ ላይ ተገኝተዋል።
ከቤተሰቦች መካከል ወ/ሮ አሰለፈች ወ/ሚካኤል እና ልጃቸው ልዕልት ገሊላ ፍስሃም በ23ተኛው የፕ/ር አስራት የመታሰቢያ ዝግጅት ተገኝተው ተሳትፈዋል።
በአማራው ብሎም በኢትዮጵያ የሰላማዊ ትግል ምዕራፍ የላቀ አበርክቶት የነበራቸው ፕ/ር አስራት ወልደዮስ በህክምና ሙያቸውም ሆነ በፖለቲካ አይሰበሬ ትግላቸው ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ ከፍተኛ እውቅና ፣ አርዓያነትን እና ዝናን ያተረፉ ጀግና የነጻነት ታጋይ ነበሩ።
በጸሎትና በጧፍ ማብራት ስነ ስርዓቱ ከተገኙት መካከል የፕ/ር አስራት ወልደዮስ የትግል ጓድ እና የመኢአድ ፕሬዝደንት አቶ ማሙሸት አማረ እንደገለጹት ፕ/ር አስራት ወልደዬስ ለገዥዎች ስልጣን እና ለጥቅም ከማደር ይልቅ ነጻነት እና ክብሩን ለተገፈፈው ሰፊው ህዝብ በመታገል ታሪካዊ አሻራ አስቀምጠው አልፈዋል።
በፕ/ር አስራት ላይም ሆነ በህዝብ ላይ ክፉ የሰሩት ሁሉ ዛሬ ላይ በህይወት እንደሌሉ የገለጹት አቶ ማሙሸት እንደ ፕ/ር አስራት ለታሪክ የሚበጅ ነገር ሰርቶ ማለፍ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ከቀኑ 7 ሰዓት ጀምሮም በመኢአድ ጽ/ቤት አዳራሽ አመራሮች፣አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም አድናቂዎችና ቤተሰቦች በተገኙበት የፕ/ር አስራት 23ተኛ ዓመት መታሰቢያ እንደሚከናወን አስታውቀዋል።
ለተሳታፊዎች ሁሉ ምስጋና ያቀረበችው ልዕልት ገሊላ ፍስሃም በበኩሏ ፕ/ር አስራት ከህዝብ ጎን በመቆም መልካም ታሪክ ጥለው ማለፋቸውን አውስታ በአገዛዙ በደረሰባቸው በደል ያለጊዜያቸው ማለፋቸው ግን አሳዛኝ ስለመሆኑ ተናግራለች።
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የወጣቶች ጉዳይ ኃላፊ አቶ ለገሰ ወልደ ሀና በበኩላቸው የፕ/ር አስራት ወልደዬስ መታሰቢያ ድርጅቱ በእያዓመቱ እንደሚያደርገው ሁሉ ቴዎድሮስ አደባባይ በሚገኘው ዋና ጽ/ቤት አዳራሽ ከቀኑ 7 ሰዓት ጀምሮ እንደሚከናወን በመግለጽ ዝግጅቱን በስፍራው ተገኝቶ መከታተል እንደሚቻል ጠቁመዋል።
አማራ ሚዲያ ማዕከል (አሚማ)ም ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተገኝቶ የመታሰቢያ ዝግጅቱን ተከታትሏል።
አማራ ሚዲያ ማዕከል