በጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ጉዳይ የአማራ ክልል መንግስትና የአማራ ብልፅግና እጃቸዉን ሊያስገቡ ይገባል!! – ቹቹ ታደሰ

May 9, 2022

በዚህ አጀንዳ ዙሪያ ተመልሸ የመጣሁት የጋዜጠኛው መታፈን ያለንበትን አገራዊ ሁኔታ የሚያሳይ በመሆኑ ነው። እንዴት አንድ ታዋቂ ጋዜጠኛ ታፍኖ ለቀናት ያህል ደብዛው ጠፍቶ ይቆያል? ይህ አገራዊ የዜጎች የደህንነት ስጋት ማሳያ ነው።

ለዚህም ነው ዛሬም ይሄን እንቁ የአማራ ጋዜጠኛ ማን ነው የሰወረው? ብለን ለመጠየቅ የምንገደደው።

በጋዜጠኛው መታፈን ዙሪያ ብዙ አስተያየቶች እየተሰጡ ሲሆን፤ ቀላል ግምት የማይሰጣቸው ሰዎች ጋዜጠኛው የተሰወረው በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ነው የሚል ቢሆንም መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ ያለው ነገር የለም።

እንደሚገመተው አፈናው የተፈፀመው በመንግስት የፀጥታ አካላት ከሆነ፤ ልጁ በህጉ መሰረት በ48 ሰዓታት ውስጥ ወደ ፍ/ቤት መቅረብ ይገባው ነበር። ነገር ግን ይህ ሲሆን አልታየም።

መንግስት ስለ ጎበዜ እገታ ምንም አይነት እጁ ከሌለበት ደግሞ በዝች አገር ሌላ አካል ችግር እየተፈጠረ አለ ማለት ነው። ይሄም ማለት የአማራን ጉልሃን (elites) የሚያጠፋ ድብቅ ቡድን አዲስ አበባ ላይ ተቋቁሟል ማለት ነው። ይህ ከሆነ እጅግ አደገኛ ነገር ውስጥ መግባታችን ነው።

ያም ሆነ ይህ ጋዜጠኛ ጎበዜ የታፈነው በመንግስት አካላትም ሆነ በኢ-መደበኛ አካላት፣ ጋዜጠኛው የተጠቃው የአማራ ድምፅ በመሆኑ ስለመሆኑ ቅንጣት ታክል አልጠራጠርም።

ስለሆነም በአማራ ህዝብ ስም ስልጣን ላይ ያለ ማንኛውም አካል በተለይም የክልሉ መንግስትና መሪ ድርጅቱ የጎበዜ ጉዳይ አጀንዳቸው ሊሆን ይገባል።

የጎበዜ ጉዳይ ተጣርቶ ችግሩና የችግሩ ምንጭ በጊዜ ካልታወቀ፤ ለአማራ ጉልሃን በተለይም የአማራ ድምፅ ለመሆን ለሚሞክሩት ወቅቱ ከባድ እንዳይሆን እሰጋለሁ።

በመጨረሻም የአማራ ጉልሃን ‘ያንተ ቤት ሲንኳኳ ይሰማል እኔ ቤት’ የሚለውን የንቁ አባቶች አባባል ማስታወስ እወዳለሁ። ዛሬ ተከላክለን ያላቆምነው አደጋ ነገ በየቤታችን መግባቱ አይቀርምና ዛሬ ነው ነገም-በኔ ብለን መነሳት ያለብን።

የጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ መታፈን የኛም የነገ ዕጣ እንዳይሆን ዛሬ እንጠይቅ! ይህ መልዕክት ለግለሰቦች ብቻ ሳይሆን ለተቋማት ጭምር የሚሰራ ነው!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

የስብዓዊ ማዕበል የጦርነት ስልት ከሽፎል፣ እልፍ አእላፍ ወጣቶች ረግፈዋል!!! ዳግማዊው “ህዝባዊ ሠራዊት፣ለህዝባዊ ጦርነት!” እልቂትም ተደግሏል!!!

Next Story

የግንቦት ቀጠሮ  (ፍርዱ ዘገየ) 

Go toTop