የአፋር የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ሊቀመንበር አቶ ጋአስ አሕመድ የአብአላ ከተማ ህወሓት በሚመራቸው ታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር መግባቱን መረጃ እንደደረሳቸው ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ዛሬ ሰኞ ባወጣው መግለጫ ኪልበቲ በተባለው ዞን አብአላ እና መጋሌ ወረዳዎች በኩል ህወሓት ጦርነት እንደከፈተ ገልጿል። የአፋር ክልላዊ መንግሥት በከባድ መሣሪያ የታገዘ ባለው እና በአብአላ፣ በመጋሌ እና በበራህሌ በኩል በሚካሔደው ጦርነት “በርካታ ንፁሀን” መጎዳታቸውን በፌስቡክ ባሰራጨው መግለጫ አስታውቋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ጦርነት ማቆሙን ካሳወቀ ጀምሮ ቂልበቲ ረሱ ተብሎ በሚጠራው ዞን ሁለት አካባቢ በሶስት ወረዳዎች ጦርነት ሲካሔድ እንደቆየ የአፋር የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ሊቀመንበር አቶ ጋአስ አሕመድ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። አቶ ጋአስ የአብአላ ከተማ በዛሬው ዕለት በትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር መግባታቸውን የሚጠቁም መረጃ እንደደረሳቸውም ገልጸዋል። እስካሁን ድረስ በህወሓት ተያዘ ስለተባለው አባላም ሆነ ስለደረሰው ጉዳት የኢትዪጵያ መንግሥት የሰጠው መግለጫ የለም።
የቪዲዮ ዘገባ፦ ሰለሞን ሙጬ
DW