በኢትዮጵያ የአርበኝነት ታሪክ ውስጥ ጉልህ አሻራ ትተው ካለፉት አባቶች መካከል ራስ ብሩ ወልደገብርኤል ይታወሳሉ :: ራስ ብሩ ወልደገብርኤል ያደጉት በአፄ ምኒልክ ቤተመንግስት ውስጥ ነበር :: ብሩ ወልደገብርኤልን አፄ ምኒልክ እጅግ ያቀርቧቸው ነበር:: እንዴውም ብሩ ወልደ ገብርኤል የአፄ ምኒልክ የሚስጥር ልጅ ነው ተብሎ በቀበሌው በሀገሩ ሁሉ ይወራ ነበር ::
ራስ ብሩ የራስ ማዕረግ እስኪያገኙ ድረስ በሀገሪቱ ጦርነት ውስጥ አንፀባራቂ ድል አስመዝግበዋል :: በማይጨው ከባድ ተጋድሎ ያደረጉ ጀግና መሪ ነበሩ :: የጦር ሚንስትር ሆነውም አገልግለዋል :: እኒህ መሪ እጅግ ሀብታም ነበሩ :: በዘመኑ የራስ ብሩን ያህል ግብር የሚያበላ አልነበረም ይባላል :: ግብር ማብላት እንደ ብሩ ወልደገብርኤል ነው ይባልላቸው ነበር :: ታዲያ የእኒህ ሰዉ ርስት የት ነው? ከተባለ አሁን መስቀል አደባባይ የምንለው ቦታና የኤግዝብሽን ማዕከሉን ሁሉ ያካተተ ነው :: መስቀል አደባባይ ቀደም ሲል የራስ ብሩ ሜዳ ነበር የሚባለው :: ራስ ብሩ በህይወት እያሉ ከይዞታቸው ላይ ቀንሰው የራስ ብሩ ሜዳ የሚባለውን ለመሰቀል ለደመራ ማክበሪያ ይሆን ዘንድ ለኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሰጡ :: ከዚያ በሁዋላ ኦርቶዶክስ ይዞታዋ ሆኖ ቆየ :: ስሙም ከራስ ብሩ ሜዳ ወደ መስቀል አደባባይ ተቀየረ:: ኦርቶዶክስ ራስ ብሩን ባርካ ይህንን ቦታ የአምልኮ ስፍራዋ አድርጋ ስትኖር ድንገት ደርግ መጣ :: ደርግ ሲመጣ መስቀል አደባባይን ለአብዮቱ ጥሩ አደባባይ ነው ብሎ አመነና ይህንን ቦታ ለራሱ መረጠው:: ስለሆነም ስሙን አብዮት አደባባይ ብሎ ሰይሞ የራሱ አደረገ :: በዚህ መሃል የራስ ብሩ ወልደግብርኤል ልጆች ሸፈቱ :: መስፍን ብሩ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ፖለቲካል ሳይንስ ያስተምር የነበረውና መርድ ብሩ የጦር ትምህርት ተምሮ የአፄ ሃይለስላሴ የቅርብ ሰዉ የነበረው የራስ ብሩ ልጅ ተያይዘው የአባታቸው ዘመዶች ሀገር መንዝ ገብተው ሸፈቱ :: መንዝ ውስጥ ባዶጌ የተባለች ቀበሌ ውስጥ የእኔን እናት ዘመዶች በሙሉ አስታጥቀው ከደርግ ጋር ተዋጉ :: እነ መርድ የአባታቸው ዘመዶች ጋር ማለትም የእኔ እናት ወይዘሮ በቀለች ደባልቄ ዘመዶች ጋር ሆነው ደርግን አምስት ዓመት ተዋግተዋል:: መርድና መስፍን ሲዋጉ ቆይተው የተሰውት እዚያው እኛ አካባቢ ነበር:: ብዙ የእናቴ ዘመዶች ከደርግ ጋር በነበረ ውጊያ ተዋድቀዋል ::
ታዱያ ከፍ ሲል እንዳልኩት ራስ ብሩ ይህንን መስቀል አደባባይን ለኦርቶዶክስ ከሰጡ በሁዋላ ደርግ ወስዶ አብዮት አደባባይ አድርጎት ኖረና ኢህአዴግ ሲመጣ ይህ ቦታ የቤተክርስቲያንም የመንግስትም መጠቀሚያ ሆነ :: ኦርቶዶክስ ጠንከር ብላ ማምለኪያዋን አላስመለሰችም :: ኢህአዴግ ደርግ የወረሳቸውን አንዳንድ ማምለኪያ ቦታዎች ሲመልስ መስቀል አደባባይን ችላ ብሎት ቆየ :: እስከማውቀው ድረስ አሁንም ይህ ቦታ የኦርቶዶክስ ነው :: ቦታው ተመልሶ ለቤተክርስትያንቱ መሰጠት አለበት ብዬ አምናለሁ :: ታሪኩ ከራሴ ቤተሰብ ጋር የተያያዘ ነገር ስላለው ሃሳብ ልስጥ ብዬ ነው ::
ይህ ሁሉ ሆኖ ኦርቶዶክስ ይህንን ቦታዋን ሕጋዊ በሆነ መንገድ እስክትረከብ ድረስ ፕሮቴስታንቱ ፕሮግራም ሲያዘጋጅ መቃወም ተገቢ አይደለም :: ሌሎች ሃይማኖቶችም ፕሮግራም ሲያደርጉበት አይተናል :: ደርግ የደም ቀለም ያለው ጠርሙስ ሰብሮ ቀይሽብር ያወጀበት ቦታ ነው :: ይህ ቦታ ለቤተክርስቲያን በግልፅ እስኪመለስ የኦርቶዶክስ አማኞች ሕጋዊ ፈቃድ ካገኙ የፕሮቴስታንት አባላት ጋር መጋጨት የለባቸውም :: እግዚአብሔር ሀገራችንን ይባርክ:: መንግስት የሃይማኖት ቦታዎችን በግልፅ ከለየ መጋጨት አይኖርም :: ማምለኪያ ቦታ እንደልብ አለና አንጋጭም::