የኢሌኒ ገብርመድን ECEX ጉድና የጎንደር ዩኒቨርሲቲው የክብር ዶክትሬት ቁማር – ሰርፀ ደስታ

December 9, 2021

ሰሞኑን በሚስጢር ነው ተብሎ ከተለቀቀ ኢሌኒ የአማራ ጠልነቷንና የአርመኔው ወያኔ አጋርነቷ የተጋለጠበት ቪዲዮ ከታየ በኋላ ሴትዮዋን ያለቦታዋና ያለ ችሎታዋ የክብር ማማ ላይ ተሸክመው ያወጧት ሁሉ  በዚህ መጥፎ ጊዜ እኛንም ታጋልጠናለች በሚል መሰለኝ ከሰቀሏት ከማማው ላይ እያወረዱ ሲፈጠፍጧት ተመልክተን ስንታዘብ ሰንብተናል፡፡ ከእነዚህ በጣም የገረመኝ ግን የጎንደር ዩኒቭረሲቲ የተባለው ተቋም ነገር ነው፡፡ ለሴትዮዋ የክብር ዶክተሬት መስጠቱን ሳንሰማ ከዚህ በኋላ የክብር ዶክተሬቷን አንስቻለሁ ሲለን ሰማን፡፡ የክብር ዶክተሬትም በድብቅ መሰጠት ጀምሮ ይሆን ወይስ እንዴት ነው ነገሩ? እሺ ከሰጠስ መቼም የክብር ዶክተሬት ለመስጠት በግልጽና በብዙ ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ የሆነ በጎ ተጽኖ ፈጣሪ መሆን ከመስፈርቶቹ ዋነኛው ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ለመሆኑ ግን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ኢሌኒ በየትኛው ሥራዋ ይሆን የክብር ዶክትሬት ሊሰጣች የቻለው? መቼም በኮሞዲቲ እክስቼንጅ (ECEX) እየተባለ በሚጠራው ቁማር በላት የተጫዋችነት ብቃቷ ነው ብሎን ማረፉ አይቀርም፡፡ ኢሌኒን ከዚህ ውጭ የሚያውቃት ካለ ንገሩን፡፡

የዚህን ኢሴክስ የተባለ ኢሌኒ ትመረው የነበረ ድርጅት ቁማር ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ባያውቁት ባልገረመኝ ነበር፡፡ ቁማሩ ከጅምሩ ከተጠነሰሰባት በይፋ የጎንደር ነጋዴና የከተማዋ ባለስልጣኖች ሁሉ  ምን አልባትም የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራርም የሚያቁትን አስነዋሪ ድርጅት ኤስክስን የምትመራ ሰው የክብር ዶክትሬት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መስጠቱ የነውሩ አባልም እንዳይሆን እጠረጥራለሁ፡፡ ይሄ ነውር ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ አመራር አይታወቅም ነበር ለማለት አያስችልም፡፡ ሁሉም ነገር የተነሳው ከዛው ከጎንደር ከተማ ነበርና፡፡

ኢሴክስ የተባለው ኢሌኒ ትመራው የነበረው ድርጅት እውነታ እንደሚከተለው ነው፡፡ ኢሌኒ እንደውም ከጅምሩ ስላልነበረችበት በዚህ ውስጥ ተጠያቂም ተወቃሽም ላትሆን ትችላለች፡፡ ሆኖም ግን ሰዎች ስንት ለፍተው ባዘጋጁት ቦታ ከአሜሪካ መጥታ ጉብ ስላለችበት ራሷን አዋቂና ፈጣሪ አድርጋ ብዙ ታዝበናታል፡፡ በዚሁ ወደ እውነታው ልውሰዳችሁ፡፡ ኋላ ላይ ኤሴክስ በሚል እነመለስ ከሌሎች ነጥቀው ያቋቋሙት ድርጅት መጀመሪያ የተመሰረተው በአምስት ባለሙያዎች ጎንደር ውስጥ ነበር፡፡ የሰዎቹን ሥም ዝርዝር መጥቀስ ስላልፈለግሁ ነው፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች አንድ ከኢትዮጵያ ወደ ዓለም ዓቀፍ ገበያዎች በሥፋት በዋናነት ሰሊጥን በተቀላጠፈ ሁኔታ ለማገበያየት የሚያስችል የግብይትና ዘመናዊ የምርት ደረጃ ጥራት ማረጋገጫ ግዙፍ ላቦራቶሪ አገልግሎት መስጠት የሚችል Sellit (sell it) በአማሪኛ  ሽጠው የሚል ትርጉም ሲኖረው እግረመንገዱንም የሐሳባቸው ዋነኛ የሆነውን ምርት ሰሊጥን ያካተተ ስያሜ ያለው ድርጅት በጎንደር ከተማ ይመሰርታሉ፡፡ በወቅቱ የሐሳቡ ግዝፈትንና አዋጭነት የተረዱት የከተማው ባለስልጣናት ለዚሁ የሚሆን መሬት ለመስጠት ምንም ማቅማማት አልነበረባቸውም፡፡ ሆኖም ለሥራው የሚያስፈልገው የቦታ መጠን ከተማው ክልሉለን ሳያሳውቅ ከሚሰጠው አንድ ሄክታር መሬት በላይ በመሆኑ ለክልሉ የፕሮጄክቱን ሀሳብ (ፕሮፖዛል) አባሪ አድርጎ ከተማው ይጽፋል፡፡ በክልልም ደረጃ ያሉ ባለስልጣናት ሐሳቡን ሲያዩት እጅግ ስለወደዱት ቦታው እንዲሰጣቸው ለጎንደር ከተማ መፍቀድ ብቻም ሳይሆን ሌላም ድጋፍ የሚያስፈልግ ከሆነ ክልሉ ራሱ ሊደግፍ ቃል ይገባል፡፡ ጉዳዩም በክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት ልዩ ትኩረት እንዲያገኝ ሆነ፡፡

በዚህ ሁኔታ ላይ እያለ የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት ይሄ ግዙፍ ፕሮጄክት ስለሆነ በአማራ ክልል ብቻ ሳይሆን ቢያንስ ትግራይና ኦሮሚያን በተጨማሪ ማካተት ስለሚያስፈልገው ከሚመለከታቸው የየክልሉ ባለስልጣናት ጋር በመነጋገር በአጭር ጊዜ ውስጥ የእነዚህ ክልሎችንም በሚያካትት መልኩ ሥራው እንዲሰራ እናደርጋለን ብለው ቃል ገቡ፡፡ በወቅቱ በዋናነት ጉዳዩን የሚከታተሉት በረከትና አዲሱ ነበሩ፡፡ በዚህ ሁኔታ እያለ ተጨማሪ የድርጅቱ አባል መሆን የሚችሉ ሌሎች ባለሙያዎችንም እንዲካተቱ ተደረገ፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በግብርና ሚኒስቴር ሚኒስቴሩን የሚያማክሩ ከፍተኛ ባለሙያዎችና ከሌሎች ትልልቅ የንግድ ድርጅቶችም ጭምር (ለምሳሌ ከሐግቤስ፣ ዳሸን ቢራ፣ ሌሎችም) ነበሩ፡፡

በዚህ ወቅት ከመጀመሪያ መሥራቾቹ አንዱ የነበረው ባለሙያ ለኢጣሊያን ኢምባሲ በአማካሪነት የሚሰራ ስለነበር የኢጣሊያን ኢምባሲ የዘመናዊ ላቦራቶሪውን በማደረጀት እንደሚያግዛቸው ቃል ገብቶ ነበር፡፡ የፈጠራ ሐሳቡ ኖሮ በአግሮ ኢንዳስትሪ ለሚሰማሩ በሚል በልማት ባንክ የተቀመጠ የግብርና ሚኒስቴር 20 ሚሊየን ብርም ቃል ይገባላቸዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ እያለ ጉዳዩ የአገሪቱም ጠ/ሚኒስቴር ማወቅ የሚገባቸው ስለሆነ ወደመለስ ቢሮ ይገባል፡፡ እዛ ሲደርስ ግን አንድ ነገር ተከሰተ፡፡ በመለስ እይታ ፕሮጄክቱ ግዙፎቹን የሕወሐት የንግድ ድርጅቶችን አደጋ ላይ የሚጥል ሆኖ ተገኘ፡፡ ስለዚህ  ፕሮጀክቱ ጥሩ ቢሆንም እንዲህ ያለ ፕሮጄክት መሰራት የሚገባው በመንግስት እንጂ በግል ሊሆን አይገባም በሚል ያ ሁሉ የተለፋበትን በቀጭን ትዕዛዝ እንዲቆም ተደረገና በመንግስት በኩል የሚሰራበትን አደረጃጀት ተጀመረ፡፡ ጎንደር ላይ ተሰጥቷቸው የነበረንም ቦታ በአንድ ስልክ ጥሪ እንዲሰረዝ ተደረገ፡፡

እንግዲህ በዚህ ሁኔታ እያለ መለስ አሜሪካ ለጉብኝት ይመጣል፡፡ በዛን ወቅት ነበር ኢሌኒን በአንድ ስብሰባ ላይ ስትሳተፍና የሆነ ወረቀት ስታቀርብ ያገኛት፡፡ በዚህ ወቅት ነበር መለስ ይሄን ሐሰብ ከእነ ሙሉ ሰነዱ የሰጣትና ይሄን ፕሮጄክት እንድተመራ ወደ ኢትዮጵያ የጋበዛት፡፡ ከላይ ስጀምር ኢሌኒ ቁማር ውስጥ የለችበትም ያልኩት ለዛ ነው፡፡ ምክነያቱም የእሷ ድርሻ የሚጀምረው ከዚህ በኋላ ነውና፡፡ በተጋበዘችውም መሠረት ኢሌኒ ይሔን ፕሮጀክት ለመምራት ወደ አዲስ አበባ ትመጣለች፡፡ ከመከመሪያ መስራቾች ከነበሩት አንዱ በዋና አማካሪነት ይመደብላታል፡፡ በአማካሪነት ከምንለው በሥራ አስኪያጅነት ብንለው ይሻላል፡፡ ሥራውን ሙሉ በሙሉ የሚሰራው በእሱ ስለሆነ፡፡ ሌሎቹ የመጀመሪያዎቹ መስራቾች እንዲበተኑ ይደረጋል፡፡ አንዳንዶቹም ከአገር ጭምር እንዲወጡ፡፡

እንግዲህ ይህ የኢሴክስ ጉድ ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ እንግዳ ሆኖ ይሄን ድርጅት የምትመራን ሰው የክብር ዶክተሬት መሥጠት ዩኒቨርሲተው የቁማሩ አንዱ አካል እንደነበር ከመመስከር ሌላ ምንም ዓይነት ለክብር የሚያበቃ ብቃት አይቶ የክብር ዶክተሬትን የሚያህል ነገር ሊሰጥ እንደደፈረ አልገባንም፡፡ በእኔ እምነት የዩኒቨርሲትው ከፍተኛ ባለስልጣናት ይቅርና ተራው ማህበረሰብም ጉዳዩን አሳምሮ ያውቀዋል እላለሁ፡፡ በወቅቱ ሐሳቡ በትልቅ አዳራሽ የከተማው ነጋዴዎችና ሌሎች ተቋማትም ባለስልጣናት በተገኙበት ተብራርቶ ከፍተኛ የሆነ መነቃቃትን ድጋፍን ያገኘ ነበርና፡፡ በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው ሂደቱን ያውቃል የሚል እምነት አለኝ፡፡ እንግዲህ የዶክተሬት ዲግሪ በመስጠት ሌብነትና ዝርፊያን ወደ ላቀ ሁኔታ እንዲደርስ የተባበረ ዩኒቨርሲቲ ምን ልንለው እንደምንችል አላውቅም፡፡ ምን ዓልባትም የክብር ዶክተሬቱን መሸለሙን ሳንሰማ የቀረንው ያው የሌባ ነገር ሆኖ እንዳይሆን፡፡ ዛሬ ደግሞ ለማስመሰልና ከሕዝብ ጋር ነኝ ለማለት በድብቅ የሰጠውን የክብር ዶክተሬት በአደባባይ ሽሬያለሁ ብሎን አረፈ፡፡ ይሄ ሁሉ አልሆነም እንኳን ብንል ለኢሌኒ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት የሚሰጥበት አንዳች ምክነያታዊ መስፈርት የለውም፣ የወያኔን ባለስልጣናት ለማስደሰት እንጂ፡፡ የማይገባትን ኢሌኒ የክብር ዶክትሬት በድብቅ ሰጥቶ የነበረው ዩኒቨርሲቲ ሴኔትስ ማን ይጠይቀው?

ይሄን ጉዳይ በግርድፉ ማውጣት ስላለብኝ ነው፡፡ ከሰሞኑ የአስመሳይነት ቁማርም ጋር ስለተነሳ፡፡ በርካታ እንዲህ ያሉ ተመሳሳይ ነገሮች አሉ ፡፡ ብዙ አገርን በእነአውሮፓና ቻይና ደረጃ ሊለውጥ የሚችል ሐሳብ ያላቸው ሰዎች ተመሳሳይ እጣ ገጥሟቸው ወይ አገር ለቀው ሄደዋል ወይ እዛው አልባሌ ሆነው ቀርተዋል፡፡ በነገራችን ላይ እንደነዚህ ያሉ ሰዎች አሁን አገር ውስጥ ባለው ሁኔታ መሥራት አይችሉም፡፡ ምክነያቱም ሐሳባቸው በጣም ግዙፍና ወሳኝ ለውጥ የሚያመጣ ስለሆነ ተቀምተው በማስጠንቀቂያ ነው የሚሰናበቱት፡፡ ምክነያቱም ዛሬ በሥልጣን ላይ ያሉት በአብዛኛው እንዲህ ያለ ነገር ከመጣ ቦታ ሊያሳጣቸው ይችላልና ነው፡፡ ከላይ ባለሙያዎቹን እንዲነጠቁ ያበቃው የወያኔን ድርጅቶች የሚጋፋ አደገኛ አካሄድ ሆነ ስላገኙት ነው፡፡  ከላይ እንደነገርኳችሁ ከመስራቾቹ አንዱ የግድ ሥራውን እነሱ በሚፈልጉትም ሆኔታ ቢሆነ አብሮ ካልሆነ ኢሌኒ እንደማትችለው ስለአወቁ ጠቀም ያለ ገንዘብ ሰጥተውት ይመስለኛል በአማካሪነት ሲቀር ሌሎቹን እንዲበተኑ ነው ያረጓቸው፡፡  ከዚህ በላይ ስለሲህ ጉዳይ መናገር አልፈልግም፡፡ የሚዲያ ሰዎች ጉዳዩን የበለጠ ማውጣት ከፈለጉ ግን መረጃውን የሚያገኙበትን መተባበር ይቻላል፡፡ በራሳቸውም ቢሄዱበት ብዙ ሕዝብ የሚያውቀው እውነት ነው፡፡

ሰሞኑን በተለይ በአማራ ክልል የደረሰውን ውደመት ለመመለስ 30 ዓመት ይፈጃል የሚሉ ኮልኮሌዎችን እየሰማን ነው፡፡ በጎነቱና ከልብ የሆነ ቁርጠኝነቱ ቢኖር ግን አይደለም ዛሬ በአማራና በአፋር የወደመውን ለመተካት ኢትዮጵያን በሙሉ በ10 ዓመት ውስጥ ሙሉ በሙሉ በሚቀይር ሁኔታ ስልት ነድፎ በተግባር ማዋል በተቻለ ነበር፡፡ የሕልውና አደጋ እያሉ ወያኔን እስከ  ሰሜን ሸዋ ድረስ ስበው የምርም የሕልውና አደጋ እንዳደረጉት አሁንም ገና ከወዲሁ የደረሰው ውድመት በ30 ዓመትም አይመለስም እያሉ ማላዘን ጀምረዋል፡፡ በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወደመሬትነት የተቀየሩት ታላላቅ በተለይም የታላቋ የጀርመን ከተሞችን መልሶ ብቻ ሳይሆን በበለጠ ዘመናዊነት ለማበልጸግ 20 ዓመት አልፈጀም፡፡  እንግዲህ በቦታው ላይ ተቀምጠው ትልልቅ ሐሳቦችን በማምከን የእነሱን ድካም የሚጭኑብንን ተሸክመን የትም መድረስ አይቻልም፡፡ ቁርጠኝነቱ ካለና አስተማማኝ ዋስትና የሚገኝ ከሆነ አሁንም የትልልቅ ሐሳብ ባለቤቶችን ማደራጀትና የተጎዱ የአማራና አፋር አካባቢዎችን ከመውደማቸው በፊት ከነበሩበት በበበለጠ  በ5ዓመት ውስጥ መገንባት ይቻላል፡፡ ሕዝብ ይሄን ሊያውቅ ይገባል፡፡ ችግሩ በተለይ በአማራ ክልል የከፋ ነው፡፡ ከላይ የነገርኳችሁ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተግባር ከመገለጫዎቹ አንዱ ነው፡፡

ቅዱስ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ ሠላምን ይስጠን!

አሜን!

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

ሌ/ጄ ባጫ ደበሌ ታላቁን የድል ዜና መቀሌ ላይ ሆነን እናበስራለን አሉ

Next Story

ዝግጅት! ለማን? – ቴዎድሮስ ጌታቸው

Go toTop