የተበተነውን የጠላት ኀይል ትጥቅ ማስፈታት እና የዘረፈውን ለማስቀረት ሕዝቡ እንዲረባረብ የኢፌዴሪ ጦር ኀይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥሪ አቀረቡ

December 3, 2021
 በምሥራቅ እና በምዕራብ የተገኘው ድል በመሃል ሀገር እንደሚደገም የኢፌዴሪ ጦር ኀይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደጎሎ አካባቢ በአራተኛው ቁልፍ ግንባር ሆነው ባስተላለፉት መልዕክት ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ቡድን መበተኑን ገልጸዋል፡፡ ጠላት ተበትኖ እየሸሸ መሆኑን ገልጸው የተበተነውን የጠላት ኀይል ትጥቅ ማስፈታት እና የዘረፈውን ማስቀረት የሕዝቡ ሚና የጎላ በመሆኑ በአንድነት እንዲረባረብ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
ከሰሞኑ በሚሠሩ ኦፕሬሽኖች በወራሪው አሸባሪ ቡድን የተያዙ ተጨማሪ ከተሞች ነጻ እንደሚወጡ ገልጸው፣ ለወረራ የገባው አሸባሪ ምንም ነገር ይዞ እንዳይወጣ ሕዝቡ ተደራጅቶ ማስቀረት እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።
“ጠላት ፈርሷል፤ ተበትኗል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ “አሁን ጠላት ያለው አማራጭ የሰረቀውን አስረክቦ እጁን መስጠት ነው” ብለዋል። “የሰረቀውን አስረክቦ እጁን ከሰጠ ምርኮኞችን ተንከባክቦ መያዝ የጀግና ባህላችን ነው” ብለዋል።
ከአሸባሪው ትህነግ ነፃ በወጡ አካባቢዎች በአስቸኳይ መስተዳድሩን በቶሎ መልሶ ማቋቋም እንደሚገባም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
“ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነዋል፤ ወታደሩ በከፍተኛ ሞራል ላይ ነው” ሲሉም የወገን ኃይል ያለበትን ደረጃ አመላክተዋል።
ሕዝቡ እስካሁን ላደረገው ተሳትፎ ምስጋና አቅርበው፣ “አንድነታችን የተጠበቀ ይሁን፤ የአሉባልታ ወሬ ወጀብ አይውሰደን፤ አንድ ሆነን የማትደፈር ሀገር ለልጆቻችን እናስረክብ” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልእክት አስተላልፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጋሸና ግንባር ድሉን ወደ ሰቆጣና ወልድያ የማስፋት ስራ እየተሰራ ነው፤ በደጎሎ ግንባር የሚሰሩ በጣም ጠቃሚ ስራዎች አሉ፤ በዚህ ግንባር ዛሬ እና ነገ በሚሰሩ ኦፕሬሽኖች ከሚሴን፣ ባቲን፣ ኮምቦልቻን እና ሌሎች ከተሞችን እንቆጣጠራለን፤ ደሴን የምንቆጣጠርበትን ሁኔታን እናሰፋለን፤ አሁን ጠላት ያለው አማራጭ የሰረቀውን አስረክቦ እጁን መስጠት ነው ብለዋል፡፡
ባሕር ዳር፡ ሕዳር 23/2014 ዓ.ም (አሚኮ)

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

በሸዋሮቢት ከተማ ለታሪክ ምስክርነት የተረፈ ንብረት የለም፤ ሙሉ በሙሉ ወድሟል

Next Story

የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም አማራ ሆይ ከዳግም ክህደት ተጠንቀቅ! – አገሬ አዲስ

Go toTop