በክልሉ ከአሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የነበራቸው 98 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

November 4, 2021
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከአሸባሪዎቹ ህወሓት እና ሸኔ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የነበራቸው 98 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አብዱልአዚም መሐመድ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመውጣቱ አስቀድሞ የክልሉ ፖሊስ የተጠናከረ የክትትል ስራ ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡
ኮሚሽነሩ እንዳሉት በሚኒስቴሮች ምክር ቤት ጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም ወጥቶ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ የጸደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የክልሉን ሠላም ለማስጠበቅ ለፀጥታ አስከባሪ ኃይሉ ተጨማሪ አቅም ሆኖታል።
ግለሰቦቹ በሕግ ቁጥጥር ስር የዋሉት ከአሸባሪዎቹ ህወሓት እና ሸኔ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንደነበራቸው ፖሊስ በደረሰው መረጃ መሰረት ከጥቅምት 21/ 2014 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ባደረገው ኦፕሬሽን ነው ብለዋል፡፡
አሸባሪው ህወሓት በሀሰት ወሬ ሀገርን ለማሸበር ጥረት እያደረገ መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነሩ በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦችም አሸባሪው ህወሓት በአማራ እና አፋር ክልሎች የፈጸመውን ጥቃት ለመድገም በድብቅ ሲዘጋጁ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡
እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ ግለሰቦቹ ላፕቶፕ ኮምፒዩተሮች እና ሌሎችንም ቁሳቁሶች ይዘው በነዋሪው ላይ ሽብር ለመልቀቅ የሚያስችል የፈጠራ ወሬዎችን የያዙ ቪዲዮዎችን ሲያዘጋጁ ተደርሶባቸዋል፡፡
ፖሊስ ይህን ተጨባጭ ማስረጃ መሠረት በማድረግ ግለሰቦቹን በሕግ ቁጥጥር ስራ እንዲውሉ ማድረጉን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
ኅብረተሰቡ ስንቅ ከማዘጋጀት ጀምሮ አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ በማድረግ ከፀጥታ ኃይሉ ጎን መቆሙን ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል፡፡
ይህም በክልሉ የሚገኙ የፀጥታ ኃይሎች የአሸባሪዎችን እንቅስቃሴ አስቀድመው ለመከላከል ከፍተኛ አቅም እንደፈጠረ ተናግረዋል፡፡
ኅብረተሰቡ በተለይ ለአሸባሪው ህወሓት የፈጠራ ወሬ ሳይደናገጥ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።
እንዲሁም ኅብረተሰቡ በማህበረሰብ አቀፍ ፖሊሲንግ ተደራጅቶ አካባቢውን እንዲጠብቅ የማድረግ ስራ እየተካሄደ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ከኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ጋር በመተባበር እየሰሩ መሆናቸውን ያመለከቱት ኮሚሽነር አብዱልአዚም፤ የሁለቱ ክልሎች ፖሊሶች ለሥራቸው አጋዥ የሆኑ የሎጅስቲክስ በጋራ እየተጠቀሙ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም በመተከል ዞን በኩል ከአማራ ክልል ልዩ ሃይል ጋር ያለው ቅንጅት ዞኑን ወደ መረጋጋት እንዲመጣ እያደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ይኸው ትብብር ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል፡፡
ከሃገር መከለከያ ሠራዊት እስከ ሚሊሻና ሌላውንም የህብረተሰብ ክፍል ያሳተፈ ጥበቃ እና ቁጥጥር መኖሩን አመልክተዋል፡፡
የአሸባሪዎቹ ህወሃትና ሸኔ ተላላኪዎች ወደ ክልሉ የአስተዳደር ወሰን አቋርጠው መግባት የሚሞክር ከሆነ የተለመደውን ቅጣት ያገኛሉ ሲሉ ኮሚሽነር አብዱልአዚም ገልጸዋል፡፡
(ኢ ፕ ድ)

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

ጠመኔ ጥለው ክላሽ የነሱት መምህራን!

Next Story

በደሴ ግንባር የሽብር ቡድኑ ሜይዴይ ክ/ጦር አዛዥ የነበረው ኮሎኔል ጉዕሽ ገብረ ተማርኳል

Go toTop