በአሸባሪው ሸኔ ላይ በተወሰደው እርምጃ እስካሁን 373 የቡድኑ አባላት መደምሰሳቸውን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ። የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በወቅታዊ የክልሉ ሁኔታ ላይ ያተኮረ መግለጫ ለሚዲያዎች ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ መርዳሳ፣ አሸባሪው የሸኔ ቡድን ለኦሮሞ ሕዝብ ደንታ የሌለው እና የአሸባሪው ሕወሓት ተላላኪ ነው ብለዋል። የኦሮሚያ ክልል ሕዝብ ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን የክልሉን ሰላም እያስጠበቀ መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ መርዳሳ፣ መንግሥት በአሸባሪው ቡድን ላይ በወሰደው እርምጃ 373 የሸኔ ቡድን አባላት ተደምስሰዋል ብለዋል።
መንግሥት የተኩስ አቁም ባደረገባቸው ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ አሸባሪው ሸኔ በ210 ሰዎች ላይ ጉዳት ማድረሱን እና ወደ ሁለት ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረትንም እንዳወደመ ኮሚሽነር ጄኔራሉ ገልጸዋል።
የሕወሓት እና የሸኔ የሽብር ቡድኖች ጥምረት ሀገርን ለማፍረስ መሆኑን ተገንዝቦ ሕዝቡ እነዚህ ሁለቱ የጥፋት ቡድኖችን ለማጥፋት ሊታገላቸው እንደሚገባም ጠቁመዋል።
እንደ ኦቢኤን ዘገባ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን የክልሉን ሰላም ለማስጠበቅ እየሠራ መሆኑን እና በዚህም ውጤት እየተገኘ መሆኑን ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ መርዳሳ ገልጸዋል።
የኦሮሞን ሕዝብ ጥቅም እናስከብራለን በሚል በተሳሳተ መንገድ ወደ ሸኔ የሽብር ቡድን የተቀላቀሉ የኦሮሞ ወጣቶች የቡድኑን ሴራ ተገንዝበው በሰላም ወደ ኅብረተሰቡ እንዲቀላቀሉም ጥሪ አቅርበዋል።
መላው ኅብረተሰብም እንደ ከዚህ ቀደሙ ከመንግሥት ጎን በመቆም እነዚህን የሽብር ቡድኖችን እንዳስወገደው ሁሉ አሁንም ድጋፉን አጠናክሮ የክልሉን ሰላም ማስጠበቅ እንደሚጠበቅበትም አስገንዝበዋል።