የሽብር ቡድኑ እድሜአቸው ለውትድርና አገልግሎት ያልደረሱ ሕጻናት እና ሴቶችን ከቀዬአቸው በተሳሳተ የሐሰት ፕሮፖጋንዳ በማስገደድ ለእንግልት እና ለጦርነት እየማገደ መሆኑን የተማረኩ የቡድኑ ታጣቂዎች ገልጸዋል።
ያለምንም ወታደራዊ ስልጠና ወደ አፋር ክልል ሰርገው በመግባት በንጹሐን ዜጎች ላይ ጥፋት ሊያደርሱ ሲሉ በመከላከያ ሠራዊት በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ተናግረዋል።
ሽብርተኛ ቡድኑ አስገድዶ ላሰማራቸው ታጣቂዎቹ ስለ ኢትዮጵያ እና ስለ መከላከያ ሠራዊት የጥላቻ እና የተዛባ ትርክት እንደነገራቸው የገለፁት ምርኮኞቹ ስለሚዋጉበት ዓላማም ኾነ ሌላ ጉዳይ ጥያቄ ማንሳት የማይቻል መሆኑንም ጠቁመዋል።
መከላከያ ሠራዊት በመንግሥት ውሳኔ መሰረት ከትግራይ መውጣቱን ተከትሎ አሸባሪው ትህነግ ወደ ክልሉ በመግባት ሠራዊቱን እንደደመሰሰ በማስመሰል በተሳሳተ መንገድ ለቅስቀሳ መጠቀሙን ገልጸዋል።
ሽብርተኛው ሕወሓት በአሀኑ ወቅት አስገድዶ ላሰማራቸው ታጣቂዎች አንድ መሳሪያ ለስድስት ሰው እያስታጠቀ መሆኑን የተናገሩት ምርኮኞቹ ምንም አይነት የሎጅስቲክ ድጋፍ ማቅረብ የማይችል በመሆኑ ታጣቂዎቹ በርሃብና በእንግልት ምክንያት ምንም አይነት የመዋጋት አቅም እንደሌላቸው እንደገለጹ ከመከላከያ ሠራዊት የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
አሚኮ