በባህርዳር ሰባታሚት ማረሚያ ቤት የሚገኙ የጦር መኮንኖች እና የልዩሃይል አባላት የፃፉት ደብዳቤ
ለክቡር አቶ አገኘሁ ተሻገር ለአብክመ ርዕሰ መስተዳድር
~ለአማራ ብልፅግና ፓርቲ
~ለአብክመ ሠላም እና ደህንነት ቢሮ
~ለአብክመ ልዩ ሀይል አዛዥ
~ለአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን)
~ለአማራ ዴሞክራሴያዊ ሀይል ንቅናቄ (አዴሀን)
ጉዳዩ፦ የህልውና ዘመቻውን እንድንቀላቅለል ስለመጠየቅ
ከላይ በርዕስ ለመግለፅ እንደተሞከረው እኛ በሰኔ 15/2011 ዓ.ም በተፈጠረው ችግር ምክንያት ተጠርጥረን በህግ ቁጥጥር ስር ሆነን ጉዳያችንን በባ/ዳር ማረሚያ ቤት የምንከታተል መሆናችን ይታወቃል።
በዚህ ማመልከቻ የችግሩን አመጣጥ መነሻ ምክንያት፤ የፍትህ አሰጣጡን ሒደት፤ ትክክለኛ ወንጀለኛን የመለየት የማስረጃ ምዘናውን አንስቶ መዘርዘር ብዙ ጥቅም አለው ብለን አናምንም። ሁሉንም ጉዳይ በራሱ ጊዜ እና ሰዓት ገሀድ የሚወጣበት ወቅት ሩቅ አይሆንም። በታሪክም ሁልጊዜ ሳይረሳ የሚኖር ሀቅ መሆኑ አይቀርም።
በመሆኑም እኛ ዛሬ መጠየቅ የፈለግነው እንደሚታወቀው ህውሀት የአማራን ህዝብ ጠላት አድርጎ በመፈረጅ የ 27 ዓመታት የስልጣን መቆናጠጫ ርካብ አድርጎ በመጠቀምና አድማሱን ሀገራዊ አድርጎ ኢትዮጵያን ሲዘርፍ እና ሲመዘብር መቆየቱ የሚታወቅ ነው። በተለይ የመንግስት ጠንካራ ክፍሎች የሚባሉትን የመከላከያ፣ የደህንነት፣ የፋይንንስና ቢሮክራሲውን አሠራር በራሱ መንገድ እንዲመቸው አድርጎ የአጭር እና የረጅም ጊዜ ስትራቴጂ ቀይሶ ከሀገር አልፎ አፍሪካን ዘሎ ወቅቱ የፈጠራቸውን ሀያላን ሀገታትን በመያዝ እና ድንበር ተሻጋሪ ድርጅታቸውን ሰርጎ በመግባት በገንዘብ በእውቀት ወጣት ልጃገረዶችን ጭምር በጋብቻ እና በፍቅር ጭምር በመያዝ ለአደጋ ጊዜ አስፈላጊ ናቸው ብሎ የሚያስባቸውን ተቋማትና ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ግለሰቦችን በመያዝ በአሁኑ ሰዓት በጦር ሜዳ ያልተገኘውን ድል በዲፕሎማሲና ዘመኑ በፈጠረው የመረጃ ዘመን ውጤታማ ስራ በመስራት ላይ ናቸው።
በተመሳሳይ በዓለም ሀገራት ቁጥር ልክ የተመደቡት አምባሳደሮች፤ የወታደራዊ አታሽወች ወዘተ የሀገርን ጥቅም ለማስጠበቅ ተወክለው በሌሎች ሀገሮች የተመደቡ ስፍር ቁጥር የሌላቸው አካላትን ጭምር የህወሀት አጀንዳ የሚያስፈፅሙ መሆናቸው ፤ የቻሉት ፊት ለፊት አጀንዳን ይዘው ሲሟገቱና የሀሰት ፕሮፓጋንዳቸውን ሲያቀጣጥሉ ያልቻሉት ደግሞ የግል ህይወታቸውን እየኖሩ እያወቁ እንዳላወቁ ዝምታን የመረጡ ነገር ግን ደግሞ ያባከኑት ዶላር በአሁኑ ሰዓት በሞት እና በእንግልት የሚሰቃየው የሀገራችን ህዝብ ሀብት እና ንብረቱ መሆኑን የዘነጉ ሆነው ተገኝተዋል።
በዚህ ውጣ ውረድ ውስጥ ሆነን አሁንም የህዝባችን አንድነት እና መተባበር መንፈስ ስንመለከት እውነትም ሀገራችን ጠላት እንደሚያስበው በቀላሉ እንደማትፈርስ መሆኗን እና ተስፋ የሚሰጥ መሆኑን ተረድተናል። ይሁን እንጅ ይህን ሁለንተናዊ ጥቃት ለመመከት ነገሮችን ሁሉ በተለመደው መንገድ በማሰብ እና በመሄድ ለውጥ ይመጣል ብሎ ማሰብ ጅልነት ነው።
አማራ የህግ የበላይነትን ለማክበርና ለማረጋገጥ ህግጋቶችን በማውጣት ብቻ የሚወሰን አይደለም። ለዚህም አንዱ ማሳያ በህግ አምላክ ብሎ ራሱን ሲያስተዳድር የነበረ ህዝብ ነው።
ስለሆነም እኛ በሰኔ 15 ተጠርጥረን የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ በሚል ሽፋን ከሁለት ዓመት በላይ ታፍነንእየተሰቃየን እንገኛለን።
ምንም እንኳን ከሳሻችን የነበረንን የኋላ ታሪክ በሚያቆሽሽ መልኩ ለእኩይ አላማ እንደተሰባሰብን አድርጎ ጥላሸት ቀብቶ ለመወንጀል ቢሞክርም እውነት እና ንጋት እያደር ይጠራል እንደሚባለው በእስር ቤት እየማቀቅን የምንገኝ ሀይሎች በአሁኑ ሰዓት የአማራን ህልውና ፊት ለፊት እየተጋፈጡ የሚገኙትን የአማራ የቁርጥ ቀን ልጅ የሆኑትን ልዩ ሀይሎች የመጀመሪያውን ዙር በጃሪ፣ በቢኮሎ አባይና ብርሸለቆ ስልጠና ሲካሄድ በግንባር ቀደምትነት ያደራጀን እና ያሰለጠን ነን።
ከዚያ በፊትም በመከላከያ ውስጥ የህወሀት ሰወችን ጫና በመቋቋም በራሳችን አቅም በኮማንዶ በአየር ወለድና ግዳጆችን በብቃት በመፈፀም ሳይወዱ በግድ ሲሸልሙን ሲያሞጋግሱን የነበሩት በት ሁኔታም ነበር። ይህም ብቻ ሳይሆን በተለያየ መንገድ አቅማችንን ሲፈታተኑና በተለያየ ጫና ከሰራዊቱ እንድንወጣ እና እንድንበተን ከፍተኛ ጫና ሲያደርጉብን የነበረውን ግፍና መከራ ተቋቁመን በመጨረሻም ክልላችን ጥሪ ሲያደርግልን ግማሾቻችን ከሞቀ ቤታችን፤ እንዲሁም ሌሎቻችን ከምንሰራው ስራ ላይ ፈጥነን በመምጣት በአጭር ጊዜ ባዳ የነበረውን ክልል ለጠላት ፊት መመለሻ የሚሆን አደረጃጀት ለመፍጠር ከፍተኛ ሚና የተወጣን ነበርን። በተመሳሳይ በክልሉ ውስጥ በአራቱም አቅጣጫ ተፈጥሮ የነበረውን ትንኮሳ እና አማራን የማዳከም የጠላት ስትራቴጂ እቅድና እኩይ ተግባር ቀድሞ በመረዳት በማጥናት እና መረጃውን በመተንተን ለውሳኔ ሰጭ አካል ለማድረስ ከፍተኛ የሆነ የመረጃ ስራ ስንሰራ እና በየደረጃው የሚገኘውን የፀጥታ እና የፖለቲካ አመራር እንዲሁም ህዝቡን ጭምር በማንቃት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ህዝብ ላይ የደረሰውን አደጋ ቀድመን መረጃውን ስንሰጥ የነበርን አካላት የዚሁ የሰኔ 15 ክስ ገፈት ቀማሽ በመሆን በእስር ላይ እንገኛለን።
ስለሆነም በአሁኑ ሰዓት ሁለንተናዊ ጥቃት እየፈፀመ የሚገኘውን የህወሀት ሀይል በተለይ በተደራጀ መልኩ ወታደራዊ ብቃት ኖሮት ከሞት የተረፉትን የአሸባሪ ቡድን አባላትን የሚጠብቁና ለተለየ ጥቃት እየተጠቀሙበት የሚገኙትን ልዩ ኮማንዶወች የኛ ጓደኛ የነበሩና በብቃትም ሆነ ውጤታማ ተልዕኮ በመወጣት ከእኛ በታች የነበሩት ልዩ የኮማንዶ አባላት ለጠላት የእግር እሳት ሆነው እየታገሉ እኛ በተድበሰበሰ ክስ በእስር ላይ በመሆናችን የአማራን ህዝብ ከመከራ እና ከተቃጣበት ጥቃት መከላከል እና የድርሻችንን ሚና መጫወት እየቻልን የክሉሉ መንግስት የተፈጠረውን አደጋ ምንነት እየተረዳነው እኛ በማናውቀው ጉዳይ በእስር ቤት በመሆናችን ያለምንም ጥቅም ወይም ህዝባችን ከኛ የሚያገኘውን ወሳኝ እና የማይተካ አስተዋፅኦ ተመዝኖ በሙያችን የክልላችንን ህዝብ ከተጋረጠበት አደጋ መከላከል እንድንችል የክልሉ መንግስት አርቆ በማሰብ መፍትሔሊያስቀምጥልን ይገባል።
በተመሳሳይ በህወሀት ሴራ በተለያየ ምክንያት በመከላከያ ተቋም ውስጥ በውጤታማ ስራቸው የሚታወቁትን ንቁ የአማራ ልጆች ወደ እስር የማገዳቸውና በከፍተኛ ቁጭት ውስጥ የሚገኙትን የመከላከያ ሠራዊት አባላትን ማሳተፍ ቢቻል የሚል ምክረ ሀሳባችንን ጭምር እንገልፃለን።
ለ ሀገር እና ለህዝብ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ ይሰጠው!
አሁንም በህወሀት አስተሳሰብ ከተጫነን የሴራ ፖለቲካ እንውጣ !
ለህዝባችን እንድረስ !
አመልካቾች፦
1 ኮ/ል ፈንታው ሙሀቤ
2 ኮ/ል ሞገስ ዘገየ
3 ሻ/ቃ አዱኛ ወርቁ
4 ሻ/ል ውለታው አባተ
5 ሻ/ል ታደሰ እሸቴ
6 ሃምሳ/አ በላቸው ዘውዴ
7 ሃምሳ/አ አበበ መልኬ
8 አቶ የማነ ታደሰ
9 አቶ ስለሺ ከበደ
10 ሃምሳ/አ አሰፋ ጌታቸው
11 ሃምሳ/አ አየነው ታደሰ
12 ሳጅን መልካሙ ባለሟል
13 ፲/አ ሙሉጌታ ፀጋየ
14 ፲/አ አያልነህ ገዛኸኝ
15 ወ/ር ብርሃኑ ይደጉ
16 ፲/አ ፈንታሁን እንድሪስ
17 ሃምሳ/አ አሊ ሀሰን
18 ሃምሳ/አ ሲሳይ ገላነው
19 ፲/አ ፈቃዱ ምትኩ
20 ፲/አ በለጠ ወርቁ
21 ፲/አ አሸናፊ ዳኘ
22 ፲/አ ይመር እሸቴ
23 ፲/አ እሸቴ ስዩም
24 ፲/አ ምስጋናው ገነት
25 ፲/አ አባተ ብዙአየሁ
26 ፲/አ መንግስቱ መኩሪያ
27 ፲/አ መለስ መብራቱ
28 ፲/አ ጥጋቡ ለገሰ
29 ፲/አ አሊ ኢብራሂም
30 ፲/አ መንግስቱ እያሱ
31 ሃምሳ/አ ልመንህ የኔሰው
32 ፲/አ ጉልሽ ደምሳሽ
ስንሆን በትህትና እንጠይቃለን።