ጦርነቱ፣ ከተቀሰቀሰ ጀምሮ በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም ዐቀፉ ማኀበረሰብ (በተለይ በምዕራባውያኑ) ዘንድ ከፌደራሉ ይልቅ፤ በዐማራ እና ኤርትራ የሚመራ ለማስመሰል ሲሞከር ቆይቷል። አንዳንድ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ዲፕሎማቶችም ሳይቀሩ፣ ይህ የተሳሳተ አረዳድ እንዲታረም የረባ አስተዋጽኦ ባለማድረግ ሲለግሙ ታዝበናል። በተለይ ከአገር ውጭ ያሉ የተወሰኑ ዲፕሎማቶች፣ በዝግ የጠረጴዛ ውይይቶች ላይ የዐማራ ልዩ ኃይል እና የኤርትራ ሠራዊትን ከፌደራል መንግሥቱ ዐቅም በላይ አድርገው መወንጀላቸውን የሾለኩ መረጃዎች ያስረግጣሉ።
የሆነ ሆኖ፣ ሕወሓት ጥቅምት 24 በመከላከያ ሠራዊቱ እና በዐማራ ክልል ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ፣ የጦር ኃይሎች አዛዥነትንና ጠቅላይ ሚንስትርነትን የደረቡት ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የሕግ ማስከበር ርምጃ እንዲወሰድ ትዕዛዝ መስጠታቸው ቢታወቅም፤ ዛሬ ይህ እውነታ ተቀይሯል። ከቅያሪውም ጋር ጉዳዩ የሁለቱ ክልሎች ግጭት ብቻ እንዲመስል እየተሴረ ነው። ይሁንና የትኛውም አካል መገንዘብ ያለበት ቁም-ነገር፣ የተፈጠረው ችግር በዚህ መንገድ ፈጽሞ የሚፈታ አለመሆኑን ነው። ከዚህ ባለፈ፣ ዓለም ዐቀፉ ማኀበረሰብም ሆነ ሚዲያው ትክክለኛውን ነገር እንዲረዳ ኃላፊነትን በበቂ ካለመወጣት አኳያ፣ ከፌደራሉ በተጨማሪ፤ የዐማራ ክልል አስተዳደሮችም ተጠያቂ እንደሚሆኑ መዘንጋት የለባቸውም።
በሌላ በኩል፣ ሠራዊቱ ከትግራይ መውጣቱን በተመለከተ ጠቅላይ ሚንስትሩ ጋዜጠኞችን ሰብስበው በሰጡት ማብራሪያ፣ ቢያንስ ሦስት ኃይሎች በቅንጅት የተሳተፉበትን ጦርነት፣ “የዐማራ ሕዝብ አገር ለመጠበቅ አያንስም” በሚል ሽንገላ፣ ጉዳዩን ለክልሉ አስተዳደር ብቻ ወደመተው ማዘመማቸው ግዘፍ-የሚነሱ በርካታ ችግሮች እንዲፈጠሩ ገፊ-ምክንያት መሆኑ አይቀሬ ነው። እዚህ ጋ ሳይጠቀስ የማይታለፈው ሌላው ደረቅ ሀቅ፣ ከኢትዮጵያ ሠራዊት እና ከዐማራ ልዩ ኃይል በተጨማሪ፤ የኤርትራ ወታደሮች እና የትግራይ ቁስለኞች የህክምና እርዳታ ሲያገኙ የነበረው በጎንደር እና ወልዲያ ሆስፒታሎች ቢሆንም፤ ከፌደራል መንግሥቱ የተደረገ ድጋፍ ስለመኖሩ አለመሰማቱ ነው።
መከላከያ ትግራይን ከለቀቀ በኋላ ደግሞ፣ ዐማራ ክልል፣ ወጣቶችን በገፍ ለመመልመል እና ለሚሊሻ ጥሪ ለማድረግ ተገድዷል። ለጦርነት የሚሆን ኃይል ማደራጀት እጅግ ከፍተኛ በጀት የሚጠይቅ መሆኑ አያከራክርም። ምክንያቱም ተዋጊው ቢያንስ ምግብ፣ ውሃ እና ወባን ጨምሮ፤ የተለያዩ ተላላፊ በሽታዎችን የመከላከያ መድሃኒት አቅርቦት ይፈልጋል። ከዚህ በተጨማሪ፣ በጦርነቱ ሂደት የአጭር ጊዜ እና የረዥም ጊዜ ጉዳቶች ማጋጠማቸው ተገማች ነው። የአጭር ጊዜው፣ በዋናነት የቆሰሉ ተዋጊዎች ሊያገኙ ከሚገባው ህክምና ጋር የተያያዘ ሲሆን፤ የረዥም ጊዜው፣ ለውጊያው የተጠራው አብዛኛው አርሶ ዐደር በመሆኑ፣ ከምርት መቀነስ አኳያ ትልቅ ክፍተት ሊፈጠረ መቻሉ ነው። ይህ ደግሞ አገር ለመታደግ የተሰለፉትን አርበኞች ቤተሰብ ከመበተኑ በዘለለ፤ በክልሉ ላይ ችጋር እንዲከሰት መግፍኤ ሊሆን ይችላል።
“ፍትሕ መጽሔት” እነዚህ ተዋጊዎች እንዲዘምቱ ጥሪ የተደረገላቸው ኢትዮጵያን እና የፌደራል መንግሥቱን ከጥቃት ለመከላከል በመሆኑ፤ መከላከያ ሠራዊቱ ሊያገኝ የሚገባውን ጥቅማ ጥቅም (ጡረታን ጨምሮ) እንዲያገኙ ማደረጉ ምክንያታዊ ነው ብላ ታምናለች።
እስከ አሁን ባለው ሂደት፣ የፌደራል መንግሥቱ ለትግራይ ከመደበኛ በጀቱ ስምንት እጥፍ እንደመደበ ቢናገርም፤ ወልቃይት-ጠገዴ፣ ጠለምት እና ራያን አለማከተቱ ይታወቃል። እነዚህን አካባቢዎች ለማስተዳደር ዐማራ ክልል ከራሱ በጀት ቀንሶ መሆኑ ደግሞ፣ ከባድ ኪሳራ የማድረሱን አይቀሬነት ለመረዳት የኦዲት ሪፖርት ማዳመጠን አይጠይቅም።
በአጠቃላይ፣ የፌደራል መንግሥቱ፣ የዐማራ ክልል ከሕወሓትም ሆነ ከሱዳን ጋር የተጋፈጠውን ጦርነት ለመመከት የሚወጡ ወጪዎችን እና ሌሎች የሚመለከቱትን ግዴታዎቹን እንዲወጣ የማድረጉ ኃላፊነት የሁሉም እንደሆነ መዘንጋት የለበትም። በተለይ በክልሉም ሆነ በፌደራል የተመደቡ የብሔሩ ተወላጅ ባለሥልጣናት እንደ እስከ ዛሬው በአድርባይነትና በፍርሃት፣ ጉዳዩ በዐማራ ክልል ላይ ብቻ እንዲጫን ፍቅደው ከቀጠሉ ግን፣ በሕግም ሆነ በታሪክ ሊጠየቁ የሚችሉበት ጊዜ እንደሚመጣ ልብ ሊሉት ይገባል።
ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም!
@ፍትህ መጽሔት