እንዳንዘናጋ (ዘ-ጌርሣም)

May 22, 2021

እንጠብቅ በራችን
እንሙላ ውኃችን
የአባይን ተፋሰስ
ዙሪያውን በማሰስ
ኬላችን እንዝጋ
ጠላት የለም ብለን
በጊዜው ተታለን
አደጋን በማቅለል እንዳንዘናጋ
በህብረት እንመክት መጭውን አደጋ
የእባብ ጭንቅላቱ
መሬት ውስጥ መግባቱ
መርዙን እየተፋ
ባይታይ በይፋ
እንደገና አድብቶ
እኛን አዘናግቶ
ኃይሉን አጎልብቶ
በሌሎች ተረድቶ
ብቅ ማለቱ አይቀርም
ጊዜው ውሎ ቢያድርም
ሲመታ መልፈስፈስ
ሲተውት በመንከስ
ሲሽነፍ ሰላምን
ጊዜ አድብቶ ጠብን
ደጋግሞ አሳይቷል
ለአንዴም ዘንጋ ሳንል
ያለማወላወል
ይገባል መጠበቅ
ቀድመን በመጠንቀቅ
ሞቶ አገር ማዳንን ያውቃል ያገሬ ሰው
ወዳጅ ብቻ ሳይሆን ጠላት ምስክር ነው
እናስታውስ አድዋን
እናስታውስ ማይጨውን
እንዘክር ወልወልን
እናስብ መተማን
የቅርቡን ወረራ
ጀግኖች ያፈራውን በተራ በተራ
ምስክር ነውና ሐረር ካራማራ
የእንኛ መታወቂያ ዓለም ያደነቀው
የመጣውን ጠላት ድባቅ የመታነው
በመልክ ስብጥር
ጥርስና ከናፍር
እንደ ጠንካራ ቤት ጨፈቃና ማገር
ሆነን በመቆም ነው
ሀገር አስከብረን በጋራ የኖርነው
የመጣ ቢመጣ ከቶ እማንበገር
በአገራቸን ጉዳይ የማንደራደር
ስለሆን እኮ ነው
የደፈረን ሁሉ አጉራ ጠናኝ ያለው
እንኳንስ ዛሬና ጀግና ኃይል እያለን
የምድር የየብሱ መከላከያቸን
እራሱ እየሞተ እኛን ጠባቂያችን
ቀደምት ተመስክሯል ያባቶቻችን ጀብድ
በቁሙ ሲያዝሉት የጠላታችን ክንድ
የሉሄ እያሰኙ በፍርሃት ሲርድ
እያርበተበቱ አገር ለቆ እስኪሄድ
እኛም በድርሻችን ካለፈው ተምረን
በአንድ ላይ በመቆም ዘብ መሆን አለብን
አደጋን በማቅለል እንዳንዘናጋ
በህብረት እንመክት መጭውን አደጋ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

ለምን ይመስልሻል? – ገጣሚ: በላይ በቀለ ወያ

ethnic
Next Story

ኢትዮጵያና ጎሳነት (በአልማዝ አሰፋ – ዘረ ሰው)

Go toTop