ይድረስ ለሻለቃ ዳዊት – ሰለሞን ሥዩም ሲያትል፣ ዋሽንግተን

የሻለቃ ዳዊት አስተያየት በጣም ያሳዝናል። ብዙ ልምድ፣ ረዥም ዕድሜ፣ እና የውትድርና ብቃት ያላቸው ሻለቃ ዳዊት በዚህ ሀገር በውስጥና በውጪ ጠላት በተከበበችበት፣ የሰዉ ስሜት በጦዞበት ክፉ ጊዜ፣ የሰከነ አስተያየት ይዘው የሚያረጋጋ የሚያበረታታ በሳል ሀሳብ ይዘዉ ኢትዮጵያ በድል አድራጊነት ፈተናዋን በምትወጣበት መንገድ ላይ ይናገራሉ ብዬ ስጠብቅ መሬት የሚነቀንቅ ሰልፍ አድርጉ፣ አማራ፣ ጉራጌ እና ኦርቶዶክስ ለአመጽ ተነሱ ብለዉ መጡ። ይባስ ብለዉ፣ እንዴት አርጎ አማራና ኦሮሞ አብሮ ይኖራል፣ እንዴት አርጎ አማራና ትግሬ አብሮ ይኖራል፣ ብለዉ በመጠየቅ አብሮ ተደጋግፎ የሚኖረውን ህዝብ የማጋጨት ፍላጎት ያለው የሚመስል ጥሪ አደረጉ። የችግር ትንተናቸዉም ላይ አፍራሽ ሚና በመጫወት ተጠያቂ ያደረጉት 1ኛ አቢይን ሲሆን 2ኛ ህዝቡን፣ ዝም ብሎ የሚያጨበጭበውን እርሳቸዉ እንደሚሉት። ኃላፊነት የጎደለው፣ ሀገር የሚያሳጣ እና ህዝብን ከህዝብ የሚያጫርስ ከፋፋይ አስተያየት ነው።

https://youtu.be/2X2UIvv6JAc

ከኢትዮጵያ መንግስት ይልቅ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለጣሉት ለአሜሪካ እና ለግብጽ በጎ አስተያየት አላቸው። ሁለቱም ኢትዮጵያ እንድትፈርስ አለመፈለጋቸዉን ይነግሩናል። አንድም ጊዜ ለዚህ ሁሉ አበሳ ኢትዮጵያን ያበቃዉን ወያኔን ሲያወግዙ አልተደመጠም። የሱዳንንም ሆነ የግብጽን ቀጥታ እና እጅ አዙር ጫና (እንደምንሰማው አስታጥቆ ተዋጊ እስከማሰረግ የደረሱትን) ሲያወግዙ አልተሰማም። የኦሮሞ ጽንፈኛ ኮርማዎች ከውስጥ እና ከውጪ ሀይሎች ጋር ሆነው የተያያዙትን በጭካኔ የተሞላ ዘግናኝ ቅስቀሳ እና ጭፍጨፋ አላነሱም።

መንግስት ፋታ አጥቶ ጥርሱን ነክሶ በተለያየ ግንባር ፍልሚያ በገጠመበት በዚህ ወሳኝ ሰዓት እርሱን አፍርሶ እርሳቸው አዘጋጅቼላችኋለሁ የሚሉት “ካውንስል” መኖሩን ያስረዱናል። ከመንግሥት ጋር የቆመዉ ከሀዲ ነው ይላሉ። የሚያስደንቅ ነው። ምን አጀንዳ ቢይዙ ነው ሻለቃ እንዲህ በርቀት ሄደዉ መስመር የለቀቁት? ይሄ ንግግራቸዉ ልዩነታቸውን እና ህመማቸውን በጉያቸው ይዘው “ተነስ፣ ታጠቅ፣ ዝመት” ጥሪ ተቀብለዉ ዛሬም እንደትላንቱ ዉድ የህይወት ዋጋ ከፍለዉ ኢትዮጵያን ከአደጋ በመታገድ ላይ ላሉት የመከላከያው እና የሚሊሻውን ወገኖቻችንን መስዋዕትነት ማርከስ መሆኑስ እንዴት አልታያቸዉ አለ? እኚህ ሰዉ በወታደሩ ቤት ዉስጥ አድገው ከፍተኛ ቦታ የደረሱ ሰው በመሆናቸው ከሌላዉ ሰዉ በተሻለ የችግሩንና የመስዋእትነቱን ክብደት ይረዳሉ ተብሎ ስለሚገመት ከርሳቸዉ የምንጠብቀው ሀሳብ ምንም ያህል ቢጎረብጥ እንኳን በዚህ ደረጃ የወረደ ይሆናል ብሎ መገመት ፈጽሞ አይቻልም ነበር።።

በአብዛኛዉ አማራውን ታርጌት ያደረገዉ ይህ ሁሉ እልቂት አንዴ በኦሮሞ ጽንፈኛ፣ ሌላ ጊዜ በወያኔ፣ ከዚያም ሲተርፉ የጉሙዙ ሽፍታ ቀዮቹ እያለ እየተፈራረቁ የሚጨፈጭፉበት የጭካኔያቸዉ ምስጢር የኢትዮጵያን መንግሥት የማፍረስ አላማ ያለው መሆኑን ጀማሪ የህግ ተማሪም ሆነ ፓለቲከኛ ሊረዳዉ እየቻለ ሻለቃ በእዉነት መገንዘብ አቅቷቸው ነው ወይንስ ሳይፈልጉ ቀርተው? በምን ምክንያት? ከጥቂት አመታት በፊት አዲስ እበባ በተዘጋጀዉ የቪዥን ኢትዮጵያ ፕሮግራም ላይ የኢትዮጵያን አንድነት ለመጠበቅ ሲባል ጠ/ሚሩ ሕገ መንግሥቱን ቸል ብለዉ ፓርላማዉን በትነዉ በኃይል እንዲገዙ መክረዉ እንደነበረ ይታወሳል። ከምክርም ባለፈ ጠ/ሚሩ ይህንን ማድረግ ካልቻሉ ከሀገር ስለማይበልጡ ለሚችል ሰዉ ቦታ እንዲለቁ አሳስበዉ ነበር። ከዚህ ሁሉ በሁዋላ ለምን ጠ/ሚሩ አግኝቶ አላነጋገረኝም ማለታቸዉ ግራ ያጋባል። ሻለቃ የሚሉትን ብለዉ ጨርሰዉ ነበር።

ከዚያ ጊዜ የጀመረ በተለያየ መድረክ ላይ እየቀረቡ ብዙ ማብራሪያ ሰጥተዋል። መንግሥትን በማብጠለጠል በተካኑት በርእዮት ሚዲያ፣ በኢትዮ ፫፷ እና በተወስነ ደረጃ በአባይ ሚዲያ ላይ መደበኛ ተጋባዥ እንግዳ እየሆኑ በመቅረብ በመንግሥት ላይ የሰላ ትችት ሲያቀርቡ መቆየታቸዉ ይታወቃል። ይሄ ግን ችግር አልነበረዉም። ችግሩ ከርሳቸዉ በሚጠበቅ ደረጃ ኢትዮጵያ የነበረችበትን ፈተና አለመረዳቱ ላይ ነዉ። ጠ/ሚሩ እንኳን ሀገር ቤተስባቸዉን ለማስተዳደር ምን ያህል ሲቸገሩ እንደነበረ በቅርብ ጊዜ አስረድተዉ ነበር። ወያኔ ባዶ ካዝና ባዶ ሀገር ትቶላቸዉ ነዉ ሄዶ የመሸገዉ። በሰሜን እዝ የሚገኘዉ ጠንካራዉ የሀገሪቱ መከላከያ ኃይል የታገተ በሚመስል ደረጃ እንዳይነቃነቅ ተደርጎ መቶ በመቶ አመራሩ በወያኔ ሰዎች እንደተያዘ ነዉ። ጥ/ሚሩ በምስጢር ጭምር ነበር የሀገሪቱን መከላከያ እያዋቀሩ የነበሩት። ወያኔ በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ሲከፍት ገና ተጨማሪ የዝግጅት ጊዜ ያስፈልጋቸዉ እንደነበር ያስረዱት የሚታመን ነዉ። በአደባባይ ባቀረቡት የስታትስቲክስ መረጃ መሰረት ከሰሜኑ እዝ ዉጪ የኮማንድ ፖስት እና የሜካናይዝድ ባታሊዮን አመራር መቶ በመቶ ለወያኔ ታማኝ በሆኑ አባላቱ እጅ እንደነበረ አሳይተዉ ነበር። ከዚያም ዉጪ ከመከላከያዉ ዋና መ/ቤት (ሄድ ኳርተር) ጀምሮ በተለያዩ ክፍሎች ዉስጥ እስከ ሰማንያ አምስት በመቶ ድረስ ቁልፍ የኃላፊነት ቦታዎች የተያዙት በሚታመኑት የወያኔ ሹማምንት መሆኑ ተዘግቧል። በዚህ ሁኔታ ዉስጥ የሻለቃ ምክር ውሃ የሚያነሳ ሊሆን አይችልም። ማንን የዘዉ ነዉ በጉልበት የሚገዙት፧ ስብጥሩ ኢትዮጵያን የመሰለ እምነት ሊጣልበት የሚችል የሀገር መከላከያ አልነበረም። ለዚህም በቂ መረጃ የሚሆነዉ ህወሀት አብሮ የኖረዉን የሰሜን እዝ ባልደረቦቹን በሌሊት ከቦ መረሸኑ ነዉ። ሻለቃ በፊት

አልገባቸዉም ነበር ቢባል እንኳን አሁን ይሄንን ሁሉ ካዪ በኋላ እንዴት መመለስ እንዳቃታቸዉ የሚያዉቁት እርሳቸዉ ብቻ ናቸዉ።

ሌላዉ ሊሰመርበት የሚገባዉ ነገር ይሄ ሁሉ እልቂት የሚደርሰዉ መንግሥት የገዛ ህዝቡን መጨፍጨፍ ፈቅዶ ነው የሚል አንድምታ ያለዉ የተዛባዉ አረዳድ ነዉ። እንዲህ ማለቱ ህዝቡን ለመታደግ ውድ የህይወት ዋጋ የሚከፍሉትን የመከላከያ እና የሚሊሺያ አባላት ክብር የሚያጎድፍ አሳዛኝ አስተያየት ነዉ።

ከጋዜጠኛ አበበ ጋር በነበራቸዉ በዚህ ቆይታቸዉ ሻለቃ በወያኔ፣ በኦሮሞ ጽንፈኛ፣ በግብጽ፣ በሱዳን፣ ወይንም ጫናቸው በበረታው ምዕራባውያን ላይ ሳይሆን የክስ መዝገባቸዉን እያዘጋጁ ያሉት የኢትዮጵያን መንግሥት ህግ ፊት ለማቆም መሆኑን ነው የሚገልጹልን። የተሰሩ ወንጀሎችን አጣርቶ ፍትህ መጠየቅ በማንኛውም ጊዜ የተገባ ነው ብቻ ሳይሆን መቅረት የለበትም። ግን ለኢትዮጵያ ይሄ ሰዓቱ አይመስለኝም። የግድቡ ሙሊት እና ምርጫው ከመድረሱ በፊት የውስጥ እና የውጪ ጠላቶች ግንባር ፈጥረው ግልጽ ጦርነት በገጠሙበት በዚህ የሞት ሽረት ሰዓት ከነችግሩ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር መቆም አለመቻላቸዉ ግራ የሚያጋባ ነው። በዚህ ወሳኝ ገዜ እምቢተኛ ሁኑ ብሎ ወጣቱን መቀስቀስስ እንደ ክህደት አይቆጠርም? ያዉም ከወታደር? በእኛ ዕድሜ እንኳን የምናዉቀዉ የኢትዮጵያ የቁርጥ ጊዜ ታሪክስ እንዲህ ያለዉን ክህደት ይፈቅዳል?

ጋዜጠኛው አበበም ሻለቃ ያዘጋጁልን “ካውንስል” ምን እንደሆነ መጠየቅ ስለሚገባዉ ይሄንን አጣርቶ እንደሚያመጣልን ተስፋ አደርጋለሁ። ነገር ግን አበበ በዩቲዩብ ላይ የጫነዉን ቪዲዮ “ሻለቃ ዳዊት ውልደጊዮርጊስ ሃቁን አፈረጡት” ከሚለዉ፣ “ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ በሀቅ ፈረጡ” ቢለን ለእዉነት የቀረበ ይሆን ነበር። ስለቃላት ምርጫዬ ትልቅ ይቅርታ እጠይቃለሁ። በአበበ በኩል ፕሮግራሙ ሲጀመርም ሆነ በየመሀሉ የሰልፉን ቪዲዮ እያስገባ፣ የሺመልስን አፍ እላፊ እያቀረበ፣ መንግስትን መኮነን እና ከፋፋይ መልዕክቶችም መደጋገማቸዉ አስፈላጊ የነበረ አይመስለኝም። ጉዳት አለዉ። እንዲህ ያለዉ አቀራረብ በዚህ ቁርጥ ሰዓት የስሜታዊዉን ወጣት ስነልቡና ሰልቦ ትጥቅ ከማስፈታት እና ሀገሪቱን ከመጉዳት ያለፈ ፋይዳ የለዉም። በአማራው ወገናችን ላይ አላባራ ብሎ በተደጋጋሚ የሚደርሰው ጭፍጨፋ ምስጢሩ በርግጥ የአማራ ጥላቻ ነው ወይንስ ይህንን ክቡር ህዝብ አስቆጥቶ ከወገኑ በማባላት መንግሥትን ከተቻለ ለመጣል እና በካዉንስሉ መተካት፣ ካልሆነ በድርድር (በምርጫ ሳይሆን) ቦታ ለመያዝ የሚፈልጉት ሀይሎች ሴራ ነው? ይሄ ቡድን ህወሀትን እና ደጋፊዎቹን፣ የኦሮሞ ጽንፈኞችንን (ምናልባትም የሀይማኖት አጀንዳም የያዙትን ይጨምራል) እና የግድቡን ሥራ ማስተጓጎል የሚፈልጉትን አጥፊ የዉጪ ሀይሎች አንድ ላይ አምጥቷል። ይሄ በዉይይቱ አልተነሳም። ከነዚህ ባላነሰ ሁኔታ በየደረጃው ባሉ የመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ ተሰግስገው የተሳካ ምርጫ ከተደረገ ቦታ የለንም በሚል ስጋት ከእኩይ ቡድኖች ጋር የተሰለፉት ደካማ ኃይሎችም ለመንግሥት ተጨማሪ ፈተና መሆናቸውም ፈጽሞ አልተነሳም።

ሻለቃም ሆነ አበበ ይህንን የተዛባ አስተያየት እና ያልተገባ ቅስቀሳ አስተካክለው ሚዛናዊ ዘገባ እንዲያቀርቡ በአክብሮት እጠይቃለሁ።

ሰለሞን ሥዩም
ሲያትል፣ ዋሽንግተን

https://zehabesha.info/amharic/archives/116782

 

https://amharic.thehabesha.com/explainer-why-ethiopias-federal-system-is-deeply-flawed/

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

የምርጫ ህጉን፣ የምርጫ ዘመቻ መመሪያን የሚተላለፉ ንግግሮችን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ መግለጫ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ 6ኛው ብሔራዊ ምርጫ ሂደትን በተመለከተና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያስተላለፉት መልዕክት
Next Story

ለመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማን ምክር ጠየቃቸው? – መርሐጽድቅ መኮንን አባይነህ

Go toTop