ይሰጣታል ቢያንስም (ዘ-ጌርሣም)

September 7, 2020

ገና ጎህ ሳይቀድ በጥዋት ተነስታ
የምታድነውን ከወዲሁ አስልታ
የበሬውን እንትን መከተል መረጠች
ተስፋዋን ሰንቃ መኳተን ጀመረች

ዓይን ዓይኑን በማየት ስትባዝን ውላ
ከአሁን ወደቀልኝ ተስፋዋንም አዝላ
በውሃ ጥም ድካም ጉልበቷ ተጠቅቶ
ከንቱ ደክማ ሄደች ምኞቷ ተረቶ
ጉልበታሙ አንበሳ ሲቀናው ስላየች
በደካማነቷ የምር ተፀፀተች

ችግሯን ተረድቶ መዋሏን ስትደክም
ለሷ ያሰበውን መቸም አይነሳትም
እንደሰው አይደለም አምላክ ቸል አይልም
የማታ የማታ ይሰጣታል ቢያንስም

ለማይገኝ ነገር ከንቱ ከመጃጃል
ባገኙት ረክቶ መኖሩ ይበጃል
የጎደለ ካለ ጊዜን መጠበቅ ነው
አንድም ነገር የለም ለሱ የሚሳነው

ጊዜ እንደ ፈረስ ነው ያደርሳል ካሰቡት
ቁስሉ ተሎ አይድንም ከጣለ የኋሊት
ፈርስ ለመጋለብ ህግና ደንብ አለው
መሟላት ሲችል ነው ኮርቻና ዛቢያው
ጊዜን ያለአግባብ ልጠቀም ለሚሉ
ካሰቡት ሳይደርሱ መንገድ ይቀራሉ

ምስኪኗ ቀበሮ ስትባዝን ውላ
ሄደች ተመልሳ በድካም ነሁልላ
ምኞትና ተስፋ ተራራ ሲወጡ
አይቀሬ ጉዳይ ነው መውደቅ መላላጡ
ያሰቡትን ነገር ከግቡ ለማድረስ
ትንፋሽን ዋጥ አርጎ ይገባል መታገስ
እንደሰው አይደለም አምላክ ቸል አይልም
የማታ የማታ ይሰጣታል ቢያንስም

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

የተመኙትን ሲኦል ልከናቸው እንመጣለን ጀነራል ብርሀኑ ጁላ የሰጡት ጠንከር ያለ መግለጫ

Next Story

ጠ/ሚ አብይ ትራፊክ መስሎ የእንኳን አደረሳችሁ ፖስት ካርዶችን በሸገር ጎዳናዎች ሰጠ

Go toTop