ለኢትዮጵያ ሕዝቦች የውይይት መድረክ – ጆቢር ሔይኢ ከሁስተን ቴክሳስ

የእግዚአብሔር ቃል፣”ሰላምን የሚያወርዱ ብፁዓን ናቸው የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው ይጠራሉና።ምሕረትን የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው፣ምሕረትን ያገኛሉና”ይላል።ይህን የአምላካችንን ቃልና ፈቃድ ተከትለን እውነተኛ ዕርቅ ለመፈጸም፣እኛም እውነቱን በግልፅ መነጋገር ይገባናል።

ኢትዮጵያ አገራችን የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች አገር ናት፡፡ የብሔር፣ የብሔረሰብና የሕዝቦችን መብት ደግሞ  በእኩልነት መከበር አለበት። ይህም የሰው ልጆች ሁሉ የእኩልነት መብት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተር የተደነገገ፣ በአባል አገሮች ፊርማ የጸደቀ ነው። በዚሁ ድንጋጌ መሠረት ነው፣በዙዎች አገሮች ከቅኝ ግዛት ነጻ የወጡት፡፡

አገራችን  ይህን ድንጋጌ ፈርማ የተቀበለች አገር ናት።ስለዚህ ሕዝባችን ከእንግዲህ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ላማስከበር ሲሉ ትጥቅ አንግበው በረሓ ለበረሓ ሊንከራተቱ አይገባም።

እስከ እሁን በአገራችን  የሰፈነው ሁኔታ ሲታይ፣ ሁላችንም የምንወደው ራሳችንን፣ ቋንቋችንን፣ ባኅላችንን፣ ታሪካችንን፣ እምነታችንን ፣ጥቅማችንን በአጠቃላይም የኔ የሚንለውን ሁሉ ነው። ከሌላውም የምንሻውም  ሰው ሁሉ፣ዓይኑን ጨፍኖ፣ የራሱ የሆነውን ሁሉ ንቆ፣ ለእኛ ብቻ የሚጠቅመውን መርጦ፣በማድነቅ እንዲያጅበን ነው።

የፌድራሊዝም ሥርዓት ለአገራችን ያስፈለገውም፣ በሕዝቦች መካከል ሥር ሰዶ የቆየውን የብሔር ጭቆና በማስወገድ፤ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አንድነትና ሰላምን ለማስፈን ነበር።ይህ ነበር የቀደመው የኢሕአዴግ ዓላማ።ለወደፊቱም ቢሆን ከኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል ቅራኔዎች ተወግደው ፍቅር፣ ስላምና ኅብረት እንዲሰፍን ከፈለገን፣ከራስ ወዳድነት ተላቀን፣   የጭቆና ፈርጆችን ሁሉ በጋራ መታገል ይገባናል።

በዚህም ረገድ፣ ከንድ መቶ በላይ የሆኑ  የፖለቲካና የብሔር ድርጅቶች ተስባስበው በተወዳዳሪ ፓርቲነት ለመደራጀት ተዘጋጅተዋል። የኢሕአዴግ አባላትም ለሁለት ተከፍለው በሥልጣን ሽሚያ ውስጥ ገብተዋል።ከዚሁ የተነሳ ሕዝባችንም በሦስት ጎራ ተሰልፏል።ይህም  የመደመር ጎራ፣ የሕገ መንግሥትና የፌድራሊዝም ጎራና፤የአሐዳዊ መንግሥት ጎራ ናቸው።

በዚህ ላይ የብልፅግና ፓርቲ አንዳንዴ ከአሐዳዊያን ጋር  ሲደመር፣በሌላ ጊዜ የብሔር ጥያቄን በመመለስ ከፌድራል ኃይሎች ጎን  ሲቆም ይታያል።በምርጫ ረገድም አሁን ይደረግ በሚሉትና፣ የኮቪድ በሽታ ሥጋት ከተወገደ በኋላ ይደረግ በሚሉት መካከል ልዩነት ተከስቷል።ይህ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሥልጣን ጥያቄ ነው።ምርጫው ዘግይቶም፣ድርጅታዊ አሠራር ቀርቶ ሕዝቡ የሚፈቅደውን ተወዳዳሪ በነጻነት ለመምርጥ ከቻለ እጅግ ጥሩ ነው።

ስለሆነም ይህንና መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ ያለን ምርጫ አንድ ነው፣ይኸውም ከአሓዳዊያን ጎን በመሰለፍ የብሔር ጭቆና እንዲቀጥል መፍቀድ፤ ወይንም ደግሞ ከፌድራሊስት ኃይል ጋር በመቆም፣  የጭቆና ፈርጆችን ሁሉ ማስወገድ ይሆናል።

ለዚህም ጎራ በመለየትና  የጠራ አቋም ይኖረን ዘንድ፣ በቋንቋ አጠቃቀም ላይ ግልጽ ውይይት ማድረግ ይገባናል።     ይህም፦          ሀ/ የኢትዮጵያ ፌድራል ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ መንግሥት የትምሕርት፣ የምርምርና የሥራ ቋንቋ እንግሊዘኛ እንዲሆን በመፈቅድ የቋንቋ አድሎንና ልዩነትን ማስወገድ፣

ለ/ እንግሊዝኛ ቋንቋ ለማይችሉት፣ በአማርኛ፣ በአፋንኦሮሞ፣ በትግርኛ፣በፈረንሳይኛና በአረቢኛ የትርጉም አገልግሎት መስጠት፣   ሐ/ብሔራዊ መስተዳድሮች፣የክልል መስተዳድሮች፣ብሔራዊ ዞኖችና ብሔራዊ ወረዳዎች በክልላቸው በመረጡት ቋንቋ የመጠቀም  መብት ማረጋገጥ፣

መ/ ሰው ሁሉ በሕግ ፊት እኩል በመሆኑ፣ከብሔሩ፣ ከቋንቋው፣ ከጾታና ከእምነት የተነሳ ልዩነት እንዳይደረግበት ሕገ መንግሥዊ ጥበቃ  መስጠት፣

ሠ/ የየክልሉን ቋንቋ ለማያውቁ ነዋሪዎች፣በመንግሥታዊ ተቋሟት ሁሉ፣ነጻ የትርጉም አገልግሎት መስጠትን የሚያጠቃልል ሊሆን ይገባዋል።

መደበኛ ትምህርትን በሚመለከት፣የአንደኛና የሁለተኛ ደርጃ ትምሕርት ቤቶችና ኮሌጆች፣እንዲሁም የግል የትምሕርት ተቋሟት በሙሉ በክልል አስተዳደር ስር መዋል ይገባቸዋል። ከፍተኛ የትምሕርት ተቋሞች  ፈተና የማውጣትና ተማሪ የመመልመል፣ መብታቸው ሰፍቶ በትምሕርት ሚኒስቴር አስተዳደር ስር ሊውሉ ይገባል።

ሕገ መንግሥትን በሚመለከት፤ማንም ቢሆን  በአንድ ጊዜ የጠራ  ሕገ መንግሥት የቀረጸ አገር የለም።ነባራዊ ሁኔታ ሲለወጥ ሕግ መንግሥቱም ከሁነታው ጋር መጣጣም ይኖርበታል።ስለዚህም በቅድሚያ  ሕዝባችን በክልሉ የራሱን ሕገ መንግሥት አውጥቶና አጽድቆ ሊመራበት ይገባል። የፌድራል ሕገ መንግሥትም የክልሎቹን ሕገ መንግሥት መሠረት በማድረግ ሊሻሻልና በውሳኔ ሕዝብ ሊጸድቅ ይገባዋል።

በዚህ መልኩ የሕዝባችን ጥያቄዎች ቢፈቱ በሕገ መንግሥቱ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ያገኛሉ። ከሕዝባችን መካከል ጥላቻ ይወጋዳል።መፈነቃቀሉ ያከትማል። መንግሥትም በሕዝቡ ላይ ፈላጭ ቈራጭ መሆኑ ይቀራል።የክልል ፓርቲዎችና የብሔር ድርጅቶችም  እስከ ምርጫው ወቅት ድረስ፣ሕገ መንግሥቱን በማሻሻል፣ ኅብርተሰቡን ለማገልገል ያስችላቸዋል።

የኢሕአዴግ የንብረት ክፍፍልን በሚመለከት፣እንደ እውነቱ ከሆነ ኢሕአዴግ የኢትዮጵያን  ሕዝብ ቢያንስ ለ27 አመታት አስተዳድሯል።በዚህ ጊዜ በውሳኔው አግሪቱን የባሕር በር አሳጥቷል፣በባድመን ጦርነትም የወንድማሞችን ደም አፋሷል። በልማት ረገድም አገሪቱን  ከኋላቀርነት አላቋል፣የትምሕርት፣የጤናና የትራንስፖት አገልግሎትን አስፋፍቷል፣ ከተሞችን አስውቧል። በዚህም ወቅት የተሰረቀና በጉልበት የተዘረፈ ሀብት ተጣርቶ፣ ከእዳ ነጻ የሆነውን  የግባሩን የወል ሀብት ሊከፋፈሉ ይገባል።

እንግዲህ ይህ  ያለመድሎ ፤በአገራችን የግለ ሰብ፣ የብሔረ ሰብና፣ የብሔር እኩልነትን  ለማስፍን የታቀደ በመሆኑ፣ትልቁም ሆነ ትንሹ ያለፈውን ጥላቻና ቅሬታውን  በይቅርታ በማለፍ፣ ከልብ  ሊተባበር ይገባል።ስለዚህም የሰላም አምላክ የሆነው እግዚአብሔር ከመለያየትና ከእርስ በርስ ጥላቻ አላቆ፤ በወንድማማች  ፍቅር አስማምቶ፣ በሰላም አብረን የምንኖርበትን ጸጋውን ያብዛልን።

ጆቢር ሔይኢ ከሁስተን ቴክሳስ፣

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

ከብልጠት ወደ ብልህነት – እውነቱ ደሳልኝ

Next Story

ከይሲነት በመልካሙ መደመር ላይ እያሴረ ነው። – መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

Go toTop