የኮሮና ቫይረስ በሀገራችን ኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ የሥጋት ድባብን ፈጥሯል፡፡ የዓለም ተመራማሪዎች የዚህን በሽታ መድኃኒት ለማግኘት ሌት ተቀን ደፋ ቀና እያሉ ቢሆንም፣ እስከ ዛሬ ድረስ ግን ምንም ዓይነት ሁነኛ መድኃኒት አልተገኘም ፡፡ በመሆኑም፣ የዓለም ማህበረሰብ የበሽታውን መስፋፋት መከላከሉ ላይ ሙሉ ትኩረቱን አድርጓል፡፡
እኛ ኢትዮጵውያን ካለን ጠንካራ ማህበራዊ መስተጋብርና ድህነት አንፃር፣ በሽታው በሀገራችን የመስፋፋት እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ ስለሆነም፣ በሸታውን ለመከላከል የሁላችንንም ትልቅ ትብብርና መተሳሰብ፣ እንዲሁም ንቁ መሆንን ይጠይቃል፡፡
ይህንን ክፉ ቀን የምናልፈው “አንተ ትብስ ፣ አንቺ ትብሽ” በመባባል፣ በመተሳሰብና ቫይረሱን ለመከላከል የሚረዱ የጤና ባለሞያዎች ምክሮችን ተግባራዊ በማድረግ ነው። ከሁሉም በላይ ልዩነቶቻችንን ሁሉ ለጊዜው ተወት አድርገን፣ ትኩረታችንን የጋራ ጠላታችን በሆነው የኮረና ቫይረስ ላይ ማድረግ አለብን፡፡
በዚህ መንፈስም፣ ባልደራስ-መኢአድ ለአባላቱ፣ ለተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች፣ ለገዢው ፓርቲ፣ ለሲቨክ ተቋማትና ብሎም ለመላው ኢትዮጵያውያን የሚከተለውን መልዕክት ያስተላልፋል
1ኛ. የኪራይ እፎይታን በሚመለከት
እንደሚታወቀው የብዙ ኢትዮጵያውያን ኑሮ ከእጅ ወደ አፍ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ዜጎች በየቤታቸው እንዲቀመጡ ሲመከሩ፣ እንዲሁም የሥራ እድሎች እየጠበቡ ሲመጡ ብዙ ዜጎች የቤት ኪራይ ለመክፈል እንደሚቸገሩ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም፣ የአዲስ አበባ መስተዳድር የግል አከራይና ተከራይ እንዲተሳሰቡ ባቀረበው ጥሪ መሠረት ፣
1/ሀ
መንግሥት ለግል አከራዮች ያቀረበውን ጥሪ እራሱም መተግበር ስለሚጠበቅበት፣
1/ሀ/1
በሀገር አቀፍ ደረጃ መንግሥት ለሚያከራያቸው ቤቶች የሚሰበስበውን ኪራይ ምህረት እንዲያደርግ
1/ሀ/2
የኮንደሚኒየም ቤቶች ወርሃዊ ክፍያ ምህረት እንዲያደረግ፣
1/ሀ/3
የስልክ፣የውሃ፥ የመብራትና የኢንተርኔት ተመኖች ቅናሽ እንዲያደረግ
1/ሀ/4
ለህክምና ባለሙያዎች የአበል ክፍያ እንዲደረግላቸውና የትራንስፖርት ችግሮቻቸው እንዲቀረፍላቸው እንዲያደርግ
2ኛ. የጦርነት እንቅስቃሴን በሚመለከት
በዚህ ወቅት ሙሉ ትኩረታችን ቫይረሱን በመከላከል ላይ መሆን ስላለበት፣ የተኩስ ድምፅ የምንሰማበትና የምንዋጋበት ጊዜ አይደለም፡፡ እንደሚታወቀው፣ ኢትዮጵያ ቀዳሚ ከሚባሉት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (UN) አባል ሀገራት አንዷ ናት፡፡ የተባበሩት መንሥስታት በዋና ፀሃፊው አንቶኒዮ ጉተሬዝ በኩል ባስተላለፈው ጥሪ፣ በመላው ዓለም የተኩስ ማቆም እርምጃ አንዲወሰድ ጠይቋል። ይህን ጥሪ በተለይ መንግሥታት እያከበሩት ይገኛል። በዚህም መሠረት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በወለጋና በአማራ ክልል ባሉ ታጣቂዎች ላይ ውጊያ የሚከፍትበትን ቀነ ገደብ እያስቀመጠ፣ ከባድ መሣሪያ የታጠቁ ወታደሮችን እያሰማራ ይገኛል። በዚህም እንቅስቃሴው ግጭት የሚፈጠርበትን ዕድል በእጅጉ ከፍ አድርጎታል ። መንግሥት ከዚህ ድርጊቱ ታቅቦ፣ ችግሮችን በድርድርና በትዕግስት ለመፍታት እንዲተጋ በአፅኖት እናሳስባለን።
ባልደራስ- መኢአድ ማንኛውንም የትጥቅ እንቅስቃሴ የሚያወግዝ ሲሆን፣ ታጣቂዎች አለመግባባቶችን በሰላም እንዲፈቱና ከተኩስ እንዲታቀቡም ጥሪ ያደርጋል፡፡
3ኛ. አላስፈላጊ እንቅስቃሴን በሚመለከት
ለበሽታው መስፋፋት ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጠር መላ ኢትዮጵያውያን ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ እንዲታቀቡ ጥሪ እናደርጋለን፡፡
4ኛ. ምሥጋና ለኃይማኖት አባቶች
ለሀገራችን ሰላምና ጤና እንዲፀልዩ የሃይማኖት መሪዎች በጋራ የወሰዱት እርምጃ በእጅጉ የሚያስመሰግናቸው፣ የሚደነቅና የሚደገፍ ሲሆን፣ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ እናስተላልፋለን።
ባልደራስ- መኢአድ
ሚያዚያ 2/2012 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ኢትዮጵያ