በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙ የራያ ተወላጆችና ወዳጆች ማህበር የተሰጠ መግለጫ

April 6, 2020

ኤፕሪል 6፣ 2020

በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙ የራያ ተወላጆችና ወዳጆች ማህበር የተሰጠ መግለጫ

ለዘሐበሻ

እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት የኮረና ወረርሽኝ ዓለምን እያስጨነቀ ይገኛል። ኢትዮጵያ ሀገራችንም የዚሁ ወረርሽኝ ሰለባ መሆን መጀመሯን የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን እየገለጹ ይገኛሉ። የፌዴራል መንግሥትም መደረግ ያለባቸዉ ጥንቃቄዎችን በመጥቀስ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ነው። ሆኖም ከማንም አቅም በላይ የሆነውና ዓለምን እያስጨነቀ ያለው የኮረና ወረርሽኝን ለመከላከል እየተደረገ ባለው ጥረት ትህነግ የሚመራው የትግራይ ክልል እየተከተለ ያለው ኢፍትሃዊ አሰራር ተቀባይነት የሌለው አግላይ አካሄድ በመሆኑ ተቃዉሞአችንን እንገልጻለን።

ወረርሽኙን ለመከለላከል ዓለም በአንድ ልብና መተባበር በሚንቀሳቀስበት በዚህ ወቅት ከድሮ ጀምሮ ህዝብን በመከፋፈል አድሎን በመፈጸም የተካነው ትህነግ ግን አሁንም የጥፋት በትሩን በራያ ህዝብ ላይ በማሳረፍ ይገኛል። ይህንን መግለጫ እንድናወጣ ያስገደደን ሰሞኑን የክልሉ የጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሐጎስ ጉድፍ በክልሉ 8 የማግለያና የማገገሚያ ማዕከላት መቋቋማቸውን የገለጸ ቢሆንም ራያን ያላካተተ መሆኑን ለመረዳት ችለናል። ትህነግ ላለፉት 30 ዓመታት የራያን ህዝብ መሬቱንና ሀብቱን እየበዘበዘ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጫና በማሳደር ህዝቡ በድህነት እንዲማቅቅ አድርጓል።

በእንግሊዝኛው Assimilation Policy በሚባል የሚታወቀውን የፖለቲካ ፈሊጥ በመከተል የራሳቸውን ሰው ወደ ራያ እያመጡ በማስፈር የራያን ማህበረሰብና ባህል  ለማጥፋት ተጽዕኖ ቢያሰድሩም “ሲገድሉን እንበዛለን” እንደሚባለው  ህዝባችን የማንነቱን ማተብ እንዳጸና ይገኛል።

ትህነግ በራያ ላይ ያስቀመጠው የረጅም ጊዜ ዕቅድ ስላልተሳካለት አሁንም መቀሌ ላይ የመሸገው ቡድን በራያ ህዝብ ላይ ጫና ማሳረፉን ተያይዞታል። ቀደም ሲል ምንም ወንጀል ሳይኖራቸው  የራያ  የማንነት ጥያቄ በማንሳታቸው ብቻ 2500 የሚሆኑ የራያ ተወላጆች ትግራይ ውስጥ በሚገኙ  እስር ቤቶች የተለያዩ ግፎች እየፈጸመባቸው ይገኛል። የፌዴራል መንግሥትና የተለያዩ የክልል ማረሚያ ቤቶች ታራሚዎችን በመፍታት ወረርሽኙን ለመከላከል ጥረት እያደረጉ ባሉበት በአሁኑ ወቅት ትህነግ ግን ከዚህ ቀደም የታሰሩትን መፍታት ሲገባው በተቃራኒው የራያን ወጣቶችን በማሰር ላይ ይገኛል። ይህም ሰዎቹን ስብስቦ ለሞት እንደማዘጋጀትና በራያ ህዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዲፈጸም ጭምር በዝግጅት ላይ መሆኑን ያመላክታል።

ከ800,000 በላይ ህዝብ ያላቸው የራያ ወረዳዎች የሚያመርቱትን ጤፍና ማሽላ እንዲሁም ሌሎች ምርቶችን የክልሉን የምግብ አቅርቦት ለመሸፈን በሚል ምርቱን አግበስብሶ እንደሚወስድ ይታወቃል። ይሁን እንጂ ለዚህ ህዝብ የጤና ተጋላጭነት አለማሰብና ማግለል “መሬቱን እንጂ ህዝቡን አንፈልገውም” የሚለው የቀድሞ ንግግራቸውን የሚያጠናክር ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ በመሆኑም የራያ ህዝብ ካለበት የጨለማ ህይወትና አገዛዝ ተላቅቆ ራሱን በራሱ እስኪያስተዳድር ድረስ ግብር ያስከፈለውና ኃላፊነት አለብኝ የሚለው የትግራይ ክልል መንግሥት ተገቢውን ቅድመ – ዝግጅት ካለማድረጉ የተነሳ ወረርሽኙ በራያ ህዝብ ላይ ለሚያደርሰው ጉዳት ተጠያቂ እንደሚሆን ከወዲሁ ሊያውቀው ይገባል።

በመሆኑም እኛ በሰሜን አሜሪካ የምንኖር የራያ ተወላጆችና ወዳጆች ማህበር የሚከተለውን መልዕክት ለማስተላለፍ እንወዳለን።

  1. የክልሉ መንግሥት አሰራሩን አስተካክሎ ኃላፊነቱን እንዲወጣ፣
  2. ትህነግ በማንነታቸውና በተለያዩ ምክንያቶች ያሰራቸውን ሰዎች በአስቸኳይ እንዲፈታ፣
  3. ህዝባችን ከመቸውም ጊዜ በበለጠ በሚዲያዎች እየተላለፈ የሚገኘውን የጤና ባለሙያዎችን ምክር ተግባራዊ እንዲያደርግ፣
  4. የራያ ወጣቶች ወረርሽኙን ለመከላከል ከሚንቀሳቀሱ በጎ አድራጊዎች ጋር ተባብረው እንዲሰሩና የማህበረሰቡን ግንዛቤ እንዲያዳብሩ፣
  5. በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ የሚገኙ ምግባረ ሠናይ ድርጅቶችና ባለሃብቶች ለራያ ህዝብ ድጋፍ እንዲያደርጉ፣
  6. የክልሉ መንግሥት ኃላፊነቱን መወጣት ስላልቻለ የፌደራል መንግሥት የኮረና ቫይረስን ለመከላከል በነደፈው ስትራቴጂ ዙሪያ ራያን በተለየ መንገድ የሚያስተናግድበትን አሰራር እንዲያመቻችና ድጋፍ እንዲያደርግ እንጠይቀለን።

በሰሜን አሜሪካ የራያ ተወላጆችና ወዳጆች ማህበር

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

ኮሮናቫይረስ ምንድነው? እንዴትስ ነው ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፈው? – SBS Amharic

Next Story

ኮረናን ለመከላከል የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከፀደቀበት ጊዜ ጀምሮ በመላ ሃገሪቱ ለ5 ወራት ተፈጻሚ እንደሚሆን ተገለጸ

Go toTop