ኢትዮጵያውያን ሆይ እባካችሁ በኮሮና ቫይረስ እንኳን ማስተዋል ይኑረን! – ሰርፀ ደስታ

March 17, 2020

እንደምታዘበው እጅግ የበዙ የተሳሳቱ መረጃዎች የኮሮናን ቫይረስ አስመለክቶ እየተሰራጩ ነው፡፡ ይሄ በሌሎችም እየተስተዋለ ያለ ቢሆንም በእኛ ማህበረሰብ ያለው አደገኛ ይመስላል፡፡ ነገሮችን ማሳከር ሥራዬ ብለው በተቀመጡ ሰዎች በሚሰራጭ ወሬ ብዙ ሰው ትክክለኛውን ነገር እንዳያስተውል እየሆነ ይመስላል፡፡ አንዳንድ መልዕክቶች በቮይስ ሜይል ሳይቀር እየደረሱን ነው፡፡ የእነዚህ ሰዎች ዓላማ መረጃዎችን ማሳከር እንጂ በእርግጥም መረጃ መስጠትን መሠረት ያደረገ አይመስልም፡፡ አንዳዶች ሳይንቲስቶችን ሌሎች ደግሞ የእምነት ሰዎችን ዋቢ እየጠቀሱ መረጃ ለማሳከር እየተጠቀሙ እናያለን፡፡ ሌሎች ደግሞ ያችኒው የኖርንባትን የፖለቲካ ቁማር ሲጠቀሙ እናያለን፡፡ ለማስተዋል እንዲረዳ በሰፊው እየተነገሩ ካሉት የሚከተሉትን እንደ ማሳያ እያነሳሁ አቀርባለሁ

የሀይማኖት አባቶች ምክር፡ፊጦ፣ ሎሚ፣ ነጭሽንኩርት….ወዘተ፡- እንግዲህ ማስተዋል ከጠፋ እንዲህ እንሆናለን፡፡ ዳንኤል ክብረት ይሄንን አስመልክቶ እባካችሁ በአባቶቻችን ሥም አትቀልዱ በሚል በትክክል ጉዳዩን ገልጾታል፡፡ ነገሩ ግን ቀልድ ሳይሆን ንግድ ስለሆነ አትነግዱ ቢለው ይሻል ነበር፡፡ እውነታው የሀይማኖት አባት ተግባር ከእግዚአብሔር በሚያገኙት መንፈሳዊ ሀየይል እንጂ ፌጦና ሎሚ ለመበጥበጥማ እኛው የተሻልን ነን፡፡ ነገሩ በዚህች ነገር ለመነገድ የፈለገ መንፈሳዊ አባቶች ተናገሩት ብዬ ብል ብዙ ሕዝብ ይሰማኛል በሚልና ቆይቶ ከፌጦና ሽንኩርት የተቀመመ መድሐኒት እያለ ሌላ የሕዝብ ንግድ ምንአልባትም አደጋ ሊሰራ የቀደ ነው የሚመስለው፡፡ እነዚህ ግብዓቶች ማንም ሳይለን መድሀኒት እንደሆኑ እናውቃለን፡፡ በባህልም ጉንፋንን ጨምሮ ለተለያዩ የጤና እክሎች ለማከም እንጠቀምባቸዋለን፡፡ የኮሮና ቫይረስንም አደጋ ለመቀነስ ሊጠቅሙ ይችላሉ፡፡ ይሄ ስህተት አደለም፡፡ ትልቁ ስህተት መጀመሪያ በሀይማኖት አባቶች ታዘዘ መባሉ ቀጥሎ፣ በእነዚህ ግብዓቶች ሕዝብን ማደፋፈርነ ሌሎች የቫይረሱ መከላከያ እርምጃ ከመውሰድ ማዘናጋቱ፣ ቀጥሎም በእርግጥም እነዚህ ግብዓቶች መድሀኒት ቢሆኑ እንኳን አሁን በምናየው ዘመቻ እነሱን ማጣጣልን ይጨምራል፡፡ እነዚህ የተጠቀሱት መድሀኒቶች በእርግጥም ሊረዱ ይችላሉ፡፡ እነሱንም እንደ አንድ አማራጭ ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ ሆኖም እነሱን ከተጠቀምክ ችግር አይኖርም አይነት አደገኛ መልዕክት፣ ከዛም በላይ በእምነት ላይ ማፌዝ የበለጠ መቅሰፍት እንዳይሆን ያሰጋል፡፡

የቻይና ዶክተሮች ሎሚ ጠጡ ብለዋል ሌላው በስፋት በቮይስ ሳይቀር እየተላለፈ ያለው አሁንም የቻይና ዶክተሮች ሎሚ ፍቱህ መድሀኒት እንደሆነ ተናግረዋል የሚለው ነው፡፡ አንዳንዶቹ መልዕክቶች ከላይ የተጠቀሱትን የእኛንው ባሕላዊ መድሀኒቶች ሁሉ እነዚሁ የቻይና ዶክተሮች አረጋግጠዋል አይነት ነው፡፡ አንዳንዶቹ እንደውም በቻይና አሁን ቫይረሱ ከተነሳበት ዊሀን ከተማ የሕክምና ተማሪ እንደሆኑ ጭምር በመጠቆም ነው መልዕክት እያስተላለፉ ያሉት፡፡ እነዚህ ሁሉ ግን ትክክለኛ ያልሆኑ ከመሆናቸውም በላይ ሕዝብን ማድረግ ከሚገባው ጥንቃቄ የሚያዘናጉ ናቸው፡፡ ከላይ እንደጠቆምኩት ስንኩርትና ሎሚ መድሀኒትነታቸው እውነት ነው፡፡ ለጉንፋን ቫይታሚን ሲ ያላቸውን ነገሮች መመገብ ወይም መጠጣት ጠቃሚ ነው፡፡ ይሄን ሁሉ ዓለም ያውቃል፡፡ አሁን የተከሰተው ቫይረስን የሚያደርሰውን አደጋ ለመቀነስ እነዚህን ምግቦች፣ ወይም ግብዓቶች መጠቀሙ ስህተት አደለም፡፡ ሆኖም ቫይረሱ እንዳይዝ ቀድመ ጥንቃቄ ማድረግ ከምንም በላይ ወሳኝ ነው፡፡ ቫይረሱ ከዚህ በፊት ከሚታወቁት የጉንፋን ቫይሮሶች በላይ አደገኛ ነውና

የኢትዮጵያ አየርመንገድ ሥራአስኪያጅ አቶ ተወልደን መወንጀል፡– እንግዲህ ነገሮችን የማስተዋል አቅማችን ምን ያህል እንደወረደ ከምንታዘብባቸው ጉዳዮች አንዱ ቫይረሱ ኢትዮጵያ ለመግባት ዋና ምክነያት ናቸው እየተባለ የሚከሰሱት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሥራ አስኪያጅ የአቶ ተወልደን ነገር እዚህ ጉዳይ ውስት አምጥተው ሆን ብለው ነገሮችን ወደሌላ ሊዘውሩ የሚሞክሩትን አለማስተዋላችን ነው፡፡ እንደእውነቱ በየትኛውም አገር የሚገቡና የሚወጡ ጉዞዎችን የማገድ ሥልጣን የመንግስት እንጂ የአቶ ተወልደ አይነት የአንድ አየር መንገድ ሥራ አስኪያጅ አደለም፡፡ ሌላው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሙሉበሙሉ ንብረትነቱ የመንግስት ሲሆን ስራ አስኪያጁ በእንዲህ ያሉ ጉዳዮች በረራን የማስቆም አንዳችም ስልጣን የለውም፡፡ የአብዬን ወደ እምዬ እንዲሉ ገና ለገና ተወልደ ትግሬ ስለሆኑ ብቻ ድሮ በወያኔ እያሳበቡ ትግሬን የመጥላት መርዝ ሲረጩ የነበሩ አሁን ደግሞ በኮሮና አሳበው ተወልደን ለመክሰስ መሞከራቸው በጣም አሳፋሪ ነው፡፡ ከዚህ በላይ ግን የሚያሳዝነው እነዚህኑ የጥላቻ መርዝ የሚረጩትን እየሰማን ትክክለኛ  መወሰን የነበረበትን አካል አለማስተዋላችን ብቻ ሳይሆን ለሌላ የፖለቲካ ቁማር መጫወቻ ራሳችንን ማጋለጣችን ነው፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ምክነያት ኢትዮጵያ ከሌሎች አገራት በተለየ አደጋ ላይ አደለችም፡፡ አደጋው ለሁሉም ነው፡፡ ይልቁንም በኢትዮጵያ ይህ አደጋ የደረሰው ዘግይቶ ከመሆኑ አንጻር የአቅም ውሱንነትና የአመራር ብቃት ችግር ካልሆነ በቂ ዝግጅት ለማድረግ ጊዜ ሰጥቷል፡፡ ያም ሆኖ ዛሬ በኢትዮጵያ ተገኙ የተባሉት የቫይረሱ የመጀመሪያ ሰዎች በኢትዮጵያ አየር መንገድ ይሁን ወይም በሌላ ኢትዮጵያ ውስጥ የገቡት የምናውቀው ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ ብዙ አውሮፕላኖች ወደ ኢትዮጵያ ይበራሉና፡፡ እንግዲህ ተወልደ ይሄንንም ማገድ ነበረበት አይነት የአስተሳሰብ ባርነት ውስጥ ካልወደቅን፡፡ የኢትዮጵያንም ሆነ ሎሎች በረራዎች የድንበር እንቅስቃሴዎችን የመቆጣጠር ሙሉ ሀላፊነቱ የመንግስት እንጂ የተወልደ አደለም፡፡ ተወልደ በሌላ የሚከሰሱበት ጉዳይ ካለ መጠየቅ ይቻላለ ግን ይሄ አይነቱ ውንጀላና ቁማር በጣም ያሳዝናል

የኮሮና ቫይረስ ክትባት ተገኘ፡- ይሄ አንዱ በሰፊው እየተሰራጨ ያለ አዘናጊ የሚመስል መልዕክት ነው፡፡ በእርግጥም የዚህ በሽታ ክትባት ዲዛይን የተደረገው ቻይናዎች የቫይረሱን መለዘር ረድፍ( ሲኩዌንስ) ይፋ ባደረጉት በሶስተኛው ቀን ነው፡፡ ዓለም በዚህ ያህል የረቀቀ ሂደት ቢፈጥንም ግን ትልቅ ስጋት እንደሆነ በጣም እያሳሰቡ ባሉበት ሆኔታ የዚህ ክትባት ሂደት ምንም የማይረዱ ሰዎች በጅምላ መረጃ ሌሎችን ለዝንጋኤ የሚዳርግ መልክት ማስተላለፍ ስህተት ነው፡፡ ክትባቱ አስፈላጊዎን ሂደት አልፎ ለሥራ እስከሚውል ድረስ ወራቶች የሚጠይቅ ነው፡፡ አሁን በምናየው የቫይረሱ ፍጥነት ክትባቱ ለሥራ በሚደርስበት ወቅት በሚሊዮኖች በቫይረሱ ሊጠቁ ይችላሉ፡፡ ሌላው በተለይ በትላንትናው ዕለት ለመጀመሪያ ሙከራ የተደረገለት ክትባት ከዚህ በፊት ከነበሩት የተለየና ሙሉ በሙሉ አዲስ በመሆኑ ስኬታማነቱን ለማረጋገጥ ተጨማሪ ጊዜ ሊጠይቅ ይችላል፡፡ ከዚህ በፊት ክትባት የሚሰራው ከሞተ ወይም አቅም ከሌለው የቫይረስ ወይም የተውሳኩ አካል ሲሆን ይሄ ትላንት ሙከራው የተጀመረው ክትባት ግን በቀጥታ mRNA ከተባለ የፕሮቲን ተሸካሚ (መሠረት) ን በመጠቀም ነው፡፡ ስኬታማ ከሆነ በእርግጥ ከተለመዱት ክትባቶች ለፍጥነትም ለምርትም፣ ለማጓጓዝም ቀላል ሊሆን ይችላል፡፡ ምን አልባትም አሰራሩ ልክ የኮምፒተር ሶፍትዌር እንደማባዛትና መጫን ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ሁሉ ግን እውን ለመሆን ቢያንስ ወራትን የሚጠይቅ ሂደት እንደሆነ ሳይንቲስቶቹ እየተናገሩ ነው፡፡ ሁሉም በተቻለ ፍጥነት እየሰራ ነው፡፡ ግን አሁን ላይ በቫይረሱ ከመያዝ አንድም መፍትሄ የለም ራስን ከመጠበቅ ውጭ፡፡

ሌሎችም ብዙ የመረጃ ማሳከር ችግሮች እያየን ነው፡፡ ሕዝብ በደንብ ሊያስብ ይገባዋል፡፡ አንዳንዶች እየተጋነነ የሚመስላቸው አሉ፡፡ ችግሩ በጣም ችግር እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ምን አልባትም መንግስታት ሕዝብ እንዳይደናገጥ በሚል ጉዳዩን ረገብ አድርገውት ከአልሆነ የችግሩን ፍጥነት ለሚመለከት ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ ለማስተዋል ይቻላል፡፡ በእርግጥም እጅግ መደናገጥ አያስፈልግም፡፡ ግን መደረግ የሚገባውን ጥንቃቄ ሁሉ ማድረግ ለራሳችንም ለሌሎችም ትልቅ ከጽድቅ  የሚቆጠር ሥራ ነው፡፡ ስለዚህ አባካችሁ በወሬ አንሳከር ትክክለኛ መረጃ የሚሰጡ የመረጃ ምንጮችን እንከተል፡፡ በተለይ የመንግስታቱን ጤና ድርጅት ጨምሮ የተለያዩ አገራት  መንግስታትና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክከር እንከተል፡፡ ይሄን ጉዳይ ለፖለቲካ ጥቅምና ለሌሎች ንግዶች ለማዋል የሚሞክሩ ብዙዎች ናቸውና እናስተውል፡፡

 

ቅዱስ እግዚአብሔር ለዓለም ሁሉ ምህረቱን ይላክ! ኢትዮጵያ አገራችንን ይጠብቅ!

አሜን

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

የሕብር ሬዲዮ ፕሮግራም … የኮሮና ቫይረስን ወቅታዊ ስርጭት

Next Story

“ሸማ በፈርጁ ነው ና የሚለበሰው ፣ ከፈርሃት ይልቅ ሁሉም በየፈርጁ  የድርሻውን እየተወጣ ቫይረሱ በሀገሩ ወረርሺኝ እንዳይሆን ይከላከል፡፡ ” – መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

Go toTop