ኦነግ ሸኔ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የጦር መሳሪያ ዘረፋና ጥቃት ፈጸመ

February 6, 2020

የኦነግ ሸኔ የታጠቀ ቡድን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ንብረት አቃጥለው የጦር መሳሪያዎችን ዘርፈው ማምለጣቸውን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

በክልሉ 7 ሰዎች ታግተው ተወስደዋል በሚል በማህበራዊ ሚዲያ እየተሰራጨ ያለው መረጃ ሃሰት መሆኑንም የክልሉ ፖሊስ ለኢትዮ ኤፍ ኤም አረጋግጧል።

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል መከላከል ዘርፍ ም/ል ኮሚሽነር ነጋ ጃራ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳሉት የኦነግ ሸኔ የታጠቁ አካላት ወደ ክልሉ ገብተው ንብረት አቃጥለው እና ዘርፈው ሸሽተዋል ብለዋል።

እንደ ምክትል ኮሚሽነሩ ገለጻ ድርጊቱ የተፈጠረው ጥር 25 ቀን 2012 ዓ.ም በአሶሳ ዞን ውስጥ ባባሲ ወረዳ ውሽማ ጥርጊጊ የሚባል ቀበሌ ላይ ቁጥር 1 እና ቁጥር 2 የሚባሉ ቦታዎች ነው፡፡

ከዚህ በፊት በዚህ ቀበሌ ይኖሩ የነበሩ 4 ሰዎች አካባቢውን ለቀው የሄዱና በኋላም የኦነግ ሸኔ ቡድን የተቀላቀሉ ነበሩ፡፡

የኋላ ኋላ እነርሱን ጨምሮ ወደ 28 የሚደርሱ የታጠቁ ሀይሎች በ25/5/2012 ዓ.ም ወደ ቀበሌው መጥተው የቀድሞውን የቀበሌ ሊቀ መንበር አቶ አደም ጉምዛ የተባለውን ግለሰብ ያገኙታል፡፡

እኚህን የቀድሞ ሊቀመንበር ባገኙ ሰዓት በወቅቱ የነበራቸው ፍላጎት የጦር መሳሪያና ከዚህ በፊት የተሰበሰበ ግብር አለ እርሱን ማምጣት አለብህ ብለው በጠየቋቸው ሰዓት ምንም እንደሌለ በመንገር ይመልሷቸዋል፡፡

በኋላም የዚህን ሰውዬ 6 ቤቶች አቃጥለው 3 ኩንታል ቦሎቄ ፤ ሁለት ኩንታል ጤፍ 1 ኩንታል ጥቁር አዝሙድ ግማሽ ኩንታል ተልባና ሁለት ኩንታል ኑግ በሳት ማቃጠላቸው ተገልጿል።

በዛው ቀበሌ ውስጥ ያገኙትን የኢትዮጵያና የክልሉን ሰንደቅ አላማ በማቃጠል ከሚኒሻዎችና ከግለሰቦች ላይ 3 ክላሽና 6 ኋላ ቀር መሳሪያዎችን ነጥቀው መሸሻቸውን ለማወቅ ችለናል፡፡

የክልሉ የፀጥታ ሀይል ወዲያው ወደ አካባቢው ያሰማራን ቢሆንም ሰዎቹን በወቅቱ ማግኘት አልቻልንም በማለት ነግረውናል፡፡

ፀረ-ሰላም ሀይሎች በባህሪያቸው አንድ ቦታ ተረጋግተው የሚቀመጡ ባለመሆናቸው የፀጥታ አካሉ ወደ አካባቢው አምርቶ አሰሳ ቢያደርግም ሊያገኛቸው ግን አልቻለም፡፡

በአሁኑ ሰዓት አካባቢው ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር እየተደረገ ይገኛል ያሉት ኮሚሽነሩ በእኛ ግምገማ እስካሁን በማህበራዊ ሚዲያ የሚራገበው ወሬ አሉባልታ ነው ብለዋል፡፡

በክልሉ የታገቱ 7 ሰዎች አሉ በሚል በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጨው መረጃ ግን ከእውነት የራቀ ነው ብለዋል ምክትል ኮሚሽነሩ።

በእርግጥ ንብረት ላይ ጉዳቶች አድርሰው ሸሽቷል፡፡ ከዛ ውጪ ወደ አካባቢው ያሰማራናቸው የፀጥታ ሀይሎች በቦታው ደርሰው ህዝቡን አረጋግተው ይህንን መረጃ አድርሰውናል ብለዋል፡፡

ይህ ከሆነበት እለት አንስቶ የኦነግ ሸኔ አባላት ለጥቃት ወደ ክልሉ መግባታቸውን ምልክቶች ታይተዋል በመሆኑም በዚህ ፀረ-ሰላም ሀይል ላይ እርምጃ ለመውሰድና ለመቆጣጠር የክልሉ ፀረ-ሽምቅ ሀይል ፤ የክልሉ ፖሊስ ፤የሀገር መከላከያ ሰራዊትና የፌደራል ፖሊስ በጋራ በመሆን በአካባቢው እንቅስቃሴዎችን እያደረገ እንደሚገኝ ነግረውናል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

የህግ የበላይነትን የቁራ ጩኸት እያወከው ነው። – ከመኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

Next Story

ሰበር ዜና: በመተከል ዞን 21 የሚሆኑ አማራዎች መገደላቸው ተገለፀ

Go toTop