ወገኖቼ፦ ይህን መልዕክት ስፅፍ ከትናንት በስቲያ ከሊቢያ ሰማይ ላይ የጦር አመፀኛው የጄነራል ካሊፋ አፍታር ተዋጊ ጄት አውሮፕላኖች ትሪፑሊ አጠገብ በቦምብ ያጋዩዋቸውን ኢትዮጲያዊያን ፣ ኤርትራውያንና ሌሎች እፍሪካዊያን ስደተኞች ልብ የሚሰብር በድን በቴሌቪዥን እየተመለከትኩኝ ነው። ለዚህም የመጀመሪያ ፅሁፌ መነሻና ምክንያቴ ይኽው የአገሬ ወጣቶችና አፍሪካዊያን ወገኖቼ አሣዛኝ አሟሟት ነው።
ውድ ወገኖቼ፦ የዛሬ 30 ዓመት ገደማ ለትምህርት ወደ ውጭ አገር ወጥቼ በዚያው ስደት ዓለም ገብቼ በለንደን ከተማ ኗሪ ነኝ። ከአገራችን ውጪ በሌላው አገር በገንዘብ ፣ በምቾት የውስጥ ጊዜያዊ ደስታ እናገኛ ይሆናል። ዋናው ሰላምና የመንፈስ እርካታ ግን ሁሉም በአገር ነው ከሚሉት ወገን ነኝ።
ምሣሌ ልጥቀስ፦
በአሁኑ ጊዜ እኔ በምኖርበት በለንደን ከተማ እኛ ጥቁሮች በየቀኑ ለልጆቻችን በሰላም ውሎ መግባት በከፍተኛ ጭንቀትና ሃሣብ ላይ ነን። ለምን ብትሉኝ በየቀኑ እስከ ሁለት ወጣቶች በመሰል ጥቁር ወጣቶች ፀብ የእርስ በርስ የጩቤ ውጊያ ይሞታሉ።
ባይገርማችሁ ታላቅ የሚባለው የእንግሊዝ አገርና መንግስት በሌሎች አገሮች ሰላምን አሰፍናለሁ እያለ ላይ ታች ሲባዝን በBBC ማየት የተለመደ ነው። በሌላ በኩል ላለፉት ዓመታት በለንደን ጎዳና በእርስ በርስ ፀብ እንደ ቅጠል ለሚረግፉት ከ16 እስከ 19 ዓመት ላሉ የአገሬው ዜግነት ላላቸው አብዛኛው ጥቁር ወጣቶች የጩቤ ውጊያ ወይም knife crime ዕልቂት ስርነቀል መፍቴህ እስከአሁን አለማግኘቱ በዓለም ደረጃ እንደመንግስት ያሣፍራል። አለያም ለጥቁሮች ሕይወት ፍፁም ግዴለሽ መሆንን ያሣያል። በተለይ የእኛን የጥቁሮች ሕይወትም አደጋ ላይ ጥሎ ይገኛል። Really Black Lives Matter?
ውድ የኢትዮጲያ አገሬ ወጣቶች፦ አገራችሁ ኢትዮጵያን አትልቀቁ ፣ አትሰደዱ ፣ ከሁሉም በላይ ኢትዮጲያ የእናንተ ናት ፣ ሣትፈልጉ ተወልዳችኋባታልና በዘር ፖለቲካ ብትማገዱም፣ ወደአልተወለዳችኋባቸው አገሮች ስትሸሸሹ ትደፈራላችሁና ፣ ትዋረዳላችሁና ፣ በባርነት ቀንበር ትወድቃላችሁና ፣ እንደ ትናንት እንደሊቢያው ባልጠበቃችሁት ቦምብ ጣይ አውሮፕላን ትቃጠላላችሁና ፣ ትታረዳላችሁና ፣ ኢትዮጵያዊነት ሣስቶ ዘረኝነት በአገራችን ቢገንም ጊዚያዊ ነውና ፣ እናት አገራችሁን ኢትዮጵያን የባሰም አለና አትልቀቁ። አትሰደዱ ፤ ዘረኝነትን ተፋለሙ ፤ እምቢ በሉ!
ወገኖቼ፦ በሰሞኑ የኢትዮጵያ ሁኔታ አትደናገጡ ፤ ተስፋ አትቁረጡ ፤ ሁሉም ነገር ለበጎ ሊሆን ይችላልና በኢትዮጵያ አንድነትና በኢትዮጲያዊነት ተፋቀሩ ፤ ዘረኝነትን ተፋለሙ። በተለይ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጲያዊነት ቅንነት ፣ ደግነት ፣ አንድነት ፣ ከእኔ አንተ ትብስ የመረዳዳት መንፈስ ፣ ከፍፁም ዘረኝነት የመንጣት መንፈስ አንገብጋቢና አስፈላጊነት ወሣኝ ስለሆነ ትኩረት ስጡት። እዚህ ላይ የሚከሰት ቸልተኝነትና ማቅማማት በኮንጎ ፣ በሩዋንዳ ፣ በማዕከላዊ አፍሪካ ፣ በማሊና በመሣሰሉት አገሮች እንደታየው ጥቁር በጥቁር ላይ መዝመትና መተላለቅ እንደሆነ ይቀጥላል። በዚያ ብቻ አያበቃም ፤ ጥቁር ወጣቶች አውሮፓ በዕድልና በስደት እንደለንደን ያለው ከተማ ቢደርሱ እንኳን ከላይ እንደጠቀስኩት የመንግስት ትኩረትን ያጣ የጥቁር ወጣቶች የጎዳና ላይ የጩቤ ውጊያ ስጋት እድሜን ያሣጥራልና ተከባብሮ በፍቅርና በሰላም በኢትዮጵያዊነትና በኢትዮጲያ መኖር መታደል ነው እላለሁ።
ኢትዮጵያን እግዚአብሔር ይባርክ!