ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በየመን በአስከፊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተገለጸ

May 9, 2018

(ቢቢኤን) በየመን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በአስከፊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተገለጸ፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ዳይሬክተር ሞሐመድ አብዲከር፣ በየመን ተገኝተው የተለያዩ ሀገራት ስደተኞች የሚገኙበትን ወቅታዊ ሁኔታ ጎብኝተዋል፡፡ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የሌሎች ሀገራት ስደተኞች ወቅታዊ የየመን ኑሮን ‹‹አስደንጋጭ እና ሰብዓዊነት የጎደለው!›› ሲሉ የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ስደተኞቹ የተሻለ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው በመጠቆም፤ ለዓለም ዓለም ዓቀፍ የረድኤት ተቋማት እና ለየመን መንግስት አፋጣኝ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዳይሬክተሩ ባለፈው ነሐሴ ወር የኢትዮጵያ እና ሶማሌ ስደተኞች በየመን ያጋጠማቸውን አስደንጋጭ ድርጊትም አስታውሰዋል፡፡ በወቅቱ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ከሀገራቸው የተሰደዱ የሁለቱ ሀገራት ለጋ ወጣቶች ባህር ሲያቋርጡ፤ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በሚያካሂዱ ደላሎች ተገፍትረው ባህር ውስጥ የሰመጡበትን ክስተት ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፤ እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች አሁንም መቀጠላቸው አሳዛኝ መሆኑንም አውስተዋል፡፡ የዓለም ዓቀፉ የስደተኞች ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ዳይሬክተር ሞሐመድ አብዲከር፤ በየመን የቆዩት ለሁለት ሳምንታት ሲሆን፤ ጉብኝታቸውን አጠናቅቀው ባለፈው እሁድ ከሰንዓ ወጥተዋል፡፡                  

በየወሩ ወደ የመን ሰባት ሺህ ስደተኞች እንደሚፈልሱ የስደተኞች ተቋሙ ሪፖርት ይገልጻል፡፡ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት (2017) ብቻ 100 ሺህ ስደተኞች ወደ የመን መሰደዳቸውንም ሪፖርቱ ያሳያል፡፡ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች ወደ የመን ቢሰደዱም፤ ከዚህ ቁጥር ውስጥ አብዛኛውን ቁጥር የሚይዘው ግን የኢትዮጵያ እና ሶማሌ ስደተኞች የሚያትተው የስደተኞች ኤጀንሲው ሪፖርት፤ ስደተኞቹ ከየመን በኋላ ብዙውን ጊዜ መሻገር የሚፈልጉትም ወደ ባህረ ሰላጤው ሀገራት መሆኑንም ይገልጻል፡፡ ወደ የመን ከሚጎርፈው ስደተኛ ውስጥ አብላጫው ቁጥር፣ ወደ ሳዑዲ አረቢያ የመግባት ፍላጎት አለው ይላል-መረጃው፡፡ ስደተኞቹ በየመን የተለያዩ ስቃዮችን እንደሚያስተናግዱ የተገለጸ ሲሆን፤ በየመን የጸጥታ አካላት ተይዘው በእስር ላይ እየማቀቁ የሚገኙ ስደተኞች እንዳሉም ተነግሯል፡፡ በቁጥጥር ስር የሚውሉት ስደተኞች ያለ ምንም የህግ ሂደት ለረዥም ጊዜ እስር ቤት እንዲቀመጡ ይገደዳሉ ሲልም ይገልጻል-የስደተኞች ተቋሙ ይፋ ያደረገው ሪፖርት፡፡

ዓለም ዓቀፉ የስደተኞች ተቋም (አይ ኦ ኤም) ለስደተኞቹ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ዳይሬክተሩ አቶ ሞሐመድ አብዲከር ቢገልጹም፤ ሆኖም ስደተኞቹ ያሉበት ሁኔታ እና ድርጅቱ እያደረገ ያለው የሰብዓዊ እርዳታ ተመጣጣኝ ባለመሆኑ፤ በስቃይ ላይ የሚገኙት ስደተኞች የሌሎች አካላት ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውም ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡ ሰዎችን ከቦታ ቦታ የሚያዘዋውሩ ደላሎች በስደተኞቹ ላይ ጥቃት እንደሚፈጽሙ የተገለጸ ሲሆን፤ አስገድዶ መድፈር፣ ስራ አሰርቶ ገንዘብ መከልከል እና መሰል ጥቃቶች በስደተኞቹ ላይ ከሚፈጸሙባቸው ጥቃቶች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

በሪፖርቱ ላይ እንደተጠቆመው፤ ዓለም ዓቀፉ የስደተኞች ኤጀንሲ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት (2017) 2 ሺህ 900 ስደተኞችን ከየመን ወደ ሀገራቸው መልሷል፡፡ ከዚህ ቁጥር ውስጥ አብላጫውን ቦታ የሚይዙት ማለትም 73 ፐርሰንት የሚሆኑት የሶማሌ ስደተኞች ሲሆኑ፤ 25 ፐርሰንቶቹ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች፣ እንዲሁም ቀሪዎቹ ወይም ሁለት ፐርሰንት የሚሆኑት የሌሎች ሀገራት ስደተኞች ናቸው፡፡ ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ፈቃደኛ የሆኑ 197 ኢትዮጵያውያንን እና 939 ሶማሊያውያን ስደተኞችን ከየመን ወደየሀገራቸው እንዲመለሱ ማስቻሉንም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ ሪፖርት ይገልጻል፡፡ ስደተኞቹ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ በተደረገው ጥረት ውስጥ የመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን እና የስደተኞች ኤጀንሲ ትብብር ማድረጋቸውንም ሪፖርቱ ያትታል፡፡

የየመን የስደተኞች እና ፓስፖርት ጉዳይ ባለስልጣን በህገ ወጥ ስደተኝነት ያሰራቸው ስደተኞች እንዳሉም በመረጃው ላይ ተቀምጧል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 97 ፐርሰንት የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ናቸው ተብሏል፡፡ በእስር ላይ የሚገኙትም፡- ከ18 በታች የሆኑ አስር ልጃገረዶች እና 12 ታዳጊ ወንዶች፣ ሃያ ሴቶች እንዲሁም 227 ወንዶች ስደተኞች ናቸው፡፡ የስደተኞች ኤጀንሲው፣ ከተጠቀሰው የየመን ባለስልጣን መስሪያ ቤት ጋር በመተባበር፤ በእስር ላይ ለሚገኙት ስደተኞች የምግብ፣ የመጠጥ ውሃ፣ የጤና እና የስነ ልቦና ምክር ድጋፍ ማድረጉን ገልጿል፡፡ በሀገሪቱ የተከሰተው የእርስ በእርስ ግጭት የመን እንኳን ለሌሎች ለራሷም ዜጎች የማትመች ሀገር እንዳደረጋት የገለጹት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ዳይሬክተር ሞሐመድ አብዲከር፤ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ወደምትገኘው የመን የተሰደዱ ዜጎች በጣም አስከፊ በሚባል ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ አጽንዖት ሰጥተው አሳስበዋል፡፡

 

Previous Story

 አበበ ቶላን ተው በሉት!!! (ከተማ ዋቅጅራ)

Next Story

ከተለያየ የአማራ ክልል በግፍ ታሰረው በግንቦት 7 የተከሰሱ የአማራ ክልል ተወላጆች የደረሱበት አልታወቀም

Go toTop