ሁለት የሶማሊላንድ ጋዜጠኞች ስለ ኢትዮጵያ በዘገቡት ዜና መታሰራቸው ተገለጸ

January 9, 2018

የሶማሊላንድ ፍርድ ቤት በሁለት የሀገሪቱ ጋዜጠኞች ላይ የእስር ቅጣት ማስተላለፉ ተገለጸ፡፡ ጋዜጠኞቹ ለእስር የተዳረጉት ኢትዮጵያን በተመለከተ በሰሩት ዜና መሆኑን የጠቆሙት ዘገባዎች፤ በዜናው ምክንያትም እያንዳንዳቸው በሁለት ዓመት እስራት እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል፡፡ አህመድ ዲሬ እና ሞሐመድ አብደላህ የተባሉት ሁለቱ ጋዜጠኞች፤ በሚሰሩበት ጋዜጣ ላይ የኢትዮጵያ አማጺ ኃይሎች ሶማሊ ላንድ ውስጥ የጦር ስልጠና እየወሰዱ ነው የሚል ዘገባ መስራታቸው፣ ለእስር እንደዳረጋቸው ነው የተገለጸው፡፡

‹‹ሄጎ ኒውስ›› በተባለው የግል ጋዜጣ ላይ ታተመ የተባለው ይኸው ዘገባ፤ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ያመጹ ታጣቂዎች አውዳል በተባለው የሶማሊላንድ አካባቢ ስልጠና እየወሰዱ እንደሚገኙ የሚጠቁም እንደሆነ ተነግሯል፡፡ ጋዜጠኞቹ የታሰሩበት ይኸው ዘገባ ከክስ መዝገባቸው ጋር ተያይዞ ለፍርድ ቤት ቀርቧል ቢባልም፤ ዘገባው በጋዜጣውም ሆነ በጋዜጣው ድረ ገጽ ላይ ሊገኝ አለመቻሉን የገለጸው ደግሞ ሲፒጄ የተባለው የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ተቋም ነው፡፡ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ጋዜጠኞቹ እንዲፈቱም ጥሪ አቅርቧል፡፡

ሂውማን ራይትስ ሴንተር የተባለ ሌላ ድርጅት በበኩሉ፤ ጋዜጠኞቹ በተከሰሱበት እና በተፈረደባቸው ጉዳይ ላይ ይግባኝ እንደሚያቀርብ አስታውቋል፡፡ ይኸው ድርጅት እንደገለጸው ከሆነ፤ ጋዜጠኞቹ ከተከሰሱባቸው ጉዳዮች መካከል፤ የሶማሊላንድን ሰንደቅ ዓላማ አራክሰዋል የሚል ክስም ይገኝበታል፡፡ ሁለቱ ጋዜጠኞች ሲሰሩበት የነበረው ጋዜጣ የሚተዳደረው በግል ሲሆን፤ የጋዜጣው ባለቤቶች ከጋዜጠኞቹ እስር ጋር በተያያዘ ምንም ዓይነት መረጃ አለመስጠታቸው ተዘግቧል፡፡

 

BBN news January 9, 2018

Previous Story

እሳቱን የጫረው ማን ነው? | ገረሱ ቱፋ እና ጀማል ድሬ ያብራራሉ | ልዩ ውይይት

Next Story

እስረኞችን መፍታት የሕዝቡ አንዱ ጥያቄ እንጂ ብቸኛውና የመጨረሻው ጥያቄ አይደለም!

Go toTop