ኮትዲቯራዊው ኮከብ ዲዲየር ድሮግባ ከዚህ በኋላ አራት ዓመት እግር ኳስ መጫወት እንደሚፈልግ ተናግሯል። ሱፐር ስፖርት እንዳስነበበው የቀድሞው የቼልሲ ኮከብ ድሮግባ ከእንግዲህ ወዲህ ለአራት ዓመታት በእግር ኳስ ሕይወት ይቀጥላል።
የሰላሳ አምስት ዓመቱ ድሮግባ ዕድሜው ቢገፋም ቼልሲን ለቅቆ ወደ ቱርኩ ክለብ ጋላታሳራይ በማቅናት ጠንካራ ተጫዋች መሆኑን አስመስክሯል። ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተጫዋቹ ጫማ ሊሰቅል መቃረቡ እየተነገረ ይገኛል።
ድሮግባ በበኩሉ ከእግር ኳስ ሕይወት በቅርቡ እንደማይለይ በመናገር ቢያንስ ለአራት ዓመታት የመጫወት እቅድ እንዳለው ገልጿል። ድሮግባ ይህን ካደረገ ጫማውን የሚሰቅለው በሰላሳ ዘጠኝ ዓመቱ ይሆናል። ይህም የታላቁን ካሜሩናዊ ሮጀር ሚላን ብዙ ዓመት የመጫወት ክብረወሰን እንዲጋራ ያስችለዋል።
የኮትዲቯር እግር ኳስ ወርቃማ ትውልድ አካል የሆነው ድሮግባ ሰላሳ ስድስተኛ ዓመቱን በመጪው መጋቢት ወር ያከብራል። ብሔራዊ ቡድኑን በአምበልነት በመምራት አገሩ ከአፍሪካ ቀዳሚውን ሥፍራ እንድትይዝ በማስቻልም ድሮግባ ትልቅ ሥራ ሠርቷል።
ድሮግባ በእዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ዕድሜያቸው ከሃያ ዘጠኝ በላይ የሆኑና በእግር ኳስ ውስጥ የነቃ ተሳትፎ ያላቸው ተጫዋቾች የሚሸለሙትን የወርቅ ጫማ በሞናኮ ከተማ መሸለሙ ይታወሳል። በሽልማቱ ወቅት ባደረገው ንግግርም ፈጣሪ ዕድሜና ጤና ሰጥቶት ለበርካታ ዓመታት እግር ኳስ እንዲጫወት ተማጽኗል።
ድሮግባ ከብራዚሉ የዓለም ዋንጫ በኋላ ከእግር ኳስ ራሱን ያገልላል የሚለው አሉባልታ እውነት እንዳልሆነ አስተባብሏል። በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ኮትዲቯር ሴኔጋልን ሦስት ለአንድ በሆነ ውጤት እንድታሸንፍ በማድረግ ድሮግባ ትልቅ ሥራ ሰርቷል።
ሴኔጋል በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከራሷ ከኮትዲቯር ጋር በሜዳዋ ጨዋታ ባደረገችበት ወቅት ደጋፊዎች ባስነሱት ሁከት ለአንድ ዓመት ያህል በሜዳዋ እንዳትጫወት ፊፋ ቅጣት ጥሎ ባታል። እንዳጋጣሚ ሆኖም በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ሴኔጋል ከኮትዲቯር ጋር ተደልድላ የመጀ መሪያውን የማጣሪያ ጨዋታ አቢጃን ላይ አድርጋ ሦስት ለአንድ ተሸንፋለች።
ኮትዲቯር በሜዳዋ ድል ካደረገች በኋላ የመልሱን ጨዋታ በገለልተኛ ሜዳ ሞሮኮ ካዛብላንካ ላይ ታደርጋለች። ኮትዲቯር በሜዳዋ ያጣጣመችው ድል አንድ እግሯን የብራዚሉ ዓለም ዋንጫ ላይ እንዳደረገች እየተቆጠረ ይገኛል። ይህ ማለትም የመልሱን ጨዋታ በገለልተኛ ሜዳ አሸንፋ የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ እንደም ትሆን ያመላከተ ሆኗል።