ርዕዮት ዓለሙ በ እስር ቤት የረሃብ አድማ ጀመረች፤ በሙስና የታሰሩት ኮ/ል ሃይማኖት እያስፈራሯት መሆኑን ተናገረች

September 11, 2013

ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ የ2005 ዓ.ም በዘ-ሐበሻ አንባቢዎች የዓማቱ ምርጥ የሴት ጋዜጠኛ በሚል የተመረጠችውና በእስር ቤት እየማቀቀች የምትገኘው ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ ከትላንት ጀምሮ ከእናት ከአባት እና ከነፍስ አባት ውጪ እንዳትጠየቅ በመከልከሏ የረሃብ አድማ ላይ መሆኑና ጋዜጠኛ በፍቃዱ ኃይሉ በፌስቡክ ገጹ ባሰራጨው መረጃ ገለጸ።

በቅርቡ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ክስ ከተመሰረተባቸው ውስጥ አንዷ የሆኑት ኮ/ል ሃይማኖት (በተመሳሳይ ወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው እና የጉምሩክ አመራር የነበሩት አቶ ገ/ዋህድ ባለቤት)፤ ርዕዮት ያለችበት ክፍል እንዳሉና፤ ከኮ/ል ሃይማኖት በተደጋጋሚ ዛቻ ፣ ስድብ እና ማስፈራሪያ እየደረሰባት እንደሆነ በዛሬው እለት ሊጠይቋት ለተፈቀደላቸው ለእናቷ ገልፃለች፡፡ እንዲሁም ከማረሚያ ቤቱ የሴት ፖሊሶችና እና ደህንነቶችም ተመሳሳይ ማስፈራሪያ፣ ስድብ እና ዛቻ እየበረታባት እንደሆነ ተናግራለች፡፡

ዛሬ ለበዓል ሊጠይቋት ከሄዱ ቤተሰቦቿ እና ጓደኞቿ መሃል እናቷ ብቻ እንዲያዩአት የተፈቀደላቸው ሲሆን፤ እየደረሰባት ያለውን የሰብአዊ ጥሰትም በመቃወም ከትላንት ጀምሮ የምግብ አድማ ላይ መሆኗን በመግለጿ፤ ይዘውላት የሄዱትን ምግብ መልሰውታል ያለው ጋዜጠኛው “በዚህ ስሜት ውስጥ ያሉትን የርዕዮት ቤተሰቦች ለማፅናናትም የሚከብድ ነገር ነው፡፡” ሲል ስሜቱን ገልጿል።

Previous Story

የማለዳ ወግ …አምላክ ሆይ ! የአዲሱ አመት ተስፋና ምኞታችን አሳካው !

Next Story

የዓመቱ የዘ-ሐበሻ አንባቢዎች ምርጥ ሰው – የአንዷለም አራጌ የሕይወት ገድል

Go toTop