አቶ ኤርሚያስ አመልጋ በተከሰሱበት የደረቅ ቼክ መስጠት ወንጀል የ600 ሺህ ብር ዋስትና ተፈቀደላቸው

April 1, 2016

የቀድሞው የአክሰስ ሪል ስቴት ስራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ አመልጋ በተከሰሱበት የደረቅ ቼክ መስጠት ወንጀል የ600 ሺህ ብር ዋስትና ተፈቀደላቸው።

ዓቃቢ ህግ ግለሰቡ የተከሰሱት በስድስት ክሶች መሆኑንና የገንዘቡ መጠንም ከ4 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ በመሆኑ ቢለቀቁ ሊሰወሩ ይችላሉ በሚል ዋስትናቸው ውቅድ እንዲሆን ጠይቆ ነበር።

የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው የቀረበው ተቃውሞ ተጨባጭ ማስረጃ የሌለውና የክሱ አንቀጽ ዋስትና የሚያስከለክል ባለመሆኑ ደንበኛቸው ዋስትና ሊፈቀድላቸው ይገባል ሲሉ ተከራክረዋል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ የወንጀል ችሎትም የግራ ቀኙን መርምሮ ተከሳሽ ከተጠረጠሩበት ቀን ጀምሮ ከ3 ዓመት በኋላ እዚሁ አገር ውስጥ የተገኙ በመሆኑና በዓቃቢ ህግ የቀረበው መቃወሚያ በህጉ ዋስትና የሚያስከለክል ባለመሆኑ ዋስትናው ሊፈቀድላቸው ይገባል ብሏል።

በዚህም የክሱን ጭብጥና ወርሃዊ ገቢያቸውን ከግምት በማስገባት የ600 ሺህ ብር ዋስትና ተፈቅዶላቸዋል።

ከሀገር እንዳይወጡም እገዳ ተፅፎባቸው ለሚመለከተው ሁሉ እንዲላክ ትዕዛዝ ተላልፏል።

አቶ ኤርሚያስ ከእምነት ማጉደል ወንጀል ጋር ተያይዞ የስር ፍርድ ቤት ለፈቀደላቸው ዋስትና የፖሊስ ይግባኝ ላይ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለመጋቢት 30 ቀን 2008 ዓመተ ምህረት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በሀይለየሱስ ስዩም

Previous Story

የፖፕ ፍራንሲስ እና የፓትሪያርክ አቡነ ማትያስ መገናኘት ቫቲካን የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እንድትጠይቅ ያስችል ይሆን?

Next Story

ኢትዮጵያ በጠቢቡ ሰለሞን ሸንጎ! (ታሪኩ አባዳማ)

Go toTop