ታህሳስ 30፣ 2008 (ጃንዋሪ 9፣ 2016)
ሕዝብ መብቱን ሲነፈግ፣ያገሩ ክብርና አንድነት ሲደፈር፣በሰላም ሠርቶ ማደር ሲሳነው፣በኑሮ ውድነትና በሥራ አጥነት ሲወጠር፣ጭራሽ የመኖር ተስፋው ሲጨልም ከትዕግስትና ከመንፈሳዊው የትግል ዘዴ ከጸሎት ወጥቶ በአደባባይ በሚገለጽ ተቃውሞ ውስጥ ለመሳተፍ ወይም ነፍጥ አንስቶ ለመፋለም ይገደዳል፡፤ በዚህም የትግል ሜዳ ውስጥ ሲገባ አምባገነን መንግስት ጉንጉን አበባ ይዞ እጁን ዘርግቶ እንደማይቀበለው ያውቀዋል።ከመንግሥት ሊሰነዘር የሚችለውን የበቀል አመጽ አይዘነጋውም። መሞት፣መቁሰል፣መደብደብ፣መታሰርና መንገላታት እንደሚኖር ገና ከጥዋቱ ቢረዳም ድምጹን አጥፍቶ፣አንገቱን ደፍቶ ከመኖር ይልቅ የመጣውን ለመቀበል ቆርጦ ያልሞት ባይ ተጋዳይ እርምጃ ይወስዳል።
ሕዝብ ለሚወስደውና ለሚከተለው የትግል አቅጣጫ መሰረቱ መዋናነት የህዝቡን ጥያቄ ለመስማት የማይሻ፣በራሱ እብሪት የሚመራ አምባገነን መንግሥት በስልጣን ላይ መኖሩ ነው።ሕዝቡ በተደጋጋሚ ለሚያሰማው እሮሮ መልስ ካላገኘ ደፍሮ አደባባይ መውጣቱ የማይቀር መሆኑ በተደጋጋሚ በአገራችንና በሌሎች አገሮች የታዬ ሂደት ነው።የሂደቱ መደምደሚያ የሚሆነው ይዋል ይደር እንጂ የሕዝቡን ጥያቄ የማይቀበሉ መንግሥታት ተወግደው ስልጣኑ በሌሎች እጅ መውደቅ ይሆናል።
በሕዝብ ትግል ሳቢያ ሊመጣ የሚችለው ለውጥና የሥልጣን እርክክቦሽ በተለያየ፣ማለትም በጠቃሚና በጎጂ አቅጣጫ ሊሄድ ይችላል፤
አንደኛ ሕዝብ በቅጡ እንዲደራጅና ሁሉም በትግሉ ተሳታፊና የውጤቱ የጋራ ባለቤት እንዲሆን፣ከጎጠኝነት የራቀ በልበ ሰፊነት በቀልን አሶግዶ በመቻቻል፣አገር አድኖ ሕዝብ ለማዳን ጥረት የሚያደርግ ከሁሉም የተውጣጣ ትግሉን የሚመራ አካል ከተፈጠረ የሚመጣው ለውጥ ተስፋ ሰጭና ለሁሉም የሚጠቅም ይሆናል።
በሌላው አቅጣጫ ደግሞ በሕዝቡ ትግል ጀርባ የሕዝቡን መብት እና ጥያቄ እያነሱ ግን ሁሉም ሕዝብ የሚሳተፍበትን መድረክ እያጠበቡ በተወሰኑ ሃይሎች ብቻ የሚመራ፣ሌሎችን ያገለለና ያራቀ፣ በጠባብ ቡድናዊ ስሜትና የተወሰኑ ክፍሎቸ ጥቅም ላይ ያተኮረ አመራር በመፍጠር መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ባይቻልም እንደ አጋጣሚ ስልጣን ለመያዝ ዕድሉና ሁኔታው ቢፈቅድ የሚመጣው ለውጥ የስርዓት ሳይሆን የባለስልጣኖች መቀያየር ይሆንና ሕዝቡን በአዲስ ጉልበተኞች ለቀጣይ ስቃይና ስርዓት የሚዳርግ ይሆናል።የዚህም ሂደት ውጤት በተደጋጋሚ በተለያዩ አገሮች ሲከሰት የታዘብነውና የምናውቀው ነው የዚህ አይነቱ ለውጥ በአገራችን በኢትዮጵያ እንዲከሰት የሚሻ ቀና ልቦናና ጤነኛ አይምሮ ያለው ኢትዮጵያዊ ይኖራል ብለን አንገምትም። ይህ ማለት ግን በዛ አይነት አሰራር ውጤት ለማምጣት የተሰለፉ የሉም ማለት አይደለም፤ አሉ።መኖራቸውም በተደጋጋሚ በሚያደርጉት የአግላይነትና የተንኮል ሴራ የተረጋገጠ ነው።
በአገራችን በሁሉም አቅጣጫ ይብዛም ይነስም ሕዝባዊ ተቃውሞ በተለያየ ደረጃና መልክ ሲገለጽ ቆይቷል።አሁን የዛ የተለያየ የሕዝብ ተቃውሞ እየሰፋና እየጠነከረ መንግሥትን ከሚያሰጋበት ደረጃ ላይ የደረሰ ይመስላል።ግምቱን ወደ ውጤት ለማሻገርር የሚቀረው ነገር ቢኖር ትግሉን አቅጣጫ የሚያሲዝና የሚመራ ሃይል ከመፍጠሩ ላይ ነው።አሁንም በየፊናው ተከፋፍለው የሚጮሁ ድርጅቶች አልጠፉም እንደውም ቁጥራቸው ጨምሯል።
በአሁኑ እየተጋጋለ በሄደው ሕዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት መኖራቸው የማይታወቅና ጠፍተው የነበሩ አንዳንድ ድርጅቶች ሳይቀሩ አንገታቸውን ብቅ ብቅ በማድረግ ውድድር ውስጥ እየገቡበት ነው።፣ ትላንት ከትላንት ወዲያ ኢትዮጵያንና ኢዮጵያዊነትን ሲያወግዙ የተደመጡ ሃይሎች ሳይቀሩ ለሕዝብ አንድነትና ጥቅም የቆምን ነን እያሉ መናገር ከጀመሩበት ጊዜ ላይ ደርሰናል።
ቀድሞም ሆነ አሁን ወደፊትም ቢሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ መብት፣የአገር ሰላምና አንድነት ሊጠበቅ የሚችለው ሁሉም ተባብሮ መታገል ሲችል ብቻ እንደሆነ ከታሪካችንና ከውድቀታችን ልንማር ይገባል።በተናጠል ወይም በውጭ ሃይሎች እርዳታና ድጋፍ በጥቂቶች የሚመጣ ለውጥ ከድጡ ወደ ማጡ እንጂ ወደተሻለ ስርዓት አይወስድም።
የሁሉም ዜጋ ጥያቄና ፍላጎት በዋናነት ተመሳሳይ ነው፤የአማራው ከኦሮሞው፣ከትግራዩ፣ከአፋሩ፣ከደቡቡ፣ ከጋምቤላው፣ከጉራጌው…ወዘተ የተለየ ፍላጎት የለውም።ሰብአዊ መብቱ፣የዜግነት መብቱ ተከብሮለት በአገሩ ሊያገኝ የሚገባውን ድርሻ አግኝቶ እሱም የድርሻውን አበርክቶ በክብር መኖር ነው የሁሉም ፍላጎት።የየክልሉ አርሶ አደር ጥያቄ የሚያርሰው መሬት ባለቤትነትን፣መፈናቀል እንዲቀርለት በገፍ የሚከፍለው ግብርና የማዳበሪያ ዋጋ እንዲቀነስለት፣ልጆቹን አስተምሮ ለማሳደግና ለቁም ነገር ለማብቃት በሀገሩ ጉዳይ ላይም ሙሉ ተሳታፊ መሆን እንጂ ሌላ ምኞትና ፍላጎት የለውም።የየብሔሩ ወጣትም እንዲሁ ተምሮ የመስራትና በአገሩ ተከብሮ እየኖረ የበኩሉን ለአገሩ ለማበርከት እንጂ ሌላ ምኞት የለውም።ሁሉም ከችግርና ከመከራ ኑሮ ተላቆ መብቱ ተከብሮለት በሰላም መኖርን ይሻል።ትልቅና የበለጸገች ኢትዮጵያ፣ለዜጎቿ የምትመች ኢትዮጵያ፣የእራሷን ጥቅምና ክብር፣ዳርድንበር አሳልፎ የማይሰጥ መንግስት ያላት ኢትዮጵያ እንድትኖረው የማይመኝና የማይፈልግ የለም።
ይህ የጋራ ሕዝባዊ ፍላጎት ወደ ተግባር ሊተረጎም የሚቻለው ሁሉንም በአንድነት አስተባብሮ ሊመራ የሚችል፣የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ከሕዝብ ጋር አብሮ የሚመክር መንግስት ሲኖር ብቻ ነው።ያ መንግስት ደግሞ በጥቂቶቸ ፍላጎትና ጥረት የሚፈጠር ሳይሆን ሁሉም አውጣጥቶ በጋራ የሚፈጥረው በተለይም እርስበርስ ማጋጨትን፣ መከፋፈልን “እኛና እነሱ “ የሚል አግላይ መርሆና መርሃግብር ማጠንጠኛው ያላደረገ የህብረተቡንም አመኔታ ያገኝ ስርአትና መንግስት ሲፈጠር ብቻ ነው።
በተመሳሳይ በጠባብና አግላይ አስተሳሰብ የሚመራ ተለያይቶ የቆመ ቡድን የሚያስተጋባው ጥሪና የሚመራው ትግል የሚያመጣው ለውጥ ካለውና ሁሉም ከሚጠላውና ከሚታገለው የወያኔ ስርዓት የተሻለ አይሆንም። ስለሆነም የዚህ አይነት የትግል ሂደት ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ በቅድሚያ አውቆ አደጋው እንዳይከሰት መከላከያ ማበጀት ለጋራ ሕዝባዊ ጥቅምና ደህንነት የሚያስቡ ሁሉ ድርሻና አላፊነት ነው።በዝምታና በቸልታ ከዳር ቆመው የሚታዘቡት ድራማ አይደለም፣ነገ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ማጤኑና መዘጋጀቱ በተግባርም የትግሉ ተሳታፊ በመሆን የወደፊቱን አቅጣጫ ለሁሉም በሚበጅ መንገድ እንዲሆን የነቃ ተሳትፎ ማድረግ አስፈላጊ ነው።
እውነት ሁሉም የተቃዋሚ ሀይሎች የአምባገነንነትን ማብቃት የሕዝቡን አብሮ መኖር፣የአገራችን ኢትዮጵያን አንድነትና ልዑላዊነት የምንሻ ከሆነ በአንድነት አብረን የጋራ ሃይል የሚፈጠርበትን ዘዴ ባሰቸኳይ መሻት ይጠበቅብናል። ያ ደግሞ በቀጠሮ የምናስቀምጠው ወይም ለተወሰኑ ቡድኖች በጎ ፈቃድ የምንተወው ሳይሆን ለዛሬው ያገራችን ሁኔታ ሁላችንም የምንሰጠው አስቸኳይና ትክክለኛ መልስ ይሆናል።
እስከዛሬ ድረስ አግላይና ተከፋፍሎ የሚገኝ የፖለቲካ አካሄድ በሀገራችን ህዝብ አንድነትና የነጻነት ትግል ላይ ያሰከተለውን አሉታዊ ተጽእኖ ሁሉም የሚረዳው ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ሰፊ አለመተማመንና ጥርጣሬን በወገኖቻችን ውስጥ ዘርቶ ይገኛል። ለግፈኛው ስርአት እድሜ መራዘምም ረድቷል። ይህን ለመስበር እና መተማመንን እንደገና ለመገንባት ሰፊ ስራ መሰራት ይኖርበታል። ለዚህም የድብቅብቆሽ ፖለቲካ ተላቆ በትግስት በግልጽነታና ባርቆ አሳቢነት፤ በሰጥቶ መቀበል መንፈስ መስራት አስፈላጊ ነው።
ሰሞኑን በአሜሪካና በሌሎች የአውሮፓ ከተሞች ቁጥራቸውና ስማቸው የበዛ የፖለቲካና የብዙሃን ድርጅቶች ለየአገራቱ መንግሥታት የድጋፍ መጠየቂያ ሰልፍ ለማድረግ እየጣሩ መሆናቸውን እናያለን። ሽንጎም የዚሁ እንቅስቃሴ አከል በመሆን ይንቀሳቀሳል፡ ከድርጅት ጉድጓዱ ወጥቶ በአንድ ላይ በሰልፍ ድምጽን ማሰማቱ ተገቢና አስፈላጊ መሆኑ ቢታመንም ይህ ብቻ መፍትሔ ያመጣል ማለት ግን አይደለም። መፈትሔ እንዲመጣ፣ችግሩ እንዲወገድ ከተፈለገ በአደባባይ ለመውጣት የሚሹት የተለያየ ድርጅቶች ከሰልፍ ባሻገር በአገር ቤት ካሉት ድርጅቶች ጋር በመተባበር ትግሉን ሊመራና ሊያቀናጅ የሚችል ግብረሃይል መፍጠር ይገባቸዋል። በተቃዋሚው ጎራ ብቻ የተሰለፈው ሳይሆን በመንግሥታዊ ዘርፍም ውስጥ የተሰለፈ ግን ስርዓቱ መለወጥ አለበት ብሎ የሚያምን ዜጋ የዚሁ ሕዝባዊ ትግል አካል ሊሆን ይገባዋል። የሰው ህይወት እስካላጠፋና ሕዝብ እስካልበደለ ድረስ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ሰርተሃል ተብሎ ሊገለል አይገባም።ወንጀል የፈጸመውም ቢሆን በማስረጃ በሕጋዊ መንገድ ሊጠየቅ ይገባል እንጂ በደም ፍላት ጥቃት ሊደርስበት አይገባም። ብሄራዊ መግባባትና አገራዊ እርቅ ለነገ የማይባል ተግባር ነው፡ ያ ካልሆነ አሁንም ዞሮ ዞሮ ዜሮ ይሆናል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ ለዚህ ወሳኝነት ላለው አደረጃጀትና ትግል ተባባሪና ደጋፊ መሆኑን አሁንም በድጋሚ ሊገልጽ ይወዳል።
ለእውነተኛ ለውጥ በመከባበር ላይ የተመሰረተ አንድነት ግንባር ወሳኝ ነው።በጥቂት የውጭ አገር መንግስታትና ድርጅቶች እርዳታና ድጋፍ ሃይል አደራጅቶ ሥልጣን ለመያዝ ከመሯሯጥ ይልቅ በራስ ሕዝብ ፍቃድ፣ተሳትፎና ድጋፍ ለውጥ ማምጣት ከመቅለሉም በላይ የሚያስከብርና የሚያኮራ ነው።
የምንሻው ለውጥ ከሳት ወደ እረመጥ ወይም ከድጡ ወደማጡ እንዳይሆን እንጠንቀቅ!!!
ለመሰረታዊ ለውጥ ሁሉንም ያሳተፈ የተቀነባበረ የጋራ ትግል ወሳኝ ነው!!
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ