እስራኤልን እንዳሰብክ ኢትዮንም አስባት (አዳነ መኮነን)

May 16, 2015

ግፍና መከራው ሲፈራረቁባት

እያየህ ዝም አትበል ተሎ ድረስላት
እስራኤልን እንዳሰብክ ኢትዮንም አስባት።
በዓለም ተበትነው ሲገቡ ከእስር ቤት
አንገታቸው ሲቀላ በሌላቸው እምነት
የፊጥኚም ታስረው ሲቃጠሉ በእሳት
ከፎቅ ተወርውረው ሲጣሉ ከመሬት
ይህነን እያየህ ምነው ጨከንክባት
እስራኤልን እንዳሰብክ እሷን አስባት
በተናገርከው፤ በቃልህ መሰረት።
እንጀራ ፍለጋ ከተሰደዱበት
ልጆቿን ሰብስበህ መልሰህ አምጣላት
ከሞት የተረፉትን የአሉትን በሕይወት።
እንደ በግ መታረድ ለክርስቲያን ሰው
ዛሬ አዲስ አይደለም ድሮም የነበር ነው
አባቶች አልፈዋል ሰማእ-ት ተቀብለው።
የውጭ ጠላትማ ጥንትም የነበር ነው
አሁን እያረደን ያለ የውስጥ አይሲስ ነው
ቆዳው እኛን መስሎ ልቡ ግን ሌላ ነው።
በአለፈው ዓመት መምህሩን ስትወስድ ተማሮች ትተሃል
እስከ መጨረሻው መቼም አይማሩ ደጋግመው ወድቀዋል
የንጉሦች ንጉሥ የኃያላን ኃያል
እነሱን አንስተህ አሳየን ዘንድሮ ክፍል አጣበዋል።
ቦታውም ይለቀቅ ለቆጠረ ፊደል
ለተማረ ሰው እውቀት ለሚያካፍል።
ተማሩ ተማሩ እያለ ህዝቡ ቢነግራቸው
ከማንስ ያዩትን ትምህርቱ ይግባቸው
ሃያ አራት ዓመት ተደፍኖ ልብና አንጎላቸው።
እጃቸውን ይዞ ሰው ሲያስተምራቸው
ትምህርቱን የሚያቁት ያኔ ነው ያኔ ነው
ከነሱም ሲደርስ ከሰው የደረሰው።
ጠላት አሰፍስፎ ዙሪያውን ቢከበን
የቅዱሳን አምላክ የአባቶቻችን
እኛን ይጠብቃል ሆኖ በጎናችን
የሚያስፈራን የለም እግዚአብሔር አለልን።
እኛ አንጠብቅም ከሰዎች እርዳታ
አለልን ፈጣሪ ችግር የሚፈታ
እልል በይ ኢትዮጵያ በትንሣኤ ለታ
አንችን ለመቀደስ ሊመጣነው ጌታ።
ከትቢያው አንስቶ ዙፋን ላይ ሊያስቀምጥሽ
መላእኩ ይመጣል ምስራች ሊያበስርሽ
ጥቁሩን አውልቂና ነጩን ልብስ ልበሽ
ከፍ ብለሽ ተቀመጭ ዓለምም እንዲያይሽ።
ኢትዮጵያ ሀገራችን ወድቀሽ ትነሻለሽ፤
ልክ እንደ እስራኤል አችንም አይረሳሽ፤
ጠላትሽን አጥፍቶ አንችን ይባርካል፤
የፈጠረሽ አምላክ የኃያላን ኃያል።
ግንቦት፤፯ቀን፡ ፪ሺ፯ ዓ/ም (15/05/2015)

Previous Story

ችግሩን ሁሉ በአቶ ኃይለማርያም ላይ በማሳበብ በስልጣን መዝለቅ አይቻልም; የኢትዮጵያ የችግሮቿ ምንጭ እራሱ ኢህአዴግ/ወያኔ ነው

Next Story

Health: ጽንስ ያለጊዜው እንዲወለድ የሚያስገድደው ደም ግፊት ለእናቶች ሞትም 14 በመቶ ድርሻ አለው ተባለ

Go toTop