በግብጽ ለበርካታ ዓመታት በሰደት የኖረውና በዚያ የሚገኘውን ኢትዮጵያዊ ስደተኛ በኮሚኒቲ ለማጠናከር የተለያዩ በጎ አስተዋጽዎችን ሲያደርግ የቆየው ደራሲ ተዘራ ታምራት <<ምስጦቹ!>> ተሰኘ መጽሐፍ አሳተመ። በአገራዊ የፖለቲካና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ልዩ ልዩ ጠቃሚ ጥያቄዎችን ጭምር የሚያነሳበት ይሄው <<ምስጦቹ>> የተሰኘው መጽሐፉ በመጪው ዕሁድ በካይሮ ከተማ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ኢሳፍ አዳራሽ ካዲ ሰርዋት ጎዳና ከጋዜጠኖች ማህበር ፊት ለፊት ከቀኑ 5 ፒኤም እስከ 11 ፒኤም ያስመርቃል።
ደራሲ ተዘራ ታምራት በግብጽ በስደት በሚኖርበት ወቅት ከዚህ ቀደም ብሉ ናይል የተሰኘ መጽሔት አሳትሞ በአቅም እጥረት እሰከተቋረጠበት ለአራት እትሞችን ለስደተኛ ወገኖቹ አሰራጭቷል።
የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ ከትላንቱ እያነጻጸረና የአገሪቱ ውድቀት መነሻና መድረሻውን ብቻ ሳይሆን ነገስ የሚለውን አብይ ጥያቄ በማንሳት በስፋት የሚተነትንበት <<ምስጦቹ>> ከምረቃው በሁዋላ በወገኖቹ እገዛ በመላው ዓለም ለሚገኙ ወገኖቹ እጅ እንዲገባ ሰፊ ድጋፍ የስርጭት ድጋፍ ይፈልጋል።
” ምስጦቹ” በስድስት አብይ እርዕሶች የተከፈለ ሲሆን የገጹ ብዛት 262 ነው ። በተለይ በግብጽ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በዕሁዱ የመጽሐፉ ምርቃት ላይ እንዲገኙ ተጋብዘዋል።