ማርች 6 ቀን 2014 ዓ.ም በዘ-ሐበሻ ድረ ገጽ ላይ “በፓሪስ ኢትዮጵያዊው ከጎዳና ተዳዳሪነት ያወጡትን እናትና ልጅ ገድሎ ተሰወረ!” በሚል ዜና አስነብበናችሁ ነበር።
የዘ-ሐበሻ የአውሮፓ አካባቢ ወኪል ጋዜጠኛ ክንፉ አሰፋ በወቅቱ ይህን ዜና ሲዘግበው “እናትና ህጻን ልጅዋን ገድሎ የተሰወረው ሰውዬ ትውልዱ ኢትዮጵያዊ ሲሆን በፈረንሳይ ፓሪስ ክርተማ የጎዳና ላይ ተዳዳሪ ነበር:: ሟች ወ/ሮ ክውን ገዳሙ ትባላለች:: ከቤትዋ ወደ ስራ ቦታ ሲመላለሱ ተጠርጣሪውን የዩታል:: በጎዳናው የተጎሳቆለውን ሰው(ጉዳዩ በህግ ስለተያዘ ስሙን እዚህ ላይ አንጠቅሰውም) ስለሚያሳዝናቸው ባለፉ ባገደሙ ቁጥር እጃቸውን ይዘረጉለት ነበር::
ከግዜ በኋላ ከክረምቱ ብርድ እንዲገላገል ሲሉ ይህንን የጎዳና ተዳዳሪ ለግዜው በቤታቸው አስጠጉት:: የአቅማቸውን እየረዱት አብረው ለወራት ኖሩ:: ባለፈው ሳምንት (ሜይ መጀመሪያ ላይ) አንድ አስደንጋጭ ክስተት በቤተሰቡ ውስጥ ተፈጸመ:: በችግሩ ያስጠጉት ሰው ከተኙበት በጭካኔ ገድሏቸው አመለጠ::
ወ/ሮ ክውን ገዳሙ የሶስት ልጆች እናት ሲሆኑ በፈረንሳይ ፓሪስ ለረጅም ግዜ ኖረዋል:: የሶስት ልጆች እናትም ናቸው:: ያለአባት ከሚያሳድጓቸውን ሶስት ልጆች ውስጥ አንደኛዋና የሁሉም ታናሽ ከሆነችው ጋር ላይመለሱ ይህችን አለም ተሰናበቱ::
ገዳዩ ጭካኔ በተሞላበት መንገድ በጩቤ ሰነጣትቆ ነው እናትና ልጅን ለህልፈት የዳረገው- እንደ ፈረንሳይ የዜና ምንጭ:: ባጎረሱት እጅ ተነከሱ:: ደግ ባደረጉ ምላሹ ግድያ ሆነ: ለዚያውም አረመኔያዊ ግድያ::
ነብሰ ገዳዩ ለግዜው ተሰውሯል:: የፈረንሳይ ፖሊስ ከኢንተርፖል ጋር በመሆን ጉዳዩን በጥብቅ ይዞታል:: እኛም እየተከታተልን ጉዳዩ ምን እንደደረሰ እናቀርብላችኋላን::” ይል ነበር በወቅቱ ያቀረብነው ዜና።
ዛሬ ከፈረንሳይ በደረን መረጃ መሠረት ኢትዮጵያዊቷን እናት ልጅ የገደለው ወጣት በፈረንሳይ ማርሴይ ከተማ ፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሏል።
ቀጣዩን ሁኔታ መረጃዎችን አሰባስበን ተከታትለን እንዘግባለን።