(ከዚህ ቀደም ኡጋንዳ ላይ ለኳስ ጨዋታ ሄዶ ጥገኝነት የጠየቁት የኤርትራ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች)
ከዳዊት በጋሻው
ኤርትራ እ.ኤ.አ ለ2015 በሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ላይ እንደማትሳተፍና እራሷን ማግለሏን የአገሪቱ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።
የኤርትራ ብሔራዊ ቡድን ( የቀይ ባህር ግመሎች) የኤርትራ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ)እንደተ ናገረው፤ ለ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚኖረውን ጨዋታ ሰርዟል።
ኤርትራ ይህንን ጨዋታ ለመሰረዟ ምንም ምክንያት አለማቅረቧ ተዘግቧል።
በዚህም መሰረት ደቡብ ሱዳን ከኤርትራ መገለል በኋላ በቀጥታ ወደሚቀጥለው የጥሎ ማለፍ ውድድር ማለፏን የአፍሪካ እግር ኳሰ ኮንፌዴሬሽን አስታውቋል። በሞሮኮ በሚዘጋጀው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ላይም የኤርትራ ብሔራዊ ቡድንን እንደማናየው ተረጋግጧል።
የኤርትራ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጨዋታዎችን እየሰረዘ ሲሆን፤ የአገር ውስጥ ተጫዋቾች ብቻ በሚሳተፉበት የአፍሪካ ዋንጫ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር የነበረውን ጨዋታ መሰረዙ ይታወሳል።
በ2012 የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ (ሴካፋ) ላይ 17 የኤርትራ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾችና የህክምና ዶክተሩን ጨምሮ በኡጋንዳ መጥፋታቸው ይታወሳል። በተጨማሪም እ.ኤ.አ በ2011እና በ2013 የኤርትራ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች በታንዛኒያ ጥገኝነት መጠየቃቸው የሚታወስ ሲሆን በ2009 ደግሞ 12 የኤርትራ ልዑካን ቡድን አባላት በኬንያ በተዘጋጀ ውድድር መጥፋታቸው ይታወሳል።
እ.ኤ.አ 2012 የለንደን ኦሊምፒክ በኋላ አራት ኤርትራውያን አትሌቶች የፖለቲካ ጥገኝነት ጠይቀው እንደነበር ቢቢሲ ዘግቧል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት እንደሚያመለ ክተው ከ2000 እስከ 3000 ኤርትራውያን ትንሿን የምስራቅ አፍሪካ አገር ለቀው መውጣታቸውን ይጠቁማል።
ደቡብ ሱዳን ከኤርትራ መገለል በኋላ በቀጥታ ወደ ቀጣዩ ዙር ያለፈ ሲሆን ቀጣይ ተጋጣሚውን ሚያዚያ 27 ቀን 2014 ያውቃል።