አማራን ላሞራ-የወያኔ ሴራ!

May 1, 2013

ይታረድ ፍሪዳዉ ግባልኝ ከቤቴ

እነሆ የላም ልጅ ከርጎ ከወተቴ

የእግዚአብሔር እንግዳ እረፍ ከመደቡ

እግርህም ይታጠብ በወጉ በደንቡ

ያዳም ልጅ እኮ ነን የእጆቹ ሥራ

ተጫወት ወንድሜ እንግዲህ አትፍራ!

እንዲህ እንዳልነበር ባህል ልማዳችን

ዉጣልን አማራ ጥፋ ከፊታችን

ጫንልኝ ደራርበህ ዳርግልኝ ላደጋ

ጎጃምና ጎንደር ወሎም ሆነ ቡልጋ

እየገፈተርከዉ በሰደፍ ባለንጋ!

እንዳልተሰዋለት እንዳልተዋደቀ

ላገር ስልጣኔ እንዳልተጨነቀ

ለሰንደቅ ዓላማዉ ሌት ተቀን የተጋ

ኢትዮጵያን ያለ ሰዉ የለዉም ወይ ዋጋ?

ዘዉዱን ከክህነት ያስተባበራችሁ

የቅዱሳን አገር ከቶ ምን አላችሁ

በግሸኗ ማርያም በክቡር መስቀሉ

አገር እያጠፉ ወገን ሲበድሉ

ባንዳ ሲዘባነን አርበኛዉ ሲጉላላ

አይታጠንም ወይ ቅዱስ ላሊበላ?

ዓይኑ እስኪታክተዉ ጋምቤላን ሲመራ

ህንዱ ካራቱሬ ሊተክል ሊዘራ

ቻይና ኮሚኒስቱ ስንት ግፍ ሲሰራ

በገዛ አገራችን ሲኮራ ሲዳራ

ምን ዓይነት ልማት ነዉ አማራን ላሞራ

ይናገር መቅደላ ይፋረደኝ ቋራ!!

ከፋኑኤል አበበ

ኒዮርክ 


 

Previous Story

የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት የፊታችን ሐሙስ ከቦታው ይነሳል

Next Story

ዶ/ር መረራ ጉዲና እና አቶ ገብሩ አስራት ለአንድነት ፓርቲን ጥያቄ ምላሽ ሰጡ

Go toTop