እሳት በሌለበት ጭስ የለም (There’s no smoke where there’s no fire.)

February 10, 2025

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

አፍንጫ ሲመታ ዐይን እያለቀ፤
የፊታችን ነገር ክፉኛ ታመሰ፡፡

ይመስለናል ለኛ ጨልሞ የሚቀር፤
ቀኒቱ ቀርባለች ዕብቁ ሊበጠር፡፡

የጨለማው ግዝፈት ተስፋ ቢያስቆርጥም፤
የትንሣኤው ብርሃን መገለጡ አይቀርም፡፡

ያኔ ቢጸጸቱ ቢያወርዱ የ’ንባ ጎርፍ፤
ምንም አይፈይድም ካሁኑ ነው ማረፍ፡፡

 

የመጨረሻውን መጀመሪያ ላምጣው፡፡ እናም ከብሶቴ በፊት ተስፋየን አስቀደምኩ፡፡ አንዳንዴ ማበድ ጥሩ ነው፡፡ በተለይ ልጓም ያለው ዕብደት በአንዳንድ ወንድሞቻችን ከምናየው የለዬለት የሚመስልና ከሁሉም ጋር የሚያናችፍ ዕብደት ራቅ በሚል ሁኔታ በመጠኑ አበድ ማለት “ማንም አያውቅብኝም” የሚልን አጨናብሮ የገባ አስመሳይ ወይም ለከርሱ ያደረ ኅሊናቢስ አጋሰስ ቆም ብሎ እንዲያስብ ይረዳልና አይጠላም፡፡  ወዳስቀደምኩት የመጨረሻ መጀመሪያየ ልሂድ፡፡

አሁን በምለው ማንም ጧ ፍጥርቅ ይበል፡፡ ምድረ ኦሮሙማና  የኦሮሙማ የትሮይ ፈረስ ባንዳ አማራም በምለው ድብን ቅጥል ይበል፡፡ የምለው እውነት በመሆኑ ይህን አጭር መልእክት የሚያነብ መልካም ዜጋ ሁሉ ደስ እንዲሰኝ በፈጣሪ ስም እጋብዛለሁ፡፡ የሆነውና እየሆነ ያለው ሁሉ መሆን ስላለበት እንጂ ብዙዎቻችን አዘውትረን እንደምንለው አምላክ ኢትዮጵያንና አማራን ስለጠላ አይደለም፤ በመሠረቱ የአምላክን በረከት ረድኤት የሚያሰናክልብን  የኃጢኣታችንና የክፋታችን ግርዶሽ መደንደን እንጂ አምላክ ማንንም በተለዬ ሁናቴ የሚወድ ወይም የሚጠላ ነው ብዬ አላምንም ወይም ቢያንስ አይመስለኝም፡፡ እናም እኛ ወደርሱ ለመመለስ በቆረጥን ማግሥት የሚሆነው ሌላ ነው – ያም ይሆናል፡፡ የፈጣሪና የምድር የጊዜ ቀመር በመለያየቱ በእኔን መሰል ወፈፌዎችና የልባቸውን ተናጋሪዎች እየተነገሩ በተግባር የተፈጸሙ ብዙ ናቸው፡፡ አሁን የምለውም ከነዚያ አንዱ ነው፡፡

አዎ፣ እደግመዋለሁ – ጠላት እርር ቅጥል በል፡፡ ኦሮሙማም የፖለቲካ ብስለትና የሰውነት ሚዛን ኖሮት አማራ የሚመስሉ ግን ትውልዳቸውና ዘራቸው የሚያጠራጥር፣ በትምህርታቸው ያልገፉ ዘበኛና ዕቃ ተሸካሚዎች የነበሩ፣ ከሆዳቸው በላይ ስለማንምና ስለምንም የማያስቡ፣ በአማራ ስም ለወያኔና ለኦነግ/ኦህዲድ ሸኔ ባርነት ያደሩ ማይማን በጭብጥ ምሥር ወንድሙን እንደለወጠው እንደኤሣው እነሱም ወንድሞቻቸውን የሸጡ፣ የአማራን ክልል ጄኖሣይድ ካወጀበት ጠላቱ በላይ እያሰቃያችሁ የምትገኙ የአማራ ብል.ግናዎችም ድብን እርር በሉ፡፡ ከፊታችሁ ያለው እሳት በቅድሚያ እናንተን ነው የሚፈጀው፡፡ ሎሳንጀለሳዊው እሳት እየተግለበለበ በመምጣት ላይ ነው፡፡ አማራን እፈጃለሁ ብሎ የተነሣ አማራና ኦሮሙማ መቀበሪያው ደርሷል፡፡

ኢትዮጵያ ሰሜን ኮርያን አይደለችም፡፡ ኢትዮጵያ ፊጂን ወይም ሃይቲን አይደለችም፡፡ ኢትዮጵያ ቱኒዚያንና የመንን አይደለችም፡፡ ሌላውን ሁሉ እንተወው፡፡ ኢትዮጵያ፣ ከተፈጠረች 300 ዓመት ሊሞላት 51 ዓመታት የሚቀሯትን ታላቋን አሜሪካ አይደለችም፡፡ ኢትዮጵያ ለክርስቶስ እናት ለእመብርሃን አሥራት በኩራት የተሰጠች የተስፋ ምድር ናት፡፡ የአሁኑን ዘመነ መርገምት አንይ፤ ይህን መሰል አስቀያሚና ደም አፋሳሽ ዘመናት ተጭነውባት አፈሩን አራግፋ ከሞት የተነሳችባቸው አጋጣሚዎች በታሪክ ብዙ ናቸው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ተደጋግሞ ስሟ የተጠቀሰው ይህች ቅድስተ ቅዱሣን ሀገር ባለ ገናናና ረጂም ታሪክ ባለቤት ሆና ሳለ  “እባብ የልቡን አይቶ እግሩን ነሣው” እንዲሉ በሃይማኖቷና በፖለቲካዋ በገቡባት የአጋንንት ውላጆች ሣቢያ ይሄውና ወገቡን እንደተመታ ከይሲ መሽመድመድ ከጀመረች በትንሹ ግማሽ ምዕተ ዓመት ሆናት፡፡ በሃይማኖቱም በፖለቲካውም በከፍተኛ አመራርነት ሳይቀር የሠረጉባትና የተሰገሰጉባት ከርሣሞች ሃይማኖቱንም ፖለቲካውንም የርገረም ወይም አካማሌ አደረጉትና መሣቂያ መዘባበቻ ሆንን፡፡ በሀሰተኛ ንግግሩ ሊቀ ሣጥናኤልን የሚያስከነዳ የውሸት ኮሎኔልና የውሸት ዶክተር ማይም ደንቆሮ መሪ የገጠመንም በክፋታችን ምክንያት – ባለመተዛዘናችን ምክንያት – እንደአንድ ሀገር ዜጋም ብቻ ሳይሆን እንደሰውም ባለመተሳሰባችን ምክንያት ፈጣሪ ስለተጣላን እንጂ እኛ ይህን የመሰለ “ወላድ አትይህ” የሚባል ጅምር ሰው የሚገባን ሆነን አልነበረም – “ጅምር ሰው” ያልኩት በቅርጹ ሰው መስሎ በባሕርዩ ግን ዐውሬ በመሆኑ ለሌላ ፍጡርነት ታቅዶ በሰው አምሳል በመውጣቱ ነው፡፡ ይህን እርጉም የወለዱ ባይፈጠሩ ይሻላቸው ነበር፡፡ ይሄ የሰንበት ጽንስ አንዲትን ታላቅ ታሪካዊት ሀገር ለጊዜውም ቢሆን አተረማመሳት፡፡

ለማንኛውም አሁን ያለው ሁኔታ በእጅጉ የሚያስፈራ ቢሆንም ለአንድዬ የሚሣነው ነገር የለምና ከጥንት ከጧትም የተስፋ ቃል አለና በቅርቡ የሚሆነው እንደዚህ ነው፡፡ ሀገር በሌለችበት ሁኔታ፣ ሕዝብና የሕዝብ ሀብት በድሮንና በታንክ ባልተወለደ አንጀት በየቀኑ እየጋዬ ባለበት ሁኔታ እርስ በርሱ እየተካሰሰና እየተገዳደለም ጭምር አሁን በጫካ ከሚተረማመሰው ይሁን ከሌላ ቦታ ከየት እንደሆነ አላውቅም ግን በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመራና ባለፉት ሁለትና ሦስት መንግሥታዊ ሥርዓቶች የግፍና የበደል ሰቆቃ የተቆጣ፣ በስሜትና በጀግንነት ወደአንበሣና ነብርነትም የተለወጠ ሕዝባዊ ሠራዊት ባላሰብነው ሰዓት ካላሰብነው አቅጣጫ ወደ አራት ኪሎ ይመጣል፡፡ ያ ኃይል እንዳሁኑ የኦሮሙማ ጭፍን ዐረመኔ መንጋ አእምሮ የሌለው ኃይል አይደለም፤ እንደወያኔም በአስተሳሰብ ከአፍ እስካፍንጫ የተቀነበበ አይደለም፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁሉንም መንግሥታዊ ተቋማት ይቆጣጠራል፡፡ ሀገራችንንም በአጭር ጊዜ ውስጥ ያረጋጋል፡፡ የተደበቁ ብርቅዬ ዜጎች አደባባይ ይወጣሉ፤ የተሰደዱም ይመለሳሉ፡፡ በዕውቀትና በልምዳቸውም ሀገራቸውን “ሀ” ብለው መገንባት ይጀምራሉ፡፡ በጥቂት ዓመታትም ሀገራችን በጉግማንጉጎች ያጣችውን ሥልጣኔና ሰብኣዊ ክብር ታገኛለች፡፡ ያ ከሰው የተፈጠረ የፖለቲካና የሃይማኖት ግብረ ኃይል ኢትዮጵያን ወደነበረችበት የታሪክ ማማዋ ይመልሳታል፤ ሰው በሰውነቱና በዜግነቱ የሚከበርበት፣ ብሶቱ የሚደመጥበት፣ ከዐረመኔያዊ አገዛዝ የሚገላገልበት ወርቃማ ዘመን በአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ሥራውን በቁጭትና በሙሉ ኃይል ይጀምራል፡፡ በከርሳሞችና በገዳዮች ላይም ትክክለኛውን ብያኔ ይሰጣል፡፡ ሁሉም እንደሥራው የሚያገኝበትን ሥርዓት ይዘረጋል፡፡ “አንተ ማነህ፣ አንቺ ማነሽ” ተብሎ በዘርና በጎሣ ሣይሆን በችሎታ፣ በልምድና በትምህርት የሥልጣንም ይሁን ክፍት የሥራ ቦታዎች የሚሞሉበት ደምብና ሥርዓት ይተከላል፡፡ ያኔ “አማራ ነኝ፣ ኦሮሞ ነኝ፣ ትግሬ ነኝ…” የሚል ቡራ ከረዩ በታሪክ የሚወሳ እንጂ ሥራ ላይ የሚውል የአስተዳደር ሥልት አይሆንም፡፡

ወደመጀመሪያየ ተመለስኩ፡፡ በጫካ ውስጥ ያላችሁ ወንድሞቻችን ብዙ የምትታሙባቸው ነገሮች አሉ – መሳሳትም ሆነ መታማት ያለ ነውና ብዙም አያስደንቅም፡፡ ይሁንና “ሕዝቡ ምን ይላል?” ለሚለው አስተያየትና ትችት ጆሮ መስጠት የአሁኖቹና ቀደምት መሪዎች ካደረሱት ጥፋትና ከደረሰባቸው ቅጣት ራስን ለማዳን ይጠቅማልና ችላ ማለት በፍጹም አይገባም፡፡ ስለሰውነት ውፍረትና ስለአመጋገባችሁ ወይም ስለ “አተኛኘታችሁ” ብዙም መናገር አልፈልግም – መናገር የሚያስችለኝ ሁኔታ ቢኖርም ወደግላዊ ምግባራት መግባቱ ቀዳዳን ይበልጥ ማስፋት ነው፡፡ ሆኖም አራት ኪሎ የሚገኝና በጫካ የሚገኝ የነጻነት ትግል አመራር በብዙ ነገር እንደሚለያዩ መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ጭብጥ ቆሎ የሚናፍቅን የነፃነት አርበኛ ወደ ድል ጫፍ ለማድረስ አዋጊና ተዋጊ ሊያከብሯቸው የሚገቡ የዲስፕሊን መርሆዎች መኖራቸውን እንዳይረሱ በገደምዳሜም ቢሆን ማስታወሱ ተገቢም ወቅታዊም ነው፡፡  በዋናነት ግን የምለው ተስማሙ ነው፤ በእናንተ መቆራቆስ ጠላታችሁ ጊዜ እያገኘ ነው፤ ሕዝባችሁም ተስፋ እየቆረጠ አማራጭም እያጣ ለባሰ አእምሯዊ ቀውስ እየተዳረገ ነው – እውነቱን የምናገረው፤ መሸፋፈን ለማንም አይጠቅምም – ብሂሉም “አለባብሰው ቢያርሱ ባረም ይመለሱ” ይላልና መሞከሻሸቱ እየጎዳን እንጂ እየጠቀመን አይደለም፡፡ የእናንተ አለመስማማት ለወሮበላ የሶሻል ሚዲያ ተዳዳሪ የገቢ ምንጭና የመነታረኪያ አጀንዳ እየሆነ ነው – አማራ እየደረሰበት ያለው ፍዳ ሌላ – ምቹ ሥፍራ (comfort zone) ሆኖ በነገር ጅራፍ የሚሞሸላለቀው የሶሻል ሚዲያው ሠራዊት ሌላ፤ በሰው ቁስል እንጨት የመስደድ ያህል ነው፡፡ ለፋኖዎች ትስማማለች ብዬ የማስባት ብዙ ጊዜ የምትነገር አንዲት መጽሐፍ ቅዱሣዊ አባባል አለች፡- “እርስ በርሷ የተከፋፈለች መንግሥት አትጸናም” የምትል፡፡ ትክክል ነው፡፡ ብዙ ሰው ስከታተል በእናንተ ተስፋ ቆርጧል ወይም እየቆረጠ ነው፡፡ እኔ የምጠብቀው እግዚአብሔርንም ጭምር እንጂ እናንተን ብቻ ባለመሆኑ እስካሁን ብዕሬንም አልሰቀልኩም ተስፋየንም አልቆረጥኩም፡፡ የጊዜ ጉዳይ እንጂ እንኳንስ ይህን ሰው አራጅና የሰው ደምና ሥጋ ተቀላቢ ይቅርና ስንትና ስንት ደጋግ የመንግሥታት መሪዎችን ሕይወትም ባልታሰበ ሰዓት የሚወስድ አምላክ እያለኝ በዚህ ጭራቅ በሥልጣን ላይ መቆየት ብዙ አልጨነቅም – መሄጃው መድረሱን በሚገባ አውቃለሁና፡፡ ተስፋ በሚቆርጡ ወንድሞች ግን አዝናለሁ – ግን አልፈርድባቸውም፡፡ ሁሉም በዚህ መልክ ከሀገሩ ገለል ማለትን ከመረጠ ግን የግፍ አገዛዙ ዘመን መራዘሙ አይቀርም – የጊዜ ጉዳይ እንጂ ማለፉ እውነት ቢሆንም፡፡ ይህ የሰይጣን አገዛዝ ሲራዘም ደግሞ ጭራቁ ልጅ ደስታው ወደር አይገኝለትም፡፡ እርሱ እንደሆነ አንዴውኑ አብዷልና የሚሠራውን አያውቅም፡፡ እኛ ግን ቢያንስ ወደሰማይ እናልቅስ፤ ወደላይ የሚረጭ ዕንባ ትልቅ ዋጋ አለው፤ ልባዊ ጸሎት ከዳመና በታች አይቀርም፡፡ በኑሮ ውድነቱ እንኳን ምን እየደረሰብን እንደሆነ ግልጽ ነው – በየቀኑ እያስለቀሱን ነው፤ ቤታችን የኛ አይመስለንም – መቼ በላያችን ላይ እንደሚያፈርሱት አናውቅምና፡፡ በሥራ ቦታችን ላይ ያለነው የዛፍ ላይ እንቅልፍ ያህል ነው – ሊያውም ሦስት ቀናትን ለማያቆይ ደሞዝ፡፡ ከቤት መውጣታችንን እንጂ ስለመመለሳችን እርግጠኞች አይደለንም – በምንሰማውና በምናነበው ነገር ሁሉ አንጎላችን ሊፈነዳ የደረስን ብዙ ነን፡፡ በጥቅሉ አቢይ በሚሉት አንድ ዕብድ ሕጻን ምክንያት ተነግሮ በማያልቅ ጭንቀትና ጥበት፣ ተጽፎ በማያልቅ መከራና ስቃይ ውስጥ እንገኛለን፡፡ ከዚህ በተያያዘ ግብርና ቀረጥ የምንከፍልበት ርዕስ ደግሞ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መጥቶ በኪሣችን አምስት ሣሳንቲም እንዳትገኝ የሚደረገው “”መንግሥታዊ” ጥረት በእጅጉ የሚገርም ሆኗል፡፡ 35 መቶኛው በግብር እና 12 መቶኛው በጡረታ መልክ ተቀንሶ ከሚሰጥህ ደሞዝ ላይ በወጪዎችህ ከሦስትና አራት ጊዜም በላይ ቫት ልትከፍል ትችላለህ – ባንዱ ደሞዝ፡፡ የሞባይል ካርድ ስትሞላ ቫት መክፈል ማለት ምን ይባላል ለምሣሌ? በወያኔ አገዛዝ መጨረሻ አካባቢ በዛ ቢባል 300 ብር የምከፍልበት ወርኃዊ የመብራት ፍጆታ ለተመሳሳይ የኃይል አጠቃቀም አሁን 6000 ብር እንድከፍል መገደዴ ምን የሚሉት ዕድገት ነው? በደርግ ዘመን የቤት ቆጣሪ በኪሎ ዋት 0.09 አንስቶ በየ50 ኪሎ ዋቱ እየተለወጠ ትልቁ ክፍያ 0.029 እንደነበር ማን ያስታውሳል? ምን ዓይነቱን የቀን ጅብ ጣለብን? ለማንኛውም ከፍ ሲል ላልኩት ነገር ተዘጋጁ፡፡ የጨለማው መበርታት የንጋቱን መቃረብ ያሳያልና ቸልተኝነታችን አላስፈላጊ ዋጋ እንዳያስከፍለን ራሳችንን ከሀገራዊ ፖለቲካ ብዙም አናርቅ፡፡

ተስፋ መቁረጥን ራሱን ተስፋ እናስቆርጠው – ጓዶች!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

“ጠበቃዎችን እያነጋገርኩ ነው፣ በአቪዬሽን ህግ ሊከለክሉኝ እንደማይችሉ ተነግሮኛል”- አቶ ልደቱ አያሌው

Go toTop