“ጠበቃዎችን እያነጋገርኩ ነው፣ በአቪዬሽን ህግ ሊከለክሉኝ እንደማይችሉ ተነግሮኛል”- አቶ ልደቱ አያሌው

February 10, 2025

ዛሬ ጠዋት ከአሜሪካ ወደ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ለመጓዝ በአትላንታ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ቢገኙም እንዳይሳፈሩ የተደረጉት ፖለቲከኛው አቶ ልደቱ አያሌው ጉዳዩን በህግ ሊይዙት እንደሚችሉ ተናገሩ።

“አየር ማረፊያው ስገኝ ሰራተኞቹ የ boarding pass ማውጣት እምቢ አላቸው፣ የአየር መንገዱ ሰራተኞች ያሉኝ በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲን አነጋግሬ የተለየ ፈቃድ ካልተሰጠኝ በስተቀር ወደ ኢትዮጵያ መጓዝ እንደማልችል ነው” ብለው ለመሠረት ሚድያ የተናገሩት አቶ ልደቱ ዋሽንግተን ወደሚገኘው ኤምባሲ ስልክ ቢደውሉም ጥሪ የሚያነሳ ማሽን እንጂ የኤምባሲው ሰራተኖችን ማነጋገር እንዳልቻሉ ጠቅሰዋል።

“ወደ ሀገሬ መሄድ ማንም ሊከለክለኝ አይችልም፣ ሀገሬ ከሄድኩ በኋላ ግን ማሰር ይችላሉ። በአሸባሪነት ወንጀል ሊከሰኝ እንደሚፈልግና በቁጥጥር ስር እንድውል ከኢንተር-ፖል ጋር ጭምር እየተነጋገረ እንደሆነ ሲገልፅ የነበረው የኢትዮዽያ መንግስት ዛሬ በራሴ ፈቃድ ወደ አገሬ ለመመለስ ስሞክር በእኔ ላይ ህገ-ወጥ ክልከላ ማድረጉ አስገርሞኛል” ያሉት ፖለቲከኛው ከአመታት በፊት ለህክምና ከሀገር ሲወጡ ከልክሏቸው እንደነበር፣ አሁን ደግሞ ሊመለሱ ሲፈልጉ መከልከሉ እንቆቅልሽ እንደሆነባቸው ጨምረው ተናግረዋል።

“መሄድ አለብኝ፣ በመብቴ ጉዳይ አልደራደርም። ጠበቆችም እያነጋገሩኝ ነው፣ በአቪዬሽን ህግ ሊከለክሉኝ እንደማይችሉ ተነግሮኛል” በማለት ወደ ሀገር ቤት በመመለስ በሀገራቸው የፖለቲካ ምህዳር ላይ ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ ቁርጠኛ አቋም እንዳላቸው ለሚድያችን ተናገረዋል።

መረጃን ከመሠረት!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

ችሮታ (በእውቀቱ ስዩም)

Go toTop